ካርታ

ከ 1 ሰአት በፊት

በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ዋርዴር ከተማ በአንድ መስጂድ ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው የአገር ሽማግሌ እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሶማሊ ተናገሩ።

ማክሰኞ መስከረም 7/2017 ዓ.ም. በምሥራቃዊ የክልሉ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ዶሎ ዞን ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት ምክንያቱ፤ በአካባቢው ባሉ ጎሳዎች መካከል ከዚህ ቀደም ተከስቶ ከነበረ ግጭት ጋር ሳይያያዝ እንደማይቀር ተነግሯል።

አቂል ሞሐመድ ሞሐሙድ የተባሉት የአካባቢው የአገር ሽማግሌ ጥቃቱ መፈጸሙን እና ወጣቶቹ መገደላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የተገደሉት ወጣቶች የሃይማኖት ተማሪዎች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የአገር ሽማግሌው “በስድስቱ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ድርጊት እጅግ ዘግናኝ ነው” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ የተገደሉት ኩጂር በተባለው መስጂድ ውስጥ ለሶላት እየተዘጋጁ ሳለ መሆኑን የገለጹት የአገር ሽማግሌው፤ “ታጣቂዎቹ በአነስ ባለ መኪና ወደ መስጂዱ መጥተው በልጆቹ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል” ብለዋል።

በጥቃቱ መስጂድ ውስጥ የተገደሉት ስድስቱ ወጣቶች ወንዶች የቀብር ሥነ ሥርዓት ረቡዕ ዕለት እዚያው ዋርዴር ከተማ ውስጥ መፈጸሙን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ግድያው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ድንጋጤና የፈጠረ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት አጋጥሞ የነበረ የጎሳ ግጭትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ከወራት በፊት ወንድማማች በሆኑት ጎሳዎች መካከል ግጭት አጋጥሞ እንደነበር ነዋሪዎች አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ዶሎ ዞን ዋርዴር ወረዳ በሁለት ንዑስ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉን አንድ የክልሉ ባለሥልጣን እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በተጨማሪም በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ “በሁለት ወንድማማች ንዑስ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል” ብሎ ነበር።

በወቅቱ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲቃድር ረሺድ በተከሰተው ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በክልሉ የሚሠራው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመድ መሐመድ ደግሞ ሟቾች አራት መሆናቸውን ገልጸው ነበር።

ይህ በዚህ ሳምንት በመስጂድ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት ከወራት በፊት አጋጥሞ ከነበረው ግጭት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ተገምቷል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ተሰማርተው የደኅንነት ጥበቃ እና ስለግድያ ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ክስተቱን በተመለከተ የዶሎ ዞን ኃላፊዎችም ሆነ የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።