አበባ የያዘች ሴት

ከ 5 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመቀጠላቸው በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ተመልሳ መግባት የምትችልበት ዕድል ገና መሆኑን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ገልጸዋል።

ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት ያስቆመውን ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ውስጥ የተወያዩት አምባሳደሩ፤ በጉብኝታቸው መጠናቀቂያ ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሉት።

ልዩ መልዕክተኛው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አጎዋን በተመለከተ በአገሪቱ “አሁንም ድርስ የመብት ጥሰት እና አሰቃቂ ድርጊቶች ቀጥለዋል። ይህ ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ መመለስ አትችልም” ብለዋል።

የለተወሰኑ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ እና ከታሪፍ ነጻ በመሆን ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ እንድትወጣ የተደረገው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

የፌዴራል መንግሥቱ እና ህወሓት ለሁለት ዓመታት ባካሄዱት ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ከአውሮፓውያኑ 2022 መግቢያ (ጥር 2014 ዓ.ም) ነው ኢትዮጵያ ከዚህ ዕደል ውጪ የሆነችው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2000 ይፋ በተደረገው በዚህ የቀረጥ ነጻ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ 38 አገራት አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ምርቶችን ለአሜሪካ ገበያ ስታቀርብ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በአጎዋ አማካኝነት ከ20 ዓመት በላይ ጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ምርቶችን ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ለመቶ ሺዎች ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች።

በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ስታገኝበት ነበር።

አሜሪካ ጦርነቱ እንዲቆም ካቀረበችው ተደጋጋሚ ጥሪ እና ግፊት በኋላ የዕግድ ውሳኔውን ይፋ ባደረገችበት ጊዜ፣ በአገሪቱ ያለው ቀውስ በ60 ቀናት ውስጥ መሻሻል ካሳየ እና መንግሥት የሚጠበቅበትን ካደረገ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ አጎዋ ልትመለስ እንደምትችል ተገልጾ ነበር።

ውሳኔው ከተላለፈ ሁለት ዓመታት በላይ ቢያልፉትም እንዲሁም ለዕግዱ ምክንያት የሆነው ጦርነት ቢያበቃም የአሜሪካ አቋም አሁንም ድረስ አልተቀየረም።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በቅርቡ በሰጡት መግለጫ “በትግራይ ሰላም መጣ ማለት ሥራው ተጠናቋል ማለት አይደለም” በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ችግሮችም በንግግር እንዲፈቱ ያስፈልጋል ብለዋ።

ለመሆኑ አጎዋ ምንድን ነው? ለኢትዮጵያ ምንስ ጥቅም አስገኘ?

አጎዋ ከቀረጥ ነጻ የንግድ ዕድል

አጎዋ (The African Growth and Opportunity Act) አሜሪካ ያስቀመጠቻቸውን መስፈርቶች ለሚያሟሉ እና ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገራት የቀረበ የንግድ ዕድል ነው። የዚህ ዕድል ተጠቃሚ አገራት የተመረጡ ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ለአሜሪካ ገበያ ማቅረብ ይችላሉ።

አሜሪካ በአጎዋ የሚካተቱ አገራት ማሟላት ያለባቸውን መሰፈረቶች አስቀምጣለች።

ይህም የሕግ የበላይነትን ለማስፈን መስራት፣ የሰብአዊ እና የሠራተኛ መብቶችን ማክበር፣ ፖለቲካዊ ብዝሃነትን ማስተናገድ፣ ገበያ መር ኢኮኖሚን መከተል ወይም ለመከተል መሥራትን ያካትታል።

በተጨማሪም አሜሪካ በዕድሉ ተጠቃሚ አገራት ውስጥ ላላት ንግድ እና ኢንቨስትመንት የተመቸ ሁኔታ መፈጠር ደግሞ ሌላኛው መስፈርት ነው።

የአሜሪካ ከሰሀራ በታች ከቀረጥ ነጻ ድንጋጌ እነዚህ መስፈርቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ወይም ዕድሉ ይዞ ለመቆየት ወሳኝ እንደሆነ ሰፍሯል።

በአሜሪካ የተቀመጠው መስፈርት ይህ ቢሆንም አንዳንዴም በአወዛጋቢ ሁኔታ አገራት ከዚህ ዕድል ይሰራዛሉ። በአውሮፓውያኑ 2018 ሩዋንዳ ‘ሰልባጅ’ ልብሶችን ወደ አገሯ አልሰገባም በማለቷ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገሪቱን ከዚህ ዕደል ተጠቃሚነት አስውጥተዋት ነበር።

አጎዋ እንደ አውሮፓውያኑ በግንቦት 18/2000 በአሜሪካ ምክር ቤት ይሁንታን አግኝቶ ነበር ተግባራዊ የሆነው። ይህ ድንጋጌ ከ25 ዓመታት በኋላ በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ክለሳ ይደረግበታል።

አጎዋ ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2008 እንዲተገበር ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ እስከ 2015 እንዲራዘም አድርገውታል።

የኢንደስትሪ ሰርተኛ

በ2015 ላይ ደግሞ ይህ ዕድል እስከ 2025 እንዲራዘም በሥልጣን ላይ የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በፊርማቸው አጽደቀዋል።

በአሜሪካ መንግሥት በጎ ፈቃድ አማካይነት የቀረበው እና አፍሪካን በሚመለከት የአገሪቱ የንግድ ፖሊስ አካል የሆነው አጎዋ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት እና በአሜሪካ መካከል የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስርን የሚያበረታታ ነው።

በተጨማሪም በዕድሉ ተጠቃሚ አገራት ውስጥ ያሉ ንግድ መስኮችን ለአሜሪካ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያን እና ዕድገትን መደገፍ ቀዳሚ ግቦቹ ናቸው።

አጎዋ በደቡብ አፍሪካ ከሚገጣጠሙ ቅንጡዎቹ ቢኤምደብሊው እና መርሰዲስ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ በኬንያ እስከሚመረቱት አበባ የሚጠቀላሉ ከ1800 በላይ ምርቶች በዚህ ዕድል አማካይነት ወደ አሜሪካ ይገባሉ።

በዚህ ነጻ የንግድ ዕድል በአፍሪካ ውስጥ ካሉ 54 አገራት መካከል አብዛኞቹ ማለትም 35 አገራት ምርቶቻቸውን ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ናቸው።

ኢትዮጵያ ከአጎዋ ምን ስትጠቀም ነበር?

በአጎዋ አማካኝነት ወደ አሜሪካ ከፍተኛ ምርት የምትልከው አገር ደቡብ አፍሪካ ናት። ተሽከርካሪዎችን፣ ጌጣጌጥ እና ብረታ ብረትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ምርቶችን በመላክ ወደ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ንግድ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

ናይጀሪያ በአብዛኛው ነዳጅ በመላክ 1.4 በሊዮን ዶላር በማግኘት እንዲሁም ኬንያ 523 ሚሊዮን ዶላር በማትረፍ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ዕድል በኩል የሚልኩት ምርት እና የሚያስገቡት ገቢ እየጨመረ በመሄድ ላይ ከነበሩ አገራት ተርታ ትገኝ ነበር።

በአሜሪካ በኩል እንድ አውሮፓውያኑ በ2019 በአጎዋ አማካኝነት ወደ አገሪቱ 8.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን መግባታቸውን የአሜሪካ ፌዴራል መንግሥት የንግድ ጉዳዮች አማካሪ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ይህ ተቋም ባወጣው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በዚያው ዓመት 246 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአጎዋ በኩል ወደ አሜሪካ ልካለች።

ከተላኩት ምርቶች አብዛኛውን የሚሸፍኑት አልባሳት፣ አበባ እና ጫማን የመሳሰሉ ሸቀጦች ናቸው።

በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢኮኖሚ አማካሪ የነበሩት እና አሁን የብሔራዊ ባንክ ገዢ የሆኑት ማሞ ምህረቱ ከሁለት ዓመት በፊት ፎሬን ፖሊስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ለአሜሪካ ገበያ ያቀረበችው ምርት ወደ 150 ሚሊዮን ዶላር ማደጉን አመልክተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከላከችው አጠቃላይ ምርት ግማሹን የሚሸፍን ነው። አጎዋ ይፋ በሆነበት ዓመት ከኢትዮጵያ የተላከው ምርት 28 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የነበረ ሲሆን፣ ከ20 ዓመታት በኋላ የተላከው ምርት ከአምስት እጥፍ የላቀ ሆኖ ነበር።

ሂደቱም ለኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እና ለዜጎች የሥራ ዕድል ምንጭ ሆኖ በመቆየት ለአገሪቱ ዕድገት እስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል።

ማሞ ምህረቱ በጽሁፋቸው በአጎዋ ዕድል አማካኝነት ኢትዮጵያ ከምትልካቸው ምርቶች አልባሳት እና የቆዳ ምርት ኢንዱስትሪዎች ለ200 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን እና ከእነዚህ መካከልም 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በወቅቱም አቶ ማሞ 30 ሺህ ሠራተኞች ያሉትን የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለአብነት በማንሳት 95 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች ሴት መሆናቸው እና የሥራ ልምድ ለሌላቸው ወጣቶች ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ ይህ የኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነት ሲቋርጥ በአብዛኛው ሴቶች የሆኑ በተለያዩ የአምራች ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ ዜጎች ዕጣ ፈንታ ጥይቄ ውስጥ ወድቋል።

አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ማዕቀፉ ደግሞ እንደ ትራንስፖርትና ሆቴል ካሉ አነስተኛ ቢዝነሶች እስከ ጥሬ ዕቃ አቅራቢ ባለው ትስስር ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቅ ዜጋ የገቢ ምንጭ መሆኑ ተገልጾ ነበር።

በሌላ በኩል የቀድሞ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ለአሜሪካ መንግሥት በጻፉት እና በኮሚሽኑ ማኅበራዊ ገጾች በተሠራጨ ግልጽ ደብዳቤ፣ አጎዋ አሜሪካን ጨምሮ ታላላቅ የዓለም ኩባንያዎች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዕድል መስጠቱን አስታውሰዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት 80 በመቶ በአጎዋ በኩል የገበያ መዳረሻቸው አሜሪካ እንደሆነ ያነሱት ኮሚሽነሯ፣ አጎዋ በከተሞች ዙሪያ ለሚኖሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የገቢ ምንጭ ሆኖ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እያገዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከገጠር ወደ ከተማ ሥራ ፍለጋ ለሚፈልሱ በርካታ ሴቶች የእንጀራ ገመድ መሆኑንም በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

ማሞ ምህረቱ በሌላ ቃለ መልልስ አግዋ በኢትዮጵያ ለኢንደስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ምክንያት እንደሆነው ጠቅሰው ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ አገሪቱ አውንታዊ እርምጃን እየወሰደች መሆኑን በመጥቀስ ተስፋቸውን ገልጸው ነበር።

ነገር ግን በምጣኔ ሀብት ቀውስ እየተፈተነች የሚትገኘው ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአጎዋ በኩል የምታገኘውን ጥቅም መልሳ ለማግኘት የአሜሪካ መንግሥት እንዲሟሉ የሚጠብቃቸውን አስገዳጅ ቅደመ ሁኔታን እንዳላሟላች ተነግሯል።

በዚህም የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በአገሪቱ ያለው የሰብአዊ ሁኔታው ሲሻሻል ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ትመለሳለች የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ስጥተዋል።

ይህ የአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል የተግባራዊነት ጊዜን በተመለከተም ከወራት በኋላ የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ተከትሎ በመጪው አውሮፓውያን አዲስ ዓመት የቀጣይነት ሁኔታው ውሳኔ ያገኛል።