ፔጀር

ከ 5 ሰአት በፊት

ማክሰኞ ዕለት ታጣቂው ሄዝቦላህ ለመረጃ ልውውጥ የሚጠቀምባቸው የሬዲዮ መገናኛዎች (ፔጀሮች) በመላው ሊባኖስ በተመሳሳይ ጊዜ ፈንድተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።

በፍንዳታው ቢያንስ 12 ሰዎች ሲገደሉ፤ 2 ሺህ 800 ያህሉ ቆስለዋል። ከፍንዳታዎቹ ሰለባዎች መካከል ብዙዎቹ የደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ነው።

ምንም እንኳን ሄዝቦላህ ለዚህ ጥቃት ባላንጣው እስራኤልን ተጠያቂ ቢያደርግም፣ ጥቃቱ እንዴት እንደተከሰተ ግልጽ አይደለም። የእስራኤል ባለሥልጣናትም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ፔጀር ገመድ አልባ የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያ ሲሆን የጽሑፍ ወይም የድምጽ መልዕክቶችን ተቀብሎ የሚያስተላልፍ ነው።

ፔጀሮች በሆስፒታሎች እና በድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2000ዎቹ ወዲህ ግን እነዚህ መሣሪያዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮች ከተተኩ በኋላ ስለቴክኖሎጂው እምብዛም አይነገርም።

ፔጀሮች እንዴት ሊፈነዱ ቻሉ?

ጥቃቱ እንዴት እንደተፈፀመ ግምቶች ቢኖሩም የሊባኖስ የደኅንነት ምንጭ ለሮይተርስ እንደገለጹት በፈነዱት ፔጀሮች ውስጥ አነስተኛ መጠን ያላቸው ፈንጂዎች እንዲጠመዱ ተደርጓል። ጥቃቶቹም የጽሑፍ መልዕክት በመላክ እንዲፈነዱ በማድረግ የደረሱ ይመስላል።

ታጣቂው ቡድን ከጎልድ አፖሎ 5 ሺህ ፔጀሮችን ማዘዙን የገለጹት ምንጩ፤ በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል ተብሏል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቀድሞ የእንግሊዝ ጦር ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቁሶቹ ምናልባት ከ10 እስከ 20 ግራም የሚመዝኑ ወታደራዊ ፈንጂ የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ፈንጂዎቹ ምንም ጥቅም የማይሰጡ ሐሰተኛ የኤሌክትሮኒክስ ክፍሎች ውስጥ ተደብቀው ፔጀሮቹ ውስጥ ገብተው ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ተናግረዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ይህ በጽሑፍ መልዕክት እንዲፈነዳ ተደርጎ የተሠራ ነው።

የታይዋን ጎልድ አፖሎ ኩባንያ በበኩሉ በጥቃቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌለው በመግለጽ ፔጀሮቹ የተሠሩት በሃንጋሪ ኩባንያ ነው ብሏል።

ፔጀር ምንድን ነው?

እነዚህ የሲጋራ ፓኬት የሚያክሉ አነስተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቀላሉ ለመጠቀም እንዲቻል ብዙ ጊዜ ቀበቶዎች ላይ ይያያዛሉ።

እነዚህ መሳሪያዎች ከፍተኛ ኃይል ካላቸው መረጃ አስተላላፊዎች ጋር በመተሳሰር ይሰራሉ። ሰፊ ቦታ ለመሸፈን እንደ ተንቀሳቃሽ ስልክ ብዙ የሞገድ ማሰራጫ ማማዎችን አይጠቀምም።

ማሰራጫዎቹ ብዙውን ጊዜ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ይቀመጣሉ። ልክ የሬዲዮ ጣቢያዎች እንደሚሠሩት ሁሉ በተወሰነ ድግግሞሽ መልዕክቶችን ይልካሉ።

ፔጀሮች ሁል ጊዜ በመረባቸው ላይ አዲስ መልዕክት ሲላክ ያዳምጣሉ። አብዛኞቹ ፔጀሮች መረጃ ለመቀበል ብቻ ነው የሚያገለግሉት። ከራሳቸው ምንም ዓይነት የመረጃ ምልክት አይለቁም።

የፔጀር ተጠቃሚዎች በጂፒኤስ ወይም በሌላ መንገድ ያሉበት ስፍራ ሊለይ ስለማይችል ከተንቀሳቃሽ ስልኮች ይልቅ ተመራጭ ሆነዋል።

አንድ ፔጀር መልዕክት ሲደርሰው በድምጽ እና በንዝረት ምልክት ይሰጣል። አጭር የጽሑፍ መልዕክት የደረሰው ለመልዕክት አድራሹ መልሶ እንዲደውል ይጠይቃል።

ከፈነዱት መካከል አንዳንዶቹ በታይዋኑ ጎልድ አፖሎ የተሠራውን ራግድ ፔጀር ኤአር924 ይመስላሉ ሲል የቢቢሲው የሳይበር ጋዜጠኛ ጆ ቲዲ ተናግሯል።

ኩባንያው ከጥቃቱ በኋላ ምርቱን ከድረ ገጹ ላይ ያነሳው ይመስላል። የድረ-ገጾችን ገጽታ በመሰብሰብ የሚያከማቸው ዌይባክ ማሽን መስከረም ላይ ምርቱ በድረ ገጹ ላይ እንደነበር እና አቧራ እና ውሃ መከላከያ እንዳለው መግለጹንም አመልክቷል።

የሊቲየም ባትሪውም አንድ ጊዜ ተሞልቶ እስከ 85 ቀናት ይቆያል ይላል።

ኩባንያው ግን መሳሪያው ውስጥ ፈንጂ ለመክተት ተባብሯል ከመባሉ ጋር በተያያዘ ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተናግሯል።

አምቡላንስ
የምስሉ መግለጫ,ማክሰኞ ምሽት ላይ የቤይሩት ጎዳናዎች በአምቡላንስ ተጨናንቀው ታይተዋል።

ሄዝቦላህ ለምን ፔጀር ይጠቀማል?

ሄዝቦላህ በሊባኖስ በጣም ኃያል የሆነውን የታጠቀ ጦር የሚቆጣጠር ሲሆን፣ በፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሺዓ ሙስሊም ድርጅት ነው።

ወታደራዊ ክንፉ በእስራኤል እና በአሜሪካ ወታደሮች ላይ አስከፊ ጥቃቶችን ፈጽሟል።

ቡድኑ በምዕራባውያን መንግሥታት፣ በእስራኤል፣ በባሕረ ሰላጤው አገራት የትብብር ምክር ቤት እና በአረብ ሊግ አሸባሪ ተብሎ ተሰይሟል።

እንደ ቢቢሲ ኒውስ አረብኛ ከሆነ ሄዝቦላህ የእስራኤልን ስለላ እና ክትትል ለማምለጥ ዝቅተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም በመሆኑ ከሞባይል ይልቅ ፔጀሮችን ይመርጣል።

ሄዝቦላህ እና ዘመናዊ ስልኮች

ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት ከሆነ ሄዝቦላህ ከባለፈው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እስራኤል ስልኮቻቸውን እየተከታተለች እንደሆነ ሲጠረጥር ቆይቷል።

የካቲት ወር ላይ ተዋጊዎቹ ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ስልኮቻቸውን እንዳይጠቀሙ ተከልክለዋል።

የሄዝቦላህ ከፍተኛ ፖለቲከኞችም ስልኮቻቸውን ወደ ስብሰባ አዳራሾች ከማምጣት የተቆጠቡ ሲሆን፣ የቡድኑ መሪ ደግሞ ስልኮች ከእስራኤል ሰላዮች የበለጠ አደገኛ ናቸው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው ባደረጉት ንግግር ደጋፊዎቻቸውን ስልኮቻቸውን እንዲሰብሩ፣ እንዲቀብሩ ወይም በብረት ሳጥን ውስጥ ቆልፈው እንዲያስቀምጡ ነግረዋቸዋል።

በዚህም ምክንያት ከስልኮች ይልቅ ፔጀር ለመጠቀም ወሰኑ። አንድ ተንታኝ በበኩላቸው ሄዝቦላህ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀምን በተመለከተ ለደጋፊዎቹ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ይፋዊ ነበር ይላሉ።

የ’ሳይበር ሴኪዩሪቲ ፎር ደሚስ’ ደራሲ ጆሴፍ ስታይንበርግ ለሮይተርስ እንደተናገሩት “ሄዝቦላህ ከሞባይል ስልክ ወደ ፔጀር እየወረደ መሆኑን ለዓለም ይፋ አድርጓል።”

“በዚህም ሄዝቦላህ ለተቃዋሚዎቹ እና ለሌሎች ባላንጣዎቹ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እንደሚፈልግ እየነገረ ነው።”

እንደ ቢቢሲ የደኅንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር ከሆነ እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ በ1996 በአገር ውስጥ የስለላ ድርጅቷ – ሺን ቤት አማካኝነት የሐማስ ቦምብ አምራች የሆነውን ያህያ አያሽ ተንቃሳቃሽ ስልኩን በመጠቀም ገድለዋለች።

ፔጀር ቀደም ሲል በሆስፒታሎች ጥቅም ላይ ይውል ነበር
የምስሉ መግለጫ,ፔጀሮች በሆስፒታሎች እና በድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።

ወደ ሃንጋሪ የሚወስድ ምሥጢራዊ መንገድ

የፈነዱት ፔጀሮች ጉዳይ ከታይዋን እስከ ሃንጋሪ ድረስ ምሥጢራዊ መንገድ መፍጠራቸው እየተነገረ ነው።

ጎልድ አፖሎ የምርት ምልክቱን ለመጠቀም ፈቃድ ባለው እና መቀመጫውን ቡዳፔስት ባደረገ ቢኤሲ በተባለ ኩባንያ መመረታቸውን በቅርቡ አስታውቋል።

በቡዳፔስት የሚገኘው የቢኤሲ ኮንሰልቲንግ አድራሻ በአብዛኛው በመኖሪያ መንደሮች ውስጥ በሚገኝ አንድ ባለቀለም ሕንፃ ላይ እንደሆነ መጠቀሱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የኩባንያው ስም በመስታወት በር ላይ በተለጠፈ ወረቀት ላይ የሰፈረ ነበር። በሕንፃው ውስጥ ያሉና አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ግለሰብ ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ መገኛውን በሕንፃው ላይ አድርጎ ቢመዘገብም በሥፍራው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልነበረውም።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሪስቲያና ባርሶኒ-አርሲዲያኮኖ እንደ ዩኔስኮ ካሉ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ልምድ ሊንክዲን በተሰኘው ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ቢዘረዝሩም ከሮይተርስ ለተላከላቸው ተደጋጋሚ ኢሜይሎች ምላሽ አልሰጡም።

የታይዋን የምጣኔ ሐብት ሚኒስቴር “ወደ ሊባኖስ በቀጥታ የተላከ ነገር ስለመኖሩ የሚያሳይ ማስረጃ የለም” ሲሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።

“ኩባንያው ምርቱ የእነሱ ስለመሆኑ አጠራጣሪ መሆኑን ከመገናኛ ብዙኃን የተነሱትን ፎቶግራፎች ከገመገመ በኋላ አረጋግጧል። ፔጀሮቹ ወደ ውጭ ከተላኩ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል” ብለዋል።

ገመድ አልባ መሳሪያዎች ምን ያህል ደኅንነታቸው የተጠበቁ ናቸው?

በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ገመድ አልባ መሳሪያዎች ደኅንነታቸው የተጠበቁ አይደሉም። “ይህም ትንሽ የሚያስፈራ ነገር ነው” ሲል የቢቢሲ የሳይበር ጉዳዮች ዘጋቢያ ጆ ቲዲ ተናግሯል።

የግብፅ የፀጥታ ባለሙያ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ሞሐመድ ኑር ፍንዳታዎቹ በስለላ ኃይሎች የተቀነባበረ የሳይበር ጥቃት ነው ሲሉ ገልጸውታል። ገመድ አልባ መሳሪያዎችን የሚያመርቱ አገራት ተጠያቂ እንደሆኑ ጠቁመው፤ እንዲህ ያሉ መሣሪያዎች “ፍፁም ደኅንነታቸው የተጠበቁ አይደሉም” ብለዋል።

ደኅንነቱ የተጠበቀ ግንኙነት ለማድረግም “አማራጭ የለም” ብለዋል። እስራኤል ለሄዝቦላህ ያስተላለፈችው መልዕክት ግልፅ ነው። የመደበኛ ስልክ ግንኙነታቸውን ከከለከለች በኋላ ኔትወርካቸው፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው፣ ዘመናዊ (ስማርት) ስልኮቻቸው፣ የሬዲዮ መገናኛዎች (ዎኪ ቶኪዎች) ብቻ ሳይሆን አሁን ደግሞ ፔጀሮች ለእስራኤል ጣልቃ ገብነት ተጋላጭ መሆናቸውን አስመስክረዋል ብለዋል።

ሄዝቦላህ እና የሌባኖስ መንግሥት እስራኤልን ለጥቃቱ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ አድርገዋል። እስራኤል ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

የሄዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስረላ
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስራላህ ባለፈው ወር በቴሌቪዥን ቀርበው ስልክን በተመለከተ ለደጋፊዎቻቸው ማሳሰቢያ ሰጥተው ነበር።

በስልኮች ላይ ሊከሰት ይችላል?

ቀደም ሲል ስልኮችን በመጠቀም ተመሳሳይ የተራቀቁ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቢቢሲ ኒውስ አረብኛ ዘግቧል። ስልኮችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ከደረሱ ጥቃቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ሚከተሉት ናቸው፡

በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል?

በዚህ ዘመቻ እስራኤል በፊልሞች ላይ ብቻ ሊሆኑ የሚመስሉ ትልልቅ ስልታዊ ድሎችን አስመዝግባለች ሲል የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ፕሮግራም አርታኢ ጄሬሚ ቦወን ገልጿል። ይህ ለሄዝቦላህ ውርደት ሲሆን፣ የደኅንነት ስጋቱንም ይጨምራል። ለሞራሉም ቢሆን መጥፎ ይሆናል።

ለእስራኤልም ከባድ የሆነ ስትራቴጂካዊ ውድቀት አለው። ምክንያቱም ፍንዳታው ኃያሉን የሊባኖስ ሚሊሻዎች ቡድንን እና የፖለቲካ እንቅስቃሴውን አንገት ቢያስደፋም ከእንቅስቃሴው አያግደውም።

ከዚህም በተጨማሪም የሄዝቦላህን ጥቃት ለማስቆም እና ለአንድ ዓመት ያህል ከሰሜናዊ ድንበር ላይ የተፈናቀሉትን ከ60 ሺህ በላይ እስራኤላውያን ወደቤታቸው ለመመለስ እስራኤል ያላትን ዓላማ እውን ለማድረግ የተቃረበ አያደርገውም።

ጥቃቱ ቀጠናውን ከጦርነት አንድ ስንዝር ወደ ኋላ ከመጎተት ይልቅ ይበልጥ ለጦርነት ቅርብ ያደርገዋል።