የእስራኤል የጦር አውሮፕላን በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት ለማድረስ ሲያኮበኩብ
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል በጦር አውሮፕላኖች በመታጀብ ነው በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት ያደረሰችው

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤ ሊባኖስ የሚገኙ 100 የሄዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ሌሎች “የሽብር ቦታዎች” እንዲሁም የመሣሪያ ማከማቻዎች መምታቷን አስታወቀች።

የእስራኤል መከላከይ ኃይል እንዳለው ወደ እስራል ለመላክ ዝግጅት ላይ የነበሩ ማስወንጨፊያዎች ናቸው የወደሙት። እስካሁን በጥቃቱ የሞተ ሰው ስለመኖሩ አልተዘገበም።

በመንግሥት የሚተዳደረው የሊባኖሱ ናሽናል ኒውስ ኤጀንሲ ሐሙስ አመሻሹን እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ 52 የአየር ጥቃቶች ማድረጓን አስታውቆ ሊባኖስ ደግሞ ሰሜን እስራኤል የሚገኙ ወታደራዊ ቦታዎችን መትታለች ብሏል።

የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በያዝነው ሳምንት በሀገሪቱ በለተያዩ ሥፍራዎች የደረሱ ፍንዳታዎችን ተከትሎ ጥቃቶቹ “ቀይ መስመር ጥሰዋል” በማለት እስራኤል ጦርነት ማወጇን ተናግረዋል።

እስራኤል ከሰሞኑ በጥቃቅን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ሊባኖስ ውስጥ ለደረሱት ጥቃቶች ኃላፊነት አልወሰደችም።

ማክሰኞ እና ረቡዕ በደረሱት ጥቃቶች ‘ፔጀሮች’ እና ‘ዎኪ ቶኪዎች’ በተመሳሳይ ሰዓት ፈንድተው 37 ሰዎች ሲሞቱ 3 ሺህ ገደማ ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮዋቭ ጋላንት ሀገራቸው በለተይ በሰሜኑ ክፍል በማተኮር “አዲስ የጦርነት ሂደት” መጀመሯን ተናግረዋል።

የሐማስ ታጣቂዎች በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7፤ 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ባደረሱ በማግስቱ ነው ሄዝቦላህ እና እስራኤል ድንበር አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ያደረጉት።

ከዚህ በኋላ በተደረጉ የተለያዩ የተኩስ ልውውጦች በመቶዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ሲገደሉ ድንበር አካባቢ የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳዊያንና እስራኤላዊያን መኖሪያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።

ሄዝቦላህ ጥቃቱን የሚፈፅመው ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ያለውን አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ይገልፃል። በእስራኤል፣ ዩኬ እና ሌሎች ሀገራት ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁት ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች በኢራን ይደገፋሉ።

ሐሙስ አመሻሹን መግለጫ ያወጣው የእስራኤል መከላከያ ኃይል የጦር አውሮፕላኖቹ “100 ገደማ ማስወንጨፊያዎችን እና ሌሎች የሽብር መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን አውድሟል” ይላል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እና ኒው ዮርክ ታይምስ የሊባኖስ ፀጥታ ኃይሎችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት እስራኤል ሐሙስ ዕለት የፈፀመችው ጥቃት ከጋዛው ጦርነት በኋላ እጅግ ከባዱ ነው።

ሐሙስ ንጋት ደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ሁለት ፀረ-ታንክ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ወደ ድንበር ተኩሰዋል።

የእስራል መከላከይ ኃይል ሁለት እስራኤላዊያን መገደላቸውን እንዲሁም አንድ ወታደር ክፉኛ መቁሰሉን አስታውቋል።