ክሬዲት ካርድ

ከ 3 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ባንክ በአራት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሳምንት የወለድ ምጣኔውን ዝቅ አደርጓል። ይህም በአገሪቱ ላሉ ነዋሪዎች ጠቀሜታ ይኖረዋል።

በጉጉት የተጠበቀው እርምጃ በአሜሪካ ለሚኖሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ባሉ ሰዎች የብድር መያዣዎች፣ የክሬዲት ካርድ እና የቁጠባ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሏል።

በርካታ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎችም የአሜሪካ ዜጎች ከባንኮች የሚያገኙትን ብድር መሠረት አድርገው ቤት፣ መኪና እና ሌሎች ውጪያቸውን ይሸፍናሉ። ይህ የወለድ ቅነሳም ተበዳሪዎች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በተወሰነ ደረጃ ዝቅ ያደርግላቸዋል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ቁልፍ የተባለውን የብድር የወለድ መጣኔ በ0.5 በመቶ ቀንሶታል። በዚህም ከ 4.75 እስከ 5 በመቶ ባለው ክልል ውስጥ እንዲሆን ተደርጓል።

ለዚህ ውሳኔ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማነቃቃት የታለመ ነው።

ታዲያ ይህ ለእርስዎ ምን ማለት ይሆን?

ውሳኔው ለቤት፣ ለመኪና ብድር እና ለሌሎች ዕዳዎች ቅነሳ ምን ማለት ነው?

ባንኮች ከመንግሥት ለሚያገኙት ብድር የሚከፍሉት ወለድ፤ ለቤትም እና ለተለያየ ዓይነት ብድር ኩባንያዎች ለሚያስከፍሉት ወለድ መሠረት ይሆናል።

በ2022 መጀመሪያ ላይ ከዜሮ የሚባል አሃዝ ላይ የነበረው የወለድ መጠን ከአንድ ዓመት በላይ 5.3 በመቶ አካባቢ ነበር። ይህም እአአ ከ2001 ወዲህ ከፍተኛ የሚባለው ሆኖ ተመዝግቧል።

የወለድ ቅነሳው ለተበዳሪዎች ትልቅ እፎይታን ያመጣል። አንዳንድ ባንኮች ለቆጣቢዎች የሚሰጡትን የቁጠባ ወለድ እንደሚቀንሱ ልብ ማለት ግን ያስፈልጋል።

እርምጃው ተግባራዊ ሊደረግ ነው ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የቤት ብድር ወለድ ቅናሽ አሳይቷል።

ስለዚህም ቤት እንዲሁም ተሽከርካሪ ለመግዛት እንዲሁም የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያቅዱ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችንም የበለጠ የሚያበረታታ ነው።

ኒው ዮርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረው ተጽዕኖ ምን ሊሆን ይችላል?

ተጽዕኖው በቀጥታ አሜሪካውያን ላይ ያርፋል። ምንዛሪዎቻቸው ከዶላር ጋር የተሳሰሩ ማዕከላዊ ባንኮች እርምጃዎቻቸውን ከዚህ ውሳኔ ጋር ያስተሳስራሉ።

በርካታ የባሕረ ሰላጤ እና እንደ ሆንግ ኮንግ ያሉ አገራት ውሳኔው ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። ስለዚህ በእነዚያ አገራት ውስጥ ባሉ ተበዳሪዎች ላይም እርምጃው የራሱ የሆነ ውጤት ይኖረዋል።

ከዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ሆነው በአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ላይ ኢንቨስት ላደረጉ ወለድ ቅነሳው ጥሩ ዜና ሊሆን ይችላል።

ዝቅተኛ የወለድ ተመን በሁለት ምክንያት የአክሲዮን ዋጋን ከፍ ያደርገዋል።

የመጀመሪያው ኩባንያዎች በአነስተኛ ወለድ ብድር ወስደው ሥራቸውን በማስፋፋት የበለጠ ትርፋማ መሆን ይችላሉ ማለት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ዝቅተኛ ወለድ ሲኖር የገንዘብ ቁጠባ እና አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ብዙም የሚስቡ አይሆኑም። ስለዚህ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን አክሲዮንን ወደመሳሰሉት ዘርፎች ፈሰስ ያደርጋሉ።

መንግሥት የወለድ ምጣኔን ለምን ቀነሰ?

ከሌሎች ማዕከላዊ ባንኮች ጋር ሲነጻጸር የአሜሪካ ግምጃ ቤት የወለድ ምጣኔውን ለመቀነስ ትንሽ ዘግይቷል።

አውሮፓ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኒውዚላንድ እና ካናዳ ተመሳሳይ እርምጃ ከወሰዱ ሰነባብተዋል። በርካታ የታዳጊ አገራት ባንኮችም ይህንኑ መንገድ ተከትለዋል።

ግምጃ ቤቱን በዋጋ ግሽበትን እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ምክንያት ምጣኔውን ይቀንሳል ወይም ይጨምራል።

እአአ በ2022 ግምጃ ቤቱ የወለድ ተመኖችን ያሳደገው በዋጋ ግሽበት ምክንያት ነበር።

የተመኑ መጨመር ብድር ለመበደር አስቸጋሪ በማድረግ ዋጋን የመቀነስ አዝማሚያ ይኖረዋል። በዚህ ምክንያት ሰዎች ከፍጆታ እቃዎች እስከ ቤት እና የንግድ ሸቀጦች ድረስ ያሉትን እንዳይገዙ ተጽዕኖ ያሳድራል።

አነስተኛ ፍላጎት አለ ማለት ደግሞ ምጣኔ ሀብቱ በፍጥነት አያድግም ማለት ነው። ዕድገቱ በጣም ከቀነሰ እና የበለጠ ካሽቆለቆለ የኢኮኖሚ ውድቀት ያስከትላል።

ባለፉት ጊዜያት የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት ከተከታታይ የዋጋ ጭማሪ በኋላ ውድቀትን አስተናግዶ ያውቃል። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል።

የሥራ ቅጥር በከፍተኛ ፍጥነት በመቀነሱ ምክንያት በአገሪቱ ያለው ሥራ አጥነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሊቀመንበር ጄሮም ፖል
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሊቀመንበር ጄሮም ፖል

ለመሆኑ የግምጃ ቤቱ ወለድን የመቀነስ ውሳኔ የዋጋ ንረትን ለማሸነፍ ነው ወይስ ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ስለወደቀ ነው?

ብዙ ተንታኞች የዋጋ ንረትን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ። የዋጋ ግሽበት በነሐሴ ወር 2.5 በመቶ ደርሷል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት የዋጋ ግሽበቱ ወደ መደበኛው እንደሚመለስ እርግጠኞች መሆናቸውን ገልጸው፤ ትኩረታቸው ወደ ሥራ ዕድል ፈጠራ እየዞረ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እዚህ ጋር አገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ትኩረት ያገኛል።

ሪፐብሊካኖች እና ዲሞክራቶች ለሁለት ዓመታት ያህል የአገሪቱን ግምጃ ቤት እንቅስቃሴ በቅርበት ሲከታተሉት ቆይተዋል። የአሁኑ ውሳኔም በሥልጣን ላይ ያለውን ዲሞክራቲክ ፓርቲ የበለጠ ሊረዳ ይችላል።

የግምጃ ቤቱ ሊቀመንበር ጄሮም ፖል በበኩላቸው ባንኩ ውሳኔውን ለማሳለፍ ፖለቲካዊ ሳይሆን ምጣኔ ሀብታዊ መረጃ ላይ ተመርኩዞ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

የወለድ መጠን በ0.5 በመቶ መቀነሱ አግራሞትን ፈጥሯል?

አዎ ይህ ውሳኔው በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ስለነበር መገረምን እና አውንታዊ ስሜትን ፈጥሯል።

ከስብሰባው በፊት ተንታኞች 0.25 በመቶ ወይስ ከፍ ያለ ቅነሳ ይኖራል በሚል ተከፋፍለው ነበር። ባልተለመደ መልኩ ግን 0.5 በመቶ ተቅናሽ ተደርጓል።

ብዙዎች 0.25 በመቶ ሳይቀነስ አይቀርም ብለው ቢገምቱም ግን ያ አልሆነም።

ቢሆንም ግን ይህ የወለድ ቅነሳ ውሳኔ ለተበዳሪዎች መልካም አጋጣሚን በመፍጠር የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይም አውንታው ውጤት ይኖረዋል እየተባለ ነው።