የኢትዮጵያ፣ ቱርክ እና ሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

ከ 5 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አመግባባት በማሸማገል መፍትሄ እንዲገኝ በሁለት ዙር የሞከረችው ቱርክ ጥረቷን ከአገራቱ ጋር በተናጠል ልትቀጥል መሆኑን አስታወቀች።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን እንዳሳወቁት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው ስምምነት ምክንያት የተፈጠረውን የአፍሪካ ቀንድ ውጥረት ለማርገብ ሦስተኛውን ዙር ንግግር ከአገራቱ ባለሥልጣናት ጋር በተናጠል ለማካሄድ አቅዳለች።

ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት ቱርክ በሁለቱ አገራት መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ፣ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ትብብርን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላት ስምምነት ላይ መድረሷ ይታወሳል።

በተመሳሳይም ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም ወታደራዊ ትብብር እንዳላት ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ማብቂያ ላይ ለኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ ጠረፍን፣ በምላሹም ነጻ አገርነቷን ላወጀችው ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ያስገኛል የተባለው ስምምነት አዲስ አበባ ላይ ከተፈረመ በኋላ ሶማሊያ ተቃውሟዋን መግለጿ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ አማካይነት ሉዓላዊነቷን እንደጣሰች የከሰሰችው ሶማሊያ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የምትገኘውን ግብፅን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት ጋር የትብብር ስምምነቶችን በመፈራረም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ስትጥር ቆይታለች።

ቱርክ ደግሞ በአገራቱ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ለማስቻል አንካራ ውስጥ የሁለቱን አገራት ባለሥልጣናት በማነጋገር መፍትሔ እንዲገኝ ስትጥር ቆይታለች። ነገር ግን በንግግሩ ይህ ነው የሚባል ውጤት ላይ ሳይደረስ በመቆየቱ ሌላ ዙር ውይይት እንደሚካሄድ ሲጠበቅ ነበር።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ቀደም ሲል የተደረጉት ሁለቱ ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካይነት የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 7/2017 ዓ.ም. ሦስተኛው ዙር የፊት ለፊት ውይይት እንደሚቀጥል ሲጠበቅ መሰረዙ ተገልጧል።

አገራቱን በማቀራረብ ጥረት እያደረጉ ያሉት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ለአገራቸው የዜና ወኪል አናዱሉ እንደተናገሩት፣ ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በሚኒስትር እና በመሪ ደረጃ ለማቀረራረብ የምታደርገውን ጥረት ትቀጥላለች።

ጨምረውም በአንካራው ንግግር ወቅት ሁለቱ አገራት “በተወሰኑ ነጥቦች መቀራረብ” በመቻላቸው ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊገኝ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ስለዚህም ቀደም ባሉት ንግግሮች ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር እንጂ በቀጥታ ያልተገናኙትን ሁለቱን ወገኖች ለውይይት “በአንድ ላይ እዚህ [ቱርክ] ከማምጣት ይልቅ በተናጠል ግንኙነት በመፍጠር የጋራ አስማሚ ነጥብ ላይ ሲደርሱ ማገናኘት የተሻለ ነው የሚል ዓላማ አለን” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቱርክ በአሸማጋይነት ጉዳዩን በተናጠል ለማካሄድ ወሰነችው ቀደም ሲል ከተካሄዱት የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ሁለት ዙር ንግግሮች ካገኘቻቸው “ልምዶች” በመነሳት መሆኑንም አመልክተዋል።

ሁለተኛው ዙር ውይይት ውጤት ሳያስገኝ የተጠናቀቀው ኢትዮጵያ “የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆኗ ነው” ሲሉ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መናገራቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ እና ሌሎች የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስምምነት የሚደረሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ ስታደርግ ብቻ ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ከተፈረመ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ተግባር ይሸጋገራል የተባለው እና ዝርዝር ይዘቱ ይፋ ያልሆነው ኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ ዘጠነኛ ወሩን ሊይዝ የተቃረበ ሲሆን፣ ስለተግባራዊነቱ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።