የኬጂ ተማሪ በጣቶቿ ቁጥሮችን እየደመረች

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው ዓመት ተቋርጦ የነበረው የቅድመ መደበኛ (ኬጂ) የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት፤ በዚህ ሳምንት በተጀመረው የ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በሳምንት ለአምስት ጊዜ ሊሰጥ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ያዘጋጀው የእንግሊዘኛ ቋንቋ የተማሪዎች መፅሐፍ እና የመምህራን መምሪያ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች መሠራጨቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ርዕሰ መምህራን እና መምህራን ገልጸዋል።

ሕጻናት ወደ አንደኛ ክፍል ከመሸጋገራቸው አስቀድሞ ባለው ቅድመ መደበኛ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የእንግሊዘኛ ትምህርት የተቋረጠው፤ በ2016 ዓ.ም. አዲስ ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) መተገበር በመጀመሩ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የቅድመ መደበኛ ሥርዓተ ትምህርት፤ ከዚህ ቀደም ለ“ኬጂ” ተማሪዎች ትምህርት ሲሰጥ የነበረበትን መንገድ የቀየረ ነው። አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፤ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በሌሎች ደረጃዎች እንደሚደረገው ሒሳብ፣ ሳይንስ፣ ቋንቋ በሚሉ የትምህርት ዓይነቶች እንዳይከፋፈል ያደረገ ነው።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ የቅድመ መደበኛ ደረጃ ተማሪዎች እየተማሩ ያሉት ሁሉንም ትምህርቶች በአንድ ላይ በያዘ አንድ መፅሐፍ ነው። በሁሉም የቅድመ መደበኛ ደረጃዎች ላይ የሚሰጠው ትምህርት በሙሉ በሕጻናቱ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ እንዲሆንም ተደርጎ ነበር።

ይህ ሥርዓተ ትምህርት ሕጻናቱ ከአንደኛ ክፍል በፊት በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዳይማሩ ማድረጉ በወላጆች እና በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።

በዚህ ሳምንት በተጀመረው አዲሱ የትምህርት ዘመን ተቋርጦ የነበረው የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት እንደሚጀመር በአዲስ አበባ የሚገኙ ሦስት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነገገራቸው ትምህርት ቤቶች፤ በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ውስጥ የእንግሊዘኛ ቋንቋም እንዲያካትቱ በከተማዋ ትምህርት ቢሮ እንደተገለጸላቸው አስታውቀዋል። ለዚሁ ትምህርት ተብለው የተዘጋጁ የመማሪያ እና ማስተማሪያ መፅሐፍት “በሶፍት ኮፒ” እንደተላኩላቸው ገልጸዋል።

በከተማዋ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው የደጃዝማች ወንድይራድ ቅድመ መደበኛ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህራንን መመደቡን ምክትል ርዕሰ መምህሩ አቶ ሳምሶን አዳፍሬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ኬጂ ላይ የእንግሊዘኛ መምህራንን መድበናል። መፅሐፉም ‘በሀርድ ኮፒ ገና ነው’ ተብሎ በሶፍት ኮፒ ነው የመጣልን። ክፍለ ጊዜም መድበናል። በአፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ የሚያስተምሩ መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል” ሲሉ የተደረገውን ዝግጅት ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሕጻናቱ የትምህርት ክፍሎች ግድግዳ ላይ ከአማርኛ በተጨማሪ የእንግሊዘኛ ፊደላት እንዲጻፍ መደረጉንም አክለዋል።

እንደ ጀሞ እና መሠረተ እድገት ባሉ ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ተመሳሳይ ዓይነት ዝግጅቶች መደረጋቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።

በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የተዘጋጁት የቅድመ መደበኛ ትምህርት የተማሪዎች መፅሐፍት
የምስሉ መግለጫ,በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የተዘጋጁት የቅድመ መደበኛ ትምህርት የተማሪዎች መፅሐፍት

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በእንግሊኛ ቋንቋ ያዘጋጀው የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መፅሐፍ፤ ሕጻናቱ ካለፈው ዓመት አንስቶ እየተማሩበት ካለው የአማርኛ መፅሐፍ ጋር ተቀራራቢ ይዘት አለው። የእንግሊዘኛው መፅሐፍ እንደ አማርኛው ሁሉ ከፊደላት በተጨማሪ ቁጥሮችን፣ ቅርፆችን፣ ቀለማትን፣ ወራትን፣ የሰውነት ክፍሎችን እና የቤተሰብ አባላትን መጠሪያ ሚያስተምር ነው።

የመጀመሪያ ዓመት የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ፊደላትን እና የተወሰኑ ቃላትን እንዲሁም እስከ ዘጠኝ ድረስ ቁጥሮችን ይማራሉ። ሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች በአብዛኛው የሚማሩት ለስያሜነት የሚውሉ ቃላትን ሲሆን፣ እስከ 15 ድረስ ያሉ ቁጥሮችን አጠራር እና አጻጻፍ እንደሚማሩ በመፅሐፉ ላይ ሰፍሯል።

ሕጻናቱ፤ እስከ 20 ድረስ ያሉ ቁጥሮችን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚማሩት ሦስተኛ ዓመት ላይ ሲደርሱ ነው። በዚህ ዓመት ላይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን መመሥረትን ይለማመዳሉ።

እነዚህን ይዘቶች ያካተተው የቅድመ መደበኛ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት፤ በሳምንቱ ትምህርት በሚሰጥባቸው አምስቱም ቀናት አንድ ጊዜ ቢሰጥ እንደሚመከር ለሁለተኛ ዓመት ትምህርት በተዘጋጀው የመምህራን መምሪያ ላይ ሰፍሯል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ትምህርት ቤቶችም በዚሁ መሠረት ትምህርቱ የሚሰጠው በየቀኑ እንደሆነ ገልጸዋል። በጀሞ ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኙ አንድ ምንጭ፤ በየቀኑ የሚሰጠው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት የቆይታ ጊዜ እንደየ ትምህርት ደረጃው እንደሚለያይ ገልጸዋል።

የአንደኛ ዓመት የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች በአንድ ቀን ውስጥ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚማሩት ከ20 ደቂቃዎች ነው። የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ለ25 ደቂቃ ሲማሩ ሦስተኛ ዓመት የትምህርቱ የቆይታ ጊዜ ወደ 30 ደቂቃ እንደሚያድግ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤት የመምህራን እና የትምህርት ጊዜ ድልድል በማድረግ ዝግጅታቸውን ቢያጠናቅቁም፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የግል ትምህርት ቤቶች እስካሁን ድረስ በይፋ መፅሐፉ እንዳልተላከላቸው ገልጸዋል። የሁለቱም ትምህርት ቤቶች አመራሮች መፅሐፉ የደረሳቸው ይፋዊ ባልሆነ መንገድ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ጣሰው፤ ከዚህ ቀደም በተደረገ ስብሰባ ላይ በዚህ ዓመት የቅድመ መደበኛ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት እንደሚጀመር መገለጹን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይሁንና ለዚሁ ትምህርት የተዘጋጁት መፅሐፍት እስካሁን እንዳልደረሳቸው አመልክተዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።