በሊባኖስ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ አምቡላንሶች በቤይሩት ሲመላለሱ ታይተዋል
የምስሉ መግለጫ,በሊባኖስ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ አምቡላንሶች በቤይሩት ሲመላለሱ ታይተዋል

ከ 2 ሰአት በፊት

በሊባኖሷ መዲና ቤይሩት ነዋሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ሌሎች ጥቃቅን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የሚጠቀሙት በስጋት ተውጠው ነው።

ነገር ግን ከዚህም በላይ አስጊ የሆነ ነገር በቀጣናው ተጋርጧል። ይህ ስጋት በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የለየለት ጦርነት ሊከሰት ይችላል የሚል ነው።

ረቡዕ እና ማክሰኞ ‘ፔጀር’ እና ‘ዎኪ ቶኪ’ ተብለው በሚታወቁት የመገናኛ መሣሪያዎች ላይ በደረሰ የተቀናበረ ፍንዳታ ምክንያት 40 ገደማ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ3000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቶቹ ዒላማ ያደረጉት የሄዝቦላህ አባላትን ነው።

ምንም እንኳ ከጥቃቱ ጀርባ ያለችው እስራኤል ናት ብትባልም አገሪቱ ስለጥቃቶቹ እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጠችም። የእስራኤሉ መከላከይ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ “ጦርነቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ ገብቷል” ብለዋል።

በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የተካረረውን ግጭት ተከትሎ በሊባኖስ ምን ሊከሰት ይችላል?

1. እስራኤል ሄዝቦላህ መዳከሙን ተከትሎ ጥቃት ልትፈፅም ትችላለች

የለየለት ጦርነት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት በአሁኑ ወቅት የሊባኖሱ የጤና ሚኒስትር ፊራስ አቢያድ አገራቸው የከፋ ነገር ሊመጣ ስለሚችል መዘጋጀት እንዳለባት ተናግረዋል።

“ባለፉት ቀናት የተደረጉት ጥቃቶች የእነሱ [የእስራኤሎች] ዓላማ ለግጭቱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ ማበጀት እንዳልሆነ በግልፅ ያሳዩ ናቸው” ይላሉ ሚኒስትሩ።

“እኔ የማውቀው የመንግሥታችን አቋም ግልፅ መሆኑን ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ እያልን ያለነው ሊባኖስ ጦርነት ውስጥ መግባት አትፈልግም ነው።”

ጉምቱ የአረብ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ኢሁድ ያሪ ከሰሞኑ የደረሰው ጥቃት እስራኤል ሄዝቦላህ እና የሚሳዔል ክምችቶቹ ላይ እርምጃ እንድትወስድ “የማይገኝ ዕድል” የፈጠረ ነው ይላሉ።

የሄዝቦላህ የግንኙነት መስመር የተቋረጠ ሲሆን፣ መሬት ላይ ሆነው የሚመሩ አዛዦቹ ደግሞ ቆስለዋል።

ለእስራኤሉ ኤን12 ኒውስ ድረ-ገፅ የፃፉት ያሪ “እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም” ይላሉ።

የቢቢሲው የደኅንነት ተንታኝ ፖል አዳምስ ደግሞ ምንም እንኳ በጋዛ ያለው ጦርነት ባያበቃም የእስራኤል ወታደራዊ ትኩረት ወደ ሰሜናዊው ክፍል ተዛውሯል ይላል።

ነገር ግን እስራኤል አሁን ያለውን አጋጣሚ ተጠቅማ ትገፋበታለች ወይ የሚለው ግልፅ አይደለም። መጠነ ሰፊ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ወይ የሚለውም አነጋጋሪ ነው።

2. ሄዝቦላህ ጥቃት ይፈፅማል፤ እስራኤል ወደ ሊባኖስ ጦሯን ታዘምታለች

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ በዚህ ሳምንት የደረሱትን ጥቃቶች ተከትሎ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ እስራኤል “ቀይ መስመር ጥሳለች” ብለዋል።

ናስራላህ ከሰሞኑ የተከሰተው ለታጣቂው ቡድን ያልተጠበቀ ኪሳራ መሆኑን ቢያምኑም የቡድኑ የዕዝ እና የመገናኛ መንገዶች አሁንም እንደተጠበቁ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። አክለው ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን ለማጣራት ምርመራ እየተደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።

“ጥቃቶቹ የጦር ወንጀል አሊያም ጦርነት ማወጅ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። የፈለጋችሁትን ስም ልትሰጡት ትችላላችሁ። ነገር ግን የጦር ወንጀል አሊያም ጦርነት ማወጅ የሚለው ይመጥነዋል። ጠላታችን ዓላማ ይሄ ነው” ብለዋል።

ናስራላህ ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመፈጸም ቢዝቱም ቡድኑ ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል የሚለውን ከመናገር ተቆጥበዋል። በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ድንበር አካባቢ ያለው የተኩስ ልውውጥ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

መሪው እንደሚሉት በሰሜናዊ እስራኤል በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ሥፍራው እንዲመለሱ አይፈቀድላቸውም።

የቻታም ሐውስ የተባለው የባለሙያዎች ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ አባል የሆኑት አምያድ ኢራቂ እንደሚሉት እስራኤል ከሰሞኑ ያደረሰቻቸው ጥቃቶች “ጠብ ጫሪ ናቸው” ይህ ደግሞ በቀጣናው የተጠናከረ ግጭት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።

“ሄዝቦላህ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው የሚገኘው። ይህን ተከትሎ ነገሮችን ሊያጣድፋቸው ይችላል። ይህ ደግሞ እየተነገረ እንዳለው እስራኤል በሊባኖስ የመሬት ላይ ወረራ እንድትጀምር ሊያደርጋት ይችላል” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

“እስራኤል በጋዛ አቅዳው የነበረው ዋና ዓላማ አልተሳካም” የሚሉት ኢራቂ የእስራኤል መንግሥት በሰሜናዊው ግንባር ከሄዝቦላህ ጋር ያለውን ግጭት በድል መወጣት እንደሚሻ ይተነትናሉ።

የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በሊባኖስ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ንግግር ሲያደርጉ
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በሊባኖስ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ንግግር አድርገዋል

3. ጥቃቶቹ ሄዝቦላህን ሊያዳክሙት ይችላሉ

የቢቢሲ ፐርሺያ የመካከለኛው ምሥራቅ ዘጋቢ ናፊሴህ ኮናቫርድ፤ ሐሰን ናስራላህ ያደረጉትን ንግግር ከቤይሩት ሆና ተከታትላዋለች።

ናፊሴህ እንደምትለው የሰሞኑ ጥቃቶች ቡድኑ ላይ ያደረሱት ኪሳራ ቀላል አይደለም። ናስራላህም በንግግራቸው ቡድኑ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው “ፈተና ገጥሞታል” ብለዋል።

የቡድኑ መሪ ይህን ማመናቸው ሁኔታው ምን ያክል እንደከበዳቸው ያሳያል ትላለች ናፊሴህ። አብዛኞቹ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ወጣቶች ቢሆኑም፤ በጣም ከባድ የሚባል ሥልጠና የወሰዱ የቡድኑ ወሳኝ አባላት ናቸው። እስራኤል እና ሄዝቦላህ አሁንም የተኩስ ልውውጥ ማድረግ ቀጥለዋል።

ምንም እንኳ እስራኤል በተጠረጠረችበት ጥቃት ከፍተኛ ኪሳራ ብታደርስም ይህ ቡድኑ ተጨማሪ ጥቃት ከመፈጸም የሚያግደው አይመስልም ስትል ናፊሴህ ትተነትናለች።

ሄዝቦላህ ሌሎች አጋር ቡድኖች እንዳሉት መዘንጋት የለብንም። እኒህ አጋር ቡድኖች ሄዝቦላህ ብቻ ሳይሆን ሊባኖስ ማለት “ቀይ መስመር ናት” ሲሉ ይደመጣሉ። ኢራን፣ የኢራቅ ሺዓ ሚሊሻ እና የየመን ሁቲ አማፂያን የሄዝቦላህ አጋሮች ናቸው።

በሊባኖስ የደረሱት ጥቃቶች ስኬታማ ቢሆኑም ሄዝቦላህ እንደ አንድ ታጣቂ ቡድኑ በቀጣናው ትልቅ ድጋፍ የሚሰጠው እንደሆነ መረሳት የለበትም።

ከፍንዳታዎቹ በኋላ የቤይሩት ነዋሪዎች ደም ሲለግሱ
የምስሉ መግለጫ,ከፍንዳታዎቹ በኋላ የቤይሩት ነዋሪዎች ደም ሲለግሱ ነበር

4. የፔጀር ጥቃቶቹ የታሰበባቸው ናቸው?

የቢቢሲው የደኅንነት ተንታኝ ጎርደን ኮሬራ እንደሚለው የእስራኤል የስለላ መሥሪያ ቤት ሞሳድ ምናልባት የለየለት ጦርነት ቢነሳ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ለመጠቀም ዝግጅት አድርጓል የሚሉ ፅንሰ-ሐሳቦች ይሰማሉ።

ነገር ግን ሄዝቦላህ ፔጀሮቹን መጠራጠር ሲጀምር ሞሳድ “እንዲሁ ከሚባክን እንጠቀመው” በሚል ባለፈው ማክሰኞ እንዳፈነዳቸው፤ ረቡዕ ደግሞ ፍንዳታዎቹ በዎኪ ቶኪ የግንኙነት ሬዲዎች ላይ መደገሙን ይነገራል።

ይህ ፅንሰ-ሐሳብ እውነት ከሆነ እስራኤል መጠነ ሰፊ የሚባል ጥቃት ለመክፈት ዕቅድ አላት ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው ይላል ጎርደን።

አምያድ ኢራቂ፤ ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎችን እንደ ጥቃቅን ፈንጂዎች መጠቀም የሚለው ሐሳብ አዲስ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን መጠቀም ለምን አስፈለገ የሚለው ጉዳይ አጣራጣሪ ነው ይላሉ።

ተንታኙ እንደሚሉት “አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ሄዝቦላህ እነዚህ ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎች ላይ ያለው እምነት መሳሳት ጀምሮ ነበር” የሚል ዘገባ አስነብበዋል።

አንዳንዶች ደግሞ እስራኤል በጋዛ ያላትን ‘ኦፕሬሽን’ አጠናቃ አሁን ፊቷን ወደ ሰሜናዊው ድንበር ወደ ሊባኖስ ማድረግ ጀምራለች ይላሉ።