September 20, 2024 

(መሠረት ሚድያ)- በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸውን ወይም የንግድ ሱቆቻቸውን ለማደስ ፈልገው የግንባታ ፈቃድ ሲጠይቁ እስከ 100 ሺህ ብር ጉቦ አምጡ እየተባሉ እንደሆነ ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

“እኔ ለምሳሌ ሰሚት ፍየል ቤት አካባቢ ነዋሪ ነኝ፣ የንግድ ቤቴን ትንሽ ለማደስ ፈቃድ ጠይቄ 80 ሺህ ብር ስጠን ተብያለሁ” ያሉ አንድ ጥቆማ ሰጪ ይህም ያለምንም ሀፍረት በግልፅ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የክፍለ ከተማው ወረዳ 10 ነዋሪ ደግሞ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ብር ቢከፈል እንኳን ደንቦች ከ3 እስከ 4 ሆነው በቡድን በመምጣት ለአንድ ሰው እስከ 10 ሺህ ብር አምጡ እንደሚሉ በምሬት ተናግረዋል።

“መስራትም፣ አለመስራትም አማራጭ እየሆነ እየሆነ አይደለም። የህዝብ አገልጋይ ተብለው የተቀመጡ ሰዎች ይህን ያህል ገንዘብ ከጉቦ ተቀብለው ካለ ምንም ሀፍረት በቀጥታ ወደ ባንክ አካውንታቸው ሲያስገቡ ማየት ያሳዝናል” ብለው አስተያየታቸውን የሰጡን ደግሞ የሰሚት ኖክ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ነዋሪ ናቸው።