September 20, 2024 

ከሳምንት በፊት በአርሲ ዞን ሲርካ ወረዳ 38 ሰዎች በጉዞ ላይ እያሉ በሸኔ ታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡

ታጣቂዎቹ ታጋቾችን ለመልቀቅ ከ250ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ብር ድረስ የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎም አንዳንድ የታጋች ቤተሰቦች ገንዘቡን ለመክፈል ወደ ተባሉበት ቦታ ማቅናታቸውን የሚገልጹት የመረጃ ምንጮች ገንዘብ አቀባዮቹ በቦታው ሲደርሱ ግን እራሳቸው በታጣቂዎቹ መታገታቸውን ነው የገለጹት ፡፡

‹‹ካሉበት ቦታ ሆነው ስልክ ደውለው እኛም ታግተናል›› አሉን የሚሉት አንድ ምንጭ የታገቱትን አስፈትተው ይመጣሉ ብለን ተስፋ ስናደርግ እነሱም መያዛቸው ሌላ ጭንቀት ፈጥሮብናል ይላሉ፡፡

ታጋቾችን ለማስለቅ የሚያስችል ገንዘብ አሁን ላይ እንደሌላቸው የሚገልጹት እነዚህ የታጋች ቤተሰቦች የቀደሙትንም ለማስፈታት በገበያ ቦታ፣ በእድርና በመሰል ማህበራዊ አደረጃጀቶች በኩል ጥረት ተደርጎ ገንዘቡ እንደተሰበሰበ ገልጸዋል፡፡

መንቀሳቀስና መስራት ውድ እየሆነ መጥቷል፤ መንግስትም የህግ የበላይነት የሚባለውን መሰረታዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል በማለትም አካባቢው ላይ የሚታይ ስጋት አሁንም እንዳለ ነው ያስታወቁት፡፡

በሌላ በኩል ታግተው ከነበሩ 38 ሰዎች ውስጥ 5 ያህል ታጋቾች ማምለጣቸውንም እነዚህ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ምንጮች አሁን ላይ ያመለጡት ታጋቾች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ግን ተጨማሪ መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የሸኔ ታጣቂ ቡድኖቹ በአርሲ ዞን ሲርካ ወረዳ ከጎቤሳ ከተማ ወደ ተለያዩ ከተሞች በመጓዝ ላይ የነበሩ አጠቃላይ 8 የህዝብ ማመላለሻዎችን ጋለማ በሚባል ጫካ ውስጥ በማስቆም 38 ሰዎችን በመምረጥ ማገታቸው የሚታወስ ነው።