September 20, 2024 – Konjit Sitotaw 

ሊባኖስ ዉስጥ ፔጀርስ በተባለዉ ሞባይል መሠል የመገናኛ መሣሪያዎች ዉስጥ የተጠመዱ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ PETN የተባለ ከፍተኛ ፈንጂ መስሪያ የተሰሩ መሆናቸውን አንድ ለሙያው ቅርበት ያለው ሰው ለሮይተርስ ተናገረ።

ይህ አደገኛ ፈንጂ ከባትሪው ጋር እንዲዋሃድ የማድረጉ ተግባር በቀላሉ እንዳይታወቁ በሚያስችል መልኩ እንደተሰራም ባለሙያው አክሏል።

ሊባኖስ ዉስጥ ፔጀርስ በተባለዉ ሞባይል መሠል የመገናኛ መሣሪያዎች ዉስጥ የተጠመዱ ቦምቦች ባለፈዉ ማክሰኞና ሮብ ፈንድተዉ በትንሹ 32 ሰዎች ተገድለዋል።ከ3000 በላይ ቆስለዋል።

አብዛኞቹ ሟችና ቁስለኞች የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የሒዝቡላሕ ተዋጊዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ናቸዉ።በፍንዳታዉ ከተገደሉት አንዱ የሊባኖስ የምክር ቤት እንደራሴ ልጅ ሲሆን፣ ከቆሰሉት ደግሞ በሊባኖስ የኢራን አምባሳደር ይገኙበታል።

ሒዝቡላሕ፣ የሊባኖስ መንግሥትና ኢራን ለፍንዳታዉ እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል።አንድ የሊባኖስ የሥለላ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዛሬ እንዳሉት ሒዝቦላሕ ከወጪ በገዛቸዉ 5000 ፔጄሮች ዉስጥ የእስራኤል የሥለላ ድርጅት ሞሳድ ከአንድ ወር በፊት ፈንጂ አጭቆባቸዋል።

ፔጀሮቹ ከታይዋን በቡልጋሪያ በኩል ሊባኖስ መግባታቸዉ ተዘግቧል።ፔጀሮቹን ሠርቷል የተባለዉ ጎልድ አፖሎ የተባለዉ የታይዋን ኩባንያ ግን ፔጀሮቹ «የኛ ምርቶች ዓይደሉም» ይላል።

ዘግየት ብለው የወጡ መረጃዎች ደግሞ ባትሪዎቹ ICOM በተባለው የጃፓን ኩባንያ እንደተሰሩ ያመላክታሉ።

ይሁንና የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ድርጅታቸው እነዚህ ለሬድዮ መገናኛ የሚውሉ ባትሪዎች መስራት ካቆመ አስርት ዓመታት እንዳለፉት ተናግሯል ስል ሮይተርስ ዘግቧል።