የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ

ከ 8 ሰአት በፊት

የጦር መሳሪያዎች በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ በኩል ወደ ፑንትላንድ እየገባ ነው ሲል የሶማሊያ መንግሥት ከሰሰ።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ዛሬ [አርብ] መስከረም 10/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የተፈጸመ ነው ያለውን ድርጊት በብርቱ አውግዟል።

ሶማሊያ ይህ ዓይነቱ ያልተገለጸ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ በኢትዮጵያ ድንበር በኩል የግዛቴ አካል ናት ወደምትላት ፑንትላንድ ክልል እየገባ ስለሆነ ድርጊቱ እንዲቆም አሳስባለሁ ብላለች።

ቢቢሲ ከሶማሊያ መንግሥት በኩል የተሰነዘረውን ክስ በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት ምላሽን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

የፑንትላንድ ማስታወቂያ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ገባ ስለተባለው የጦር መሳሪያን በተመለከተ ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሲዘዋወር ከማየታቸው ውጪ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ አለመግባቱን ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ይህ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ከመሆኑም ባሻገር ቀጠናውን ወደ ትርምስ እንዲያመራ መንገድ የሚከፍት ሊሆን ይችላል ብሏል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር በመግለጫው አሁን ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ ግዛት የጦር መሳሪያ የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች “ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወይንም ይሁንታ” መላኩን ጠቅሶ ይህ ግልጽ የሉዓላዊነት ጥሰት ነው ሲል ገልጾታል።

ይህም በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ ያለው ጉዳይ መሆኑን መግለጫው የጠቀሰ ቢሆንም በይፋ የቀረበ ማስረጃ የለም።

ይህ በኢትዮጵያ በኩል ተፈጽሟል የተባለው ድርጊት በሶማሊያን የግዛት አንድነት የተፈጸመ ጥሰት ማሳያ ነው በማለት፣ ክስተቱ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሕግ እና ለቀጣናው መረጋጋት ያላት ፈቃደኝነት እንደሚያሳስበው መግለጫው ገልጿል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ተግባሩን በፍጥነት እንዲያቆምም ጠይቋል።

በተጨማሪም እንዲህ ያለው የጦር መሳሪያ ወደ ሶማሊያ የማስገባት ድርጊት በኢትዮጵያ ሲፈጸም የመጀመርያው አይደለም ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ወደ ጋልሙደግ እና ባይዶዋ ክልል በአየር ጭምር የጦር መሳሪያ ተሸጋግሯል ይላል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቀረበው ክስ በሰጠው ምላሽ ወደ ጋልሙዱግ ግዛት ገብቷል ከተባለው የጦር መሳሪያ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ በመግለጽ አስተባብሏል።

በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ የወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ከዚህ ድርጊቷ እንድትታቀብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እንዲያወግዝ ይጠይቃል።

የሶማሊያ መንግሥት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ ግዛት የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሶማሊያ የጦር መሳሪያ አስገብቷል በማለት ቢከስም የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በወቅቱ የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ በድብቅ የገባ ጦር መሳሪያን የሶማሊያ የደኅንነት ኃይሎች ይዘው ሲጓጉዙ ነበር ያለ ሲሆን፣ የጋልሙዱግ ግዛት የደኅንነት ምክትል ኃላፊ አሊ ባሺ አብዱላሂ ጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የሶማሊያ መረጃ እና የደኅንነት ኤጀንሲ አባላት ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ይህ አወዛጋቢ የጦር መሳሪያ በጋልሙዱግ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ሚሊሻዎች ጥቃት ተፈጽሞበት በነዋሪዎች ጭምር መዘረፉ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ነግሷል።

ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ-ሰላጤ የባሕር ኃይል ሰፈር እንድትገነባ እና የባሕር በር እንዲኖራት የሚያስችል ነው የተባለው የመግባቢያ ሰነድ፣ በምትኩ ኢትዮጵያ የሶማሊላንድን አገርነት በይፋ እውቅና እንደምትሰጥ ተነግሯል።

ሶማሊላንድን የራሷ ግዛት አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ በዚህ ስምምነት ደስተኛ አለመሆኗን በተደጋጋሚ የገለፀች ሲሆን ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች።

ከዚህ በኋላም ሁለት የግብፅ አውሮፕላኖች የጦር ሠራዊት እና ወታደራዊ ቁሳቀሶች ጭነው የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ማረፋቸው ለውጥረቱ አዲስ መልክ ሰጥቶታል።

ኢትዮጵያ የግብፅ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ገብተው ማረፋቸውን ተከትሎ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ኃይሎችን እያስጠለለች ነው በማለት ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የቱርክ መንግሥት እየሰራ ይገኛል።