የ“አልፋ ሚዲያ” መስራች የሆነው በቃሉ አላምረው እና የ“የኢትዮ ኒውስ” መስራቹ በላይ ማናዬ
የምስሉ መግለጫ,የ“አልፋ ሚዲያ” መስራች የሆነው በቃሉ አላምረው እና የ“የኢትዮ ኒውስ” መስራቹ በላይ ማናዬ

ከ 8 ሰአት በፊት

የፈረንጆቹ 2018 ከ20 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ አንድም ጋዜጠኛ እስር ላይ ያልተገኘበት ዓመት ነበር። በጊዜው ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር ላይ 40 ደረጃዎችን አሻሽላ 110ኛ ሁናም ነበር።

ይህን ምክንያት በማድረግም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያዘጋጀው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በአዲስ አበባ ተከብሮ ነበር።

ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ሙገሳን ካገኘች አምስት ዓመታት በኋላ 54 ጋዜጠኞች አገር ጥለው መሰደዳቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ተቋም ሲፒጄ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ከዚህ ሪፖርት መውጣት ሦስት ወራት በኋላ ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞችም እንዲሁ አገር ጥለው መሰደዳቸውን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስታውቀዋል።

አገር ጥለው የተሰደዱት ጋዜጠኞች የ“አልፋ ሚዲያ” መስራች የሆነው በቃሉ አላምረው እና የ“የኢትዮ ኒውስ” መስራቹ በላይ ማናዬ ናቸው።

ጋዜጠኞቹ ከአገር የተሰደዱት ወደ ሙያቸው “መመለስ ስላልቻሉ” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቃሉ እና በላይ ከአገር ለመውጣት ለተከታታይ 11 ቀናት መጓዝ ነበረባቸው።

“በጣም አስቸጋሪ የሚባለውን መንገድ ተከትለን በእግር፣ በመኪና እና በሞተር ሳይክል ነው የወጣነው። የነበሩብን [የጉዞ] እገዳዎች እና ክትትሎች መደበኛውን የጉዞ መንገድ እንድንጠቀም አላስቻለንም” ሲል በቃሉ ጉዞውን ያስታውሳል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለወራት በእስር ካሳለፉ በኋላ የተፈቱት ባለፈው ዓመት ሰኔ መጀመሪያ ነበር። በአዋሽ አርባ የነበራቸውን ቆይታ፤ “በጣም አስቸጋሪ” ሲሉ ይገልጹታል።

ነገር ግን ሁለቱም ጋዜጠኞች ወደ አዋሽ አርባ ከመዘዋወራችው በፊት ለሳምንታት ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ታስረው ነበር።

“ለቤተሰቦቼ አይመለስም አታልቅሱ አሏቸው”

ሐምሌ 30፤ 2015 ዓ.ም. ኒው ጄነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እያስመረቀ ነበር። ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው። በቃሉ በ“Global study and international relations” የማስትርስ ዲግሪውን ተቀብሏል።

ከምርቃት ስነ ስርዓቱ በኋላ በቃሉ ወደ ቤቱ የገባው ብቻውን አልነበረም። የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ አባላት ቤቱ እስከሚገባ ሲከታተሉት እንደነበር ያስታውሳል።

በቃሉ “ከምርቃት ስነ ስርዓት በኋላ ተከታትለው መጥተው ቤት ስገባ ነው የያዙኝ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። “በሚይዙኝ ሰዓት ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስድብ፣ ቁጣ እና ማንጓጠጥ ነበር” የሚለው በቃሉ፤ “ለቤተሰቦቼ አይመለሰም አታልቅሱ ነው ያሏቸው” ይላል።

የማስተርስ ዲግሪውን ደስታ በቅጡ ሳያከበር የታሰረው በቃሉ የሚቀጥሉትን ሁለት ሳምንታት ያሳለፈው በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ነበር። ከዛ በኋላ ነሐሴ 15፤ 2015 ዓ.ም. አዋሽ አርባ ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ተዘዋውሯል።

በቃሉ ጋር አብሮ ከአገር የተሰደደው ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በበኩሉ ከአራት ወራት በኋላ ከአራት ኪሎ ወደ መኖሪያ ቤት ሲጓዝ ነበር በጸጥታ ኃይሎች የተያዘው።

ምሽት 12:30 ተኩል አካባቢ በፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አባላት ከተያዘ በኋላ “በቀጥታ ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ነው የተወሰድኩት” ይላል።

በላይ በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሦስት ሳምንታትን አሳልፏል። “አንድ ጊዜ ብቻ የቃል መቀበያ የሚል ጽሁፍ ያለበት ቢሮ ጠርተው አነጋግረውኛል” የሚለው በላይ፤ “በወቅቱ ሚዲያን በመጠቀም ለፋኖ ኃይሎች ድምጽ ትሆናለህ፤ አሁን ያለውን ሁኔታ ታባብሳለህ የሚል ነገር አነሱ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በላይ ለ26 ቀናት በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከታሰረ በኋላ ወደ አዋሽ አርባ ተዘዋውሯል።

“በለሊት ነው በር በኃይል ተደብድቦ፣ ከእንቅልፋችን እንድንነሳ ተደርጎ፣ በቀጥታ ወደ አዋሽ እንድንወሰድ የተደረገው፤ ወዴት እንደምንወሰድም አናውቅም ነበር፤ መንገዱን ይዘው መሄድ ሲጀምሩ የራሳችንን ግምት እየሰጠን እስከ መጨረሻው ድረስ የት እንደምንደርስ አናውቅም” ሲል በጊዜው የነበረውን ስሜት ለቢቢሲ አጋርቷል።

“የማስበው መቼ እንደምሞት ነበር”

አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከመገናኛ ብዙኃን እና ከፖለቲከኞች እስር ጋር በተያያዘ ስሙ በበጎ አይነሳም።

ለወራት በካምፑ ታስረው የቆዩት በላይ እና በቃሉ ያሳለፉትን ጊዜ “አስቸጋሪ” ሲሉ ይገልጹታል።

በላይ [አዋሽ አርባ ስንደርስ] በከፍተኛ የአካል መጎሳቆል ውስጥ የነበሩ፣ ቀደም ሲል አዋሽ የቆዩ ታሳሪዎችን አገኘናቸው” የሚለው በላይ፤ “አዋሽ እንደ ደረስን በጣም የተደበላለቀ ስሜት ነው ይሰማን የነበረው” ሲል ስሜቱን ያስታውሳል።

ካምፑ በጫካ የተከበበ እና የአዋሽ ወንዝ የሚያጎራብተው መሆኑን ጋዜጠኞቹ ይገልጻሉ። በተጨማሪም “ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ነው ያለው እኛ የተያዝንበት ቤት፤ ካምፑ ውስጥ ሰልጣኝ ወታደሮች አሉ። እንደገና ደግሞ እኛ ያለንበትን ቤት ብቻ የሚጠብቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት አሉ” ሲል በላይ ተናግሯል።

በላይ ወደ አዋሽ ከተወሰደ በኋላ ያለበትን ቦታ ለቤተሰቦቹ ለማሳወቅ ሁለት ሳምንት መጠበቅ ነበረበት። በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በቆየባቸው ስድስት ወራት አብረውት ከታሰሩት ውጭ ከማንም ጋር አይገናኝም ነበር።

“ከውጭ ማንም ሰው አይገባም፤ ጠበቃ የለም። ቤተሰብ የለም። ዘመድ የለም። መረጃ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ አዳዲስ ሰዎች ሲመጡ ነው ምን እየተከናወነ ነው ብለን የምንጠይቀው” ሲል ሁኔታውን ያስታውሳል።

በላይ በካምፑ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “ከወታደራዊ ሰልጣኞች የተለያየ ዛቻ ይደርስብን ነበር። እንደ ምርኮኛ ነው የሚቆጥሩን። ከአዲስ አበባ በሲቪል ስራ ላይ የቆየን እና ባለሙያዎች እንደሆንን አይደለም የሚረዱት። ወታደር ሆነን [የጦር] ሜዳ ላይ በምርኮ እንደተያዝን ነው የሚያስቡት። ይሄ ሁሉ አስጨናቂ ያደርገው ነበር ቆይታውን” ይላል።

ጋዜጠኛ በቃሉም “የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጅምላ ይመጣሉ፤ ይሰድቡናል፤ እንደምርኮኛ ነው የምንቆጠረው፤ ስንፈልጋቸው ስንፈልጋቸው አዋሽ አርባ አገኘናቸው እያሉ በየቀኑ ይጨፍሩብን ነበር” ሲል የበላይን ሃሳብ ይጋራል።

“ጋዜጠኛ የሆንነውን እንደ ከፍተኛ ጠላት ነው የሚቆጥሩን” የሚለው በቃሉ፤ “እንደሚገድሉን ነበር የሚነግሩን። ፍርድ ቤት እንደማንቀርብ፣ ክስም እንደማይመሰረትብን ግን ሌላ እርምጃ እንደሚወሰድብን ነው ይነግሩን የነበረው” ይላል።

“እኔ እዚህ በረሃ ነው የምሞተው፣ በቃ እንደምሞት እርግጠኛ ነበርኩ” የሚለው በቃሉ፤ “ሞትን ነበር የማስበው። በአቅራቢያችን ያለው ነገር በሙሉ የሚያሳስበን ሞትን ነበር። እኔ የማስበው መቼ እንደምሞት ነው” ሲል በጊዜው ያስብ የነበረውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጋዜጠኛ በላይም በተመሳሳይ “ሁል ጊዜ በሕይወታችን እየሰጋን ነው የቆየነው። በእያንዳንዱ ቀን በሕይወት የመቆየት [እና] ያለመቆየት ስጋት ውስጥ ሆነን ነበር የምናሳልፈው” ይላል።

በላይ እና በቃሉ ለወራት በአዕምሯቸው ይመላለስ የነበረው ስጋት ድንገት ተገፈፈ።

ከወራት እስር በኋላ ተለቀቁ። ነገር ግን ከመፈታታቸው አንድ ቀን በፊት ሦስት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት እና አንድ የፌደራል ፖሊስ አባላት በተናጥል እንዳዳነጋገሯቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጸጥታ አባላቱ፤ “አንደኛ ስልክ እና አድራሻ መቀየር አትችሉም። ወጥታችሁ ለመገናኛ ብዙኃን የእስር ቆይታችሁን እና አገራዊ ሁኔታን በተመለከተ ምንም አይነት ቃለ ምልልስ መስጠት አትችሉም” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።