የሶማሊያ እና የቱርክ ባንዲራ

ከ 4 ሰአት በፊት

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት ነግሷል።

በዚህ ውጥረት መካከል ዋና አሸማጋይ ሆና ብቅ ያለችው ቱርክ ናት።

ቱርክ እና ሶማሊያ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው።

ቱርክ ከአስር ዓመታት በላይ ሶማሊያ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን እንድታረጋግጥ እንዲሁም ሽብርተኝነትን እንድትዋጋ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ትገልጻለች።

እንደ ቱርክ መንግሥት ከሆነ እአአ 2009 ጀምሮ የቱርክ ጦር በሶማሊያ የባሕር ላይ ውንብድና፣ ዘረፋ እና የባሕር ላይ ሽብር ለመከላከል የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረቶች ሲደግፍ ቆይቷል።

በየካቲት ወር ደግሞ ቱርክ ወታደሮቿ በሶማሊያ ያላቸውን ቆይታ በሁለት ዓመት ለማራዘም ወስናለች።

ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት ቱርክ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ትብብርን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላት ስምምነት ላይ መድረሷም ይታወሳል።

በተመሳሳይም ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም ወታደራዊ ትብብር እንዳላት ይታወቃል።

ቱርክ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ማብቂያ ላይ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለመፍታትም በሁለት ዙር ስታደርግ የቆየችውን ጥረት ከአገራቱ ጋር በተናጠል ልታደርግ መሆኑን አስታውቃለች።

በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ቁርሾ የተፈጠረው ለኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ ጠረፍን፣ በምላሹም ነጻ አገርነቷን ላወጀችው ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ያስገኛል የተባለው ስምምነት ተከትሎ ነበር።ይህም በቀጠናው ውጥረትን አስከትሏል።

የቱርክ እና የሶማሊያ ወዳጅነት የሚጀምረው እኤአ በ2011 መቶ ሺህዎችን የቀጠፈው አስከፊ ረሃብ በአገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ ነው።

በወቅቱ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች በደኅንነት ስጋት የተነሳ አገሪቱን ለቅቀው ወጥተው ነበር።

ሌሎች በአገሪቱ የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ እጃቸውን በሰበሰቡበት ወቅት ቱርክ እግሯን ለማስገባት አላመነታችም።

በወቅቱ ሶማሊያውያን መካከል የተገኙት ፕሬዝዳንት ታይብ ኤርዶዋንም፣ አገሪቱን የጎበኙ የመጀመርያው አፍሪካዊ ያልሆኑ መሪ ሆነዋል።

ይህንን የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ተከትሎም ሁለቱ አገራት በሰብዓዊ እርዳታ እና ሌሎች ግንኙነቶች ያላቸውን ወዳጅነት ጀመሩ።

በ2012 ደግሞ የቱርክ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ በረራ ማድረግ የጀመረ ሲሆን ይህም ሶማሊያን ከቀሪው ዓለም ጋር ማገናኛት የቻለ እርምጃ ነበር።

ቱርክ የሶማሊያ ምጣኔ ኃብት በንግድ እና ቱሪዝም ረገድ እንዲነቃቃ የበኩሏን ጥረት ማድረግ ቀጠለች።

የቱርክ ኩባንያዎችም በሞቃዲሾ የሚገኙ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን፣ አውሮፕላን ማረፍያ እና ወደብን ማስተዳደር በመጀመር የሁለቱን አገራት ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ከፍ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ አገራቸው ሶማሊያን መልሶ መገንባት ላይ ያላትን ሚና አጠናክረዋል።

ቱርክ እአአ በ2017 ከአገር ውጪ ትልቁን የራሷን ወታደራዊ ጦር ሰፈር በሶማሊያ ገንብታለች።

ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የሶማሊያን ሠራዊት እና ፖሊስ አባላት ታሰለጥናለች።

ቱርክ በሶማሊያ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ከመገንባቷ ባሻገር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሶማሊያ ተማሪዎች በቱርክ የትምህርት ዕድል እያገኙ ይገኛሉ።

በአንካራ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤለም አይሪስ (ዶ/ር) ይህንን የሶማሊያ እና የቱርክ ወዳጅነት “የተሟላ የሰላም ግንባታ መንገድ ” ሲሉ ያንቆለጳጵሱታል።

ፕሮፌሰሯ አክለውም ቱርክ በሶማሊያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቁልፍ አጋር ለመሆን ራሷን በፍጥነት ማቅረቧን ይገልጻሉ።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል አገር የሆነችው ቱርክ በአሁን ሰዓት በሶማሊያ ምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካ እና ሰብዓዊ እርዳታ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ንቁ ተሳታፊ ነች።

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ቱርክ የሶማሊያን የባሕር ኃይል በማሠልጠን ለማስታጠቅ የሚያስችላትን እንዲሁም የሶማሊያን የባሕር ጠረፍን ለመጠበቅም የራሷን የባሕር ኃይል በአካባቢው እንድትሰማራ የሚፈቅድ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የባሕር ኃይል
የምስሉ መግለጫ,ሐምሌ ወር ላይ የቱርክ ፓርላማ የአገሪቱ ባሕር ኃይል በሶማሊያ እንዲሰማራ ፈቅዷል።

ሶማሊያ በአፍሪካ ረዥም የባህር ዳርቻ ያላት እና የዓለም አቀፉ የባሕር ንግድ ትራንስፖርት መተላለፍያ ናት።

ለቱርክ ይህንን ወሳኝ የሆነ የንግድ መስመርን እንዲሁም የሶማሊያን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ዋነኛ ተግባር ነው።

ቱርክ የንግድ፣ የሰብዓዊ እርዳታ እና የምጣኔ ኃብት አጋር የሆነቻት ሶማሊያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ደጆችን ስታንኳኳ ቱርክ ቋሚ አጋሯ መሆኗን በማንሳት ትጠቀምበታለች።

“ይህ በበርካታ የሶማሊያ ባለስልጣናት ይታያል፤ አስተማማኝ አጋራችን እና የኔቶ አባል አገር ናት ሲሉ ይደመጣሉ።” ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰሯ ኤለም አይሪስ (ዶ/ር) ።

ቱርክ ሶማሊያ የተገኘችው ማንም ባልነበረበት ወቅት መሆኑ ሌላ የሚሰጣት ጥቅም ነው ይላሉ የዩኒቨርስቲ መምህሯ።

“ ይህ ሶማሊያ የእኛን ድጋፍ ትፈልጋለች የሚል ግልጽ መልዕክት ነው።”

ኃላፊነት እንደሚሰማው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የድርሻችንን መወጣት አለብን የሚለው የቱርክ መንግሥት ስሜት መሆኑን ፕሮፌሰሯ አክለው ተናግረዋል።

ሶማሊያ እና ጂቡቱ በቀይ ባሕር ላይ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ እንደሚገኙ ያስታወሱት ፕሮፌሰሯ፣ በዚህም ቱርክ በቀጠናው ጠቃሚ የንግድ አጋር ማፍራት መቻሏን ያሰምሩበታል።

ለዚህም እንደማስረጃ የሚጠቅሱት ቱርክ እና ሶማሊያ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ፍለጋ ስምምነት መፈራረማቸውን ነው።

በርካታ አገራት ይህንን ስምምነት ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ለመፈራረም ይፈልጋሉ የሚሉት ፕሮፌሰሯ ኤለም አይሪስ (ዶ/ር)፣ ይህንን ግን በቀዳሚነት ያሳካችው ቱርክ መሆኗን ገልጸዋል።

ወደ ሶማሊያ እግራቸውን ለማስገባት ከሞከሩ አገራት መካከል የምትጠቀሰው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ናት።

በአፍሪካ ቀንድ ወደቦችን በማስተዳደር የምትታወቀው ዩኤኢ አፍሪካ በቅርቧ የምትገኝ አህጉር ናት።

እንደ ፕሮፌሰሯ ገለጻ ከሆነ ዩኤኢ በምጣኔ ኃብት ትስስር ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ያለ መረጋጋት እና ደኅንነት፣ የእርሷም ደኅንነት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ስላለው በንቃት ትከታተለዋለች።

በሶማሊያ አንገቷን እያስገባች ያለች ሌላኛዋ አገር ሩስያ ናት።

ሩስያ የሶማሊያን 684 ሚሊዮን ዶላር እዳ በመሰረዝ 25 ሺህ ቶን ስንዴ በመለገስ ወዳጅነቷን ለማጠናከር ሞክራለች።

ሞስኮ ወዳጅ አገር መሆን ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ወደፊት ላይ ድርሻ እንዲኖራት ትፈልጋለች።

ይህ የዓለም አቀፉ ሥርዓት አንድ ባህርይ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ኤለም አይሪስ (ዶ/ር) ።

አገራት ብሔራዊ የንግድ ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ ይፎካከራሉ የሚሉት የአንካራ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሯ፣ ቱርክ በሶማሊያ የምትገኘው የትኛውንም አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት ለመግፋት አይመስለኝም ይላሉ።

ምክንያቱም በሁለቱ አገራት ያለው ትብብር ለቀጠናው መረጋጋት አስፈላጊ ስለሆነ የግድ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።