Friday, 20 September 2024 18:46

Written by  Administrator

የአዳብና ባሕል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ስራዎች እየተሰሩ "ናቸው" ተባለ

የአዳብና ባሕል የልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች ጨዋታና መተጫጫ ስነ ስርዓት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተነግሯል። ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም. አዘጋጆቹ በቶቶት የባሕል አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ስነ ስርዓቱ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ በድምቀት እንደሚከበር አስታውቀዋል።

አዳብና በከስታኔ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ማህበርን በመወከል አዘጋጆቹ እንዳብራሩት ከሆነ፣ ማሕበራቸው “ይህ ድንቅ የሆነ” የአዳብና ባሕል በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በፌስቲቫልነት እንዲታወቅና በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ፣ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ በመሆን ለአካባቢውም ለኢትዮጵያም የገቢ ምንጭ እንዲሆን ስነ ስርዓቱን የማስተዋወቅ ስራዎች እየሰራ “ነው” ብለዋል።


“ይህ ባሕል በተለያዩ ምክንያቶች ደብዝዞና ሊጠፋ ተቃርቦ ነበረ” የተባለ ሲሆን፣ የአዳብና በከስታኔ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ማህበር ከአካባቢው የመንግስት መዋቅሮች ጋር በመሆን ባደረገው ጥረት ባሕሉ ጥንታዊ ወጉና ቱባ ባህሉን ይዞ በከፍተኛ ሁኔታ በማንሰራራት በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ላይ በፌስቲቫልነት እየተከበረ እንደሚገኝ ተገልጿል።


አዳብና በክስታኔ ጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ከጨዋታ ባለፈ፣ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ትዳር የሚመሰርቱበት የወጣቶች ባሕል መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል። “ይህም በአካባቢው ዘንድ ትዳር የሚመሰረተው በሁለቱ ተቃራኒ ጾታ ምርጫና መፈቃቀድ ብቻ የነበረና የሴቶች መብትና ነፃነት የተጠበቀ መሆኑን ያሳያል።” ብለዋል፣ አዘጋጆቹ።



በያዝነው 2017 ዓ.ም. የአዳብና በክስታኔ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ማሕበር አዳብናን ሰፋ ባለና በደመቀ ሁኔታ በፌስቲቫልነት ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅቶች ማድረጉን አስታውቋል። አያይዞም፣ ዘንድሮ ፌስቲቫሉ መስከረም 18 በምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ ኬላ ከተማና በሌሎች የሶዶ-ከስታኔ አካባቢዎች የሚከበር እንደሚሆን ተገልጧል።


በጥናት በተረጋገጠ መረጃ መሰረት፣ የአዳብና ባሕል ከ800 ዓመታት በፊት ጀምሮ በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ አካባቢ ለዘመናት ሲከበር መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።