ኻሊድ ሜሻል [ግራ]፣ ያህያ አያሽ [መሐል] እና ጭምብል ያጠለቀ የእስራኤል ሰላይ
የምስሉ መግለጫ,ኻሊድ ሜሻል [ግራ]፣ ያህያ አያሽ [መሐል] እና ጭምብል ያጠለቀ የእስራኤል ሰላይ

ከ 8 ሰአት በፊት

የሄዝቦላህ መሪዎች እና አባላት የሚጠቀሙበት የመገናኛ መሣሪያ የሆነው ፔጀር የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል። እነዚህ መዳፍ የማይሞሉ መሣሪያዎች ውስጥ የተጠመዱ ፈንጂዎች ፈንድተው 40 ገደማ ሰዎችን ገድለዋል።

የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ፔጀር የሚጠቀመው በእስራኤል የረቀቀ የስለላ መረብ ከመጠመድ ለማምለጥ በማሰብ ነው። ነገር ግን እነዚህ ፔጀሮች ፈንድተው የሰው ነፍስ ከማጥፋታቸውም በላይ ብዙዎች ክፉኛ እንዲቆስሉ ምክንያት ሆነዋል።

የሊባኖስ መንግሥት “የእስራኤል የወንጀል ወረራ” ሲል ከጥቃቱ ጀርባ ያለችው እስራኤል ናት ይላል። ሄዝቦላህ ደግሞ “ተመጣጣኝ ምላሽ” ለመስጠት በመሪው አማካኝነት ዝቷል።

እስራኤል እስካሁን ስለጥቃቱ ትንፍሽ አላለችም። አንዳንድ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት የአገሪቱ ሚኒስትሮች ስለጥቃቱ ምንም አስተያየት እንዳይሰጡ ታዘዋል።

እስራኤል ለሰከንዶች አይኗን ሳትከድን ነው የሄዝቦላህን እንቅስቃሴ የምትከታተለው። ከሰሞኑ የደረሱት ጥቃቶች በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግጭት አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ ብዙዎች ይጠረጥራሉ።

እንደሚባለው እስራኤል ከዚህ ጥቃት ጀርባ ከሆነች ከአገሪቱ መብረቃዊ እና ውጤታማ እርምጃዎች መካከል አንዱ ይሆናል ማለት ነው። እስራኤል ለመሰል ጥቃቶች አዲስ አይደለችም። በተለይ የስለላ መሥሪያ ቤቷ ሞሳድ በዚህ የተካነ ነው።

ሞሳድ በጣም በርካታ ስኬታማ የሚባሉ ተልዕኮዎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ በማካሄድ ዝናን ያተረፈ ተቋም ነው። እንደማሳያ የተወሰኑትን እናንሳ. . .

በፔጀር ፍንዳታ ምክንያት የሞተው የሄዝቦላህ ታጣቂ የሆነው ሁሴን አምሀዝ የቀብር ሥነ-ሥርዓት
የምስሉ መግለጫ,በፔጀር ፍንዳታ ምክንያት የሞተው የሄዝቦላህ ታጣቂ የሆነው ሁሴን አምሀዝ የቀብር ሥነ-ሥርዓት

የናዚው አዶልፍ ኢክማን

ሞሳድ ከሚታወቅባቸው የስለላ ሥራዎች አንዱ በአውሮፓውያኑ 1960 የናዚ ጀርመን የጦር መኮንን የሆነው አዶልፍ ኢክማንን ከአርጀንቲና አፍኖ ያመጣበት ሴራው አንዱ ነው።

ሆሎኮስት ተብሎ የሚጠራው የአይሁዶች ጭፍጨፋን ካቀናበሩ የናዚ መኮንኖች መካከል አንዱ የሆነው ኢክማን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ማጎሪያዎች አይሁዶች እንዲገደሉ አድርጓል። በወቅቱ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች በናዚ ጀርመን ተገድለዋል።

ኢክማን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተገባደደ በኋላ በተለያዩ አገራት ሲደበቅ ቆይቶ በስተመጨረሻም መኖሪያውን አርጀንቲና አደረገ።

14 ሰላዮች ያሉት የሞሳድ ቡድን ኢክማንን አፈላልጎ፣ ከደቡብ አሜሪካዊቷ አገር አርጀንቲና አፍኖ ወደ እስራኤል በማምጣት ለፍርድ በማቅረብ በሞት ተቀጥቷል።

የናዚ ጀርመን መኮንን የነበረው አዶልፍ ኢኽማን በእስራኤል የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል
የምስሉ መግለጫ,አዶልፍ ኢክማን (መነጽር ያደረገው) በእስራኤል የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል

የኢንቴቤ ኦፕሬሽን

በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ ውስጥ በእስራኤል የስለላ ድርጅት የተካሄደው የኢንቴቤ ኦፕሬሽን ከሞሳድ ትልቅ ድሎች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።

ሞሳድ የደኅንነት መረጃዎችን ሲያቀርብ የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ደግሞ እጅግ ውስብስቦቹን ተልዕኮ በስኬት አጠናቅቋል።

ከእስራኤል ቴል አቪቭ በግሪክ አቴንስ በኩል ወደ ፓሪስ እያቀና የነበረው አውሮፕላን ተጠልፎ ነበር ወደ ኡጋንዳ የመጣው። አውሮፕላኑ 250 መንገደኞች አሳፍሮ የነበረ ሲሆን፣ 103 የሚሆኑት እስራኤላውያን ናቸው።

ሁለት የፍልስጤም ሕዝባዊ ነፃነት ግንባር አባላት እና ሁለት ጀርመናውያን ጠላፊዎቹ አውሮፕላኑ አስገድደው ወደ ኡጋንዳ እንዲያበር አስገደዱት። አገራትን አቋርጠው የዜጎቻቸውን ሕይወት ለመታደግ የተሰማሩት የእስራኤል ኮማንዶዎች በሞሳድ ድጋፍ ታጋቾቹን ማስለቀቅ ችለዋል።

ይህን የአውሮፕላን ጠለፋ ለማክሸፍ በተወሰደ እርምጃ ሦስት ታጋቾች፣ ጠላፊዎቹ፣ በርካታ የኡጋንዳ ወታደሮች እና የአሁኑ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ወንድም ዮናታን ኔታኒያሁ ተገድለዋል።

የኢንቴቤ አውሮፕላን ታጋቾች ከተለቀቁ በኋላ
የምስሉ መግለጫ,የኢንቴቤ አውሮፕላን ታጋቾች ከሳምንት በኋላ ነው የተለቀቁት

ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ መውሰድ

ሌላው ሞሳዳ ካከናወናቸው ኦፕሬሽኖች ስኬታማ የሚባለው 7 ሺህ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ከኢትዮጵያ በምሥጢር በማስወጣት በሱዳን በኩል ወደ እስራኤል ለመውሰድ የተደረገው ነው።

ይህ የሆነው በ1980ዎቹ ሲሆን ሞሳድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኼም ቤጊን በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሐሰተኛ ‘የዳይቪንግ ሪዞርት’ (የመዝናኛ ስፍራ) ሽፋንን ተጠቅሞ ቤተ-እስራኤላውያኑን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ማጓጓዝ ችሏል።

ሱዳን በወቅቱ የእስራኤል ጠላት የሆነው የአረብ ሊግ አባል ነበረች። የሞሳድ አባላት በሱዳን የቀይ ባሕር ወደብ አካባቢ ሪዞርት አቋቁመው ነበር። ይህ ሪዞርት ለሰላዮቹ እንደ ካምፕ ሆኖ ነበር የሚያገለግለው።

ሰላዮቹ ቀን ቀን የሆቴል ሠራተኛ ሆነው ያገለግላሉ። ማታ ማታ ደግሞ ከኢትዮጵያ በእግራቸው የመጡ አይሁዶችን በድብቅ በአውሮፕላን እና በባሕር ያጓጉዛሉ።

ይህ ኦፕሬሽን ቢያንስ ለአምስት ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ የሰላዮቹ እንቅስቃሴ በተጋለጠበት ወቅት የሞሳድ ቡድን አባላት ሱዳንን ለቅቀው ወጥተው ነበር።

የሞሳድ መኮንን ከሱዳን ወደ እስራኤል ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የተጫኑበት ክፍት መኪና አጠገብ ቆሞ
የምስሉ መግለጫ,የሞሳድ መኮንን ከሱዳን ወደ እስራኤል ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ጋር

የሙኒክ ኦሊምፒክ አፀፋ

አውሮፓውያኑ 1972 የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ‘ብላክ ሴፕተምበር’ በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ የሄዱ ሁለት የእስራኤል ኦሊምፒክ ቡድን አባላትን ገድሎ ዘጠኙን ደግሞ አገታቸው።

በወቅቱ የምዕራብ ጀርመን ፖሊስ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት ቢያደርግም ባለመሳካቱ ዘጠኙም ታጋቾች ተገደሉ።

በዚህ ጥቃት ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉትን ለመበቀል ዓላማ ይዞ አደን ያካሄደው ሞሳድ፣ ሞሐመድ ሀምሻሪን ጨምሮ በርካታ የፍልስጤም ነፃ አውጭ ቡድን አባላትን ዒላማ ማድረግ ጀመረ።

ሞሐመድ ሀምሻሪ ፓሪስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ስልክ ላይ በተጠመደ ፈንጂ አማካይነት ተገደለ።

ሀምሻሪ በፍንዳታው አንድ እግሩን ካጣ በኋላ ነው ከቀናት በኋላ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ለሞት የበቃው።

በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሄደው ታግተው የተገደሉ የእስራኤል አትሌቶችና አሰልጣኞች ፎቶ
የምስሉ መግለጫ,በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሄደው ታግተው የተገደሉ የእስራኤል አትሌቶችና አሠልጣኞች

ያህያ አያሽ እና የሚፈነዱት ስልኮች

በተመሳሳይ በ1996 በተካሄደ ኦፕሬሽን ያህያ አያሽ የተባለው ለሐማስ ቦምብ የሚሠራው ግለሰብ ሞቶሮላ አልፋ የተሰኘው የግንኙነት ሬዲዮው ላይ በተጠመደ 50 ግራም በሚመዝን ፈንጂ አማካይነት ተገደለ።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪ የነበረው አያሽ ቦምብ በመሥራት ጥበቡ እና የእስራኤል መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ውስብስብ ጥቃቶች በማቀነባበር ይታወቃል።

በዚህ ድርጊቱ ምክንያት ነው በእስራኤል የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ዘንድ እጅግ ተፈላጊው ሰው የሚል መዝገብ ላይ የሰፈረው።

በአውሮፓውያኑ 2019 እስራኤል ግድያውን በተመለከተ ደብቃው የነበውን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ ቻነል 13 የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ አያሽ ከመሞቱ በፊት ከአባቱ ጋር ያደረገውን የስልክ ልውውጥ አስደምጧል።

የአያሽ እና የሀምሻሪ ግድያ የረቀቀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈፀም ግድያ ምሳሌዎች ናቸው።

የያህያ አያሽ ፎቶ ቢልቦርድ ላይ ተሰቅሎ
የምስሉ መግለጫ,ያህያ አያሽ የፍልስጤም ነፃነት አርማ ተደርጎ ይቆጠራል

ታንቆ የተገደለው ማህሙድ አል-ማብሁህ

የሐማስ ነባር ወታደራዊ መሪ የነበረው ማህሙድ ማብሁህ በአውሮፓውያን 2010 ነው ዱባይ ውስጥ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ የተገደለው።

መጀመሪያው ሰውየው ተፈጥሯዊ ሞት የሞተ ይመስል ነበር። ነገር ግን የዱባይ ፖሊስ የፀጥታ ካሜራውን ካጠኑ በኋላ ማህሙድ በሰው እጅ እንደተገደለ ለማወቅ ችለዋል።

ፖሊስ ቆየት ብሎ ባወጣው መግለጫ ማህሙድ መጀመሪያ በኤሌክትሪክ ንዝረት ከተገደለ በኋላ ቀጥሎ እንደታነቀ ይፋ አደረገ።

ከግድያው ጀርባ የእስራኤሉ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሞሳድ አለበት መባሉን ተከትሎ በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ነበር።

ነገር ግን የእስራኤል ዲፕሎማቶች በተደጋጋሚ ግድያው በሞሳድ ስለመፈፀሙ የሚያሳይ ማስረጃ የለም ሲሉ ተከራክረዋል። በግድያው አልተሳተፍንምም የሚል አስተያየት ሰጥተው አያውቁም።

ይህ የእስራኤል ፖሊሲ ነው። አገሪቱ በመሰል ጥቃቶች አሊያም ግድያዎች ላይ እጇ ይኑርበት አይኑርበት መግለጫ አትሰጥም። ለየትኛውም ክስተት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ሰጥታ አታውቅም።

ማሕሙድ አል-ማብሁህ

ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎች

ምንም እንኳ ሞሳድ በርካታ የተሳኩ ኦፕሬሽኖች ቢፈጽምም ታዋቂ የሆኑ ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎችን አካሂዷል።

በአውሮፓውያኑ 1997 እስራኤል የሐማስ ፖለቲካዊ ቢሮ ኃላፊ ኸሊድ ሜሻል ጆርዳን እያሉ በመርዝ ለመግደል ያደረገችው ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ተከስቷል።

የሞሳድ ሰላዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ እስራኤል ለሜሻል የተሰጠውን መርዝ የሚያረክስ መድኃኒት ለመስጠት ተገዳለች።

በዚህ ሙከራ ሳቢያ በጆርዳን እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ነበር።

በ2003 እስራኤል በጋዛ ከተማ የሚገኘውን የሐማሱ መሪ ማህሙድ አል-ዛሃርን ቤት በአየር ጥቃት አወደመች። ምንም እንኳ አል-ዛሃር ከጥቃቱ ቢተርፍም ሚስቱ እና ወንድ ልጁ እንዲሁም በርካታ ሰዎች በጥቃቱ ተገደሉ።

ኻሊድ ሜሻል ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ
የምስሉ መግለጫ,ኻሊድ ሜሻል በአውሮፓውያኑ ከ1996 እና 2017 የሐማስ መሪ ሆኖ አገልግሏል

የሐማስ ጥቃት

አውሮፓውያኑ ጥቅምት 1973 ግብፅ እና ሶሪያ በሶቪየት ኅብረት ታግዘው እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል።

ከ50 ዓመታት በኋላ እስራኤል ድጋሚ ድንገተኛ ጥቃት ተከፈተባት። መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ተነስተው ወደ እስራኤል በመግባት ያልተጠበቀ ጥቃት ፈፀሙ።

የእስራኤልን ጠላቶች በያሉበት እግር በእግር ይከታተላል የሚባለው ሞሳድ ይህ ከባድ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል ቀድሞ ሊደርስበት አለመቻሉ በአንዳንዶች ዘንድ ወቀሳ እንዲሰነዘርበት እያደረገ ነው።

የእስራኤል ባለሥልጣናት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ባደረሰው ጥቃት በአብዛኛው ሰላማዊ የሆኑ 1200 ሰዎች ገድሎ ከ250 በላይ የሚሆኑት ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል ይላሉ።

ለሐማስ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በሚል እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ጦርነት ከፍታ አሁን ድረስ እየተካሄደ ነው። በዚህ ጦርነት ሳቢያም ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አብዛኛዎቹ የጦርነቱ ሰለባዎች ሰላማዊ ዜጎች ናቸው ይላል።