የቴሌግራም ገጽ

ከ 6 ሰአት በፊት

ዩክሬን ለመንግሥት እና ወታደራዊ ሠራተኞች እንዲሁም በመከላከያ ዘርፍ ውስጥ ላሉ እና ቁልፍ ለሆኑ መሠረተ ልማት ሠራተኞች በተሰጡ የመንግሥት መሣሪያዎች ላይ ቴሌግራም መጠቀምን አገደች።

የአገሪቷ የብሔራዊ ደኅንነት እና መከላከያ ምክር ቤት (ርንቦ) እንዳለው ውሳኔው ከሁለት ዓመት በፊት በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ የከፈተችው ሩሲያ የምትፈጥረውን ስጋት ለመቀነስ ያለመ ነው።

ምክር ቤቱ አርብ እለት ባወጣው መግለጫ “ጠላት የሳይበር ጥቃት ለመፈፀም፣ ሃሰተኛ እና አሳሳች ሶፍትዌሮችን ለማሰራጨት፣ የተጠቃሚዎችን አድራሻ ለመለየት እና የሚሳኤል ጥቃት ኢላማ ላይ ማስተካከያ ለማድረግ በስፋት ቴሌግራምን ይጠቀማል” ብሏል።

ቴሌግራም በዩክሬን እና በሩሲያ በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በጦር አባላት ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው ላይ እንዳለው እግዱን ለመፈፀም ከዩክሬን ከፍተኛ የኢንፎርሜሽን እና የደኅንነት ባለሥልጣናት እንዲሁም ከጦሩ እና ከሕግ አውጪዎች ጋር ከስምምነት ተደርሷል።

የጦሩ የስለላ ኃላፊ ክይርይሎ ቡዳኖቭም፣ የሩሲያ ልዩ አገልግሎቶች የተሰረዙ አሊያም የጠፉ መልዕክቶችን ሳይቀር የቴሌግራም ተጠቃሚዎች የግል መረጃዎችን ማግኘት መቻላቸውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ አቅርበዋል ብሏል መግለጫው።

ቡዳኖቭ “ ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን ሁልጊዜም እደግፋለሁ፤ መደገፌንም እቀጥላለሁ፤ ነገር ግን የቴሌግራም ጉዳይ ከመናገር ነጻነት ጋር የሚያያዝ አይደለም።የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው” ማለታቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ሆኖም ሥራቸው ቴሌግራምን መጠቀም የሚያስገድዳቸው ባለሥልጣናትን ከእገዳው ነጻ ይሆናሉ ተብሏል።

የደኅንነት ምክር ቤቱ – ርንቦ የሐሰተኛ መረጃዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ኃላፊ አንድሪይ ኮቫልንኮ በበኩላቸው እግዱ ተግባራዊ የሚሆነው በመንግሥት በተሰጡ መገልገያ መሣሪያዎች እንጂ የግል ዘመናዊ ስልኮች ላይ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የጦር አባላትም ቢሆኑ ይፋዊ የቴሌግራም ገጾቻቸውን ‘አፕዴት’ ማድረጋቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ኃላፊው አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ኢንተርኒውስ በተሰራ የዳሰሳ ጥናት መሠረት በዩክሬን ዜናዎችን ለማንበብ እና መረጃዎችን ለማግኘት ቴሌግራም በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።72 በመቶ የሚሆኑ ዩክሬናውያን መተግበሪያውን እንደሚጠቀሙም የዳሰሳ ጥናቱ አመልክቷል።

የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያው ቴሌግራም የተመሠረተው የሩሲያ ተወላጅ በሆነው ፓቭል ዱሮቭ እና ወንድሙ እአአ በ2013 ነበር።

ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ዱሮቭ ተቃዋሚ ገጾችን እንዲዘጋ በመንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ ለመቀበል ባለመፍቀዱ ሩሲያን ለቅቆ ለመውጣት ተገዷል።

የሩሲያ፣ የፈረንሳይ እና የአረብ ኤምሬትስ ጥምር ዜግነት ያለው ያለው ዱሮቭ፣ ከታዋቂው የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ጋር በተያያዘ በተፈጸም ጥሰት ባለፈው ወር በፈረንሳይ ምርምራ ተደርጎበታል።

የእርሱ ጉዳይም ከመናገር ነጻነት ፣ ከተጠያቂነት እና የማኅበራዊ መድረኩን ይዘቶች ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ ክርክር እንዲነሳ አድርጎ ነበር።

ዱሮቭ ሐምሌ ወር ላይ እንደገለጸው ወርሃዊ የቴሌግራም ንቁ ተጠቃሚዎች ቁጥር 950 ሚሊዮን ደርሷል።