ጥቃቱ የተፈፀመበት ሥፍራ

21 መስከረም 2024, 08:13 EAT

ተሻሽሏል ከ 4 ሰአት በፊት

አርብ ዕለት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት የሄዝቦላህ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ተገደሉ።

ሄዝቦላህ ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮቹን ጨምሮ 31 ሰዎች በአርብ ዕለቱ የእስራኤል ጥቃት መሞታቸውን አስታወቋል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በጥቃቱ ሦስት ሕጻናትን ጨምሮ 31 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

ሄዝቦላህ በጥቃቱ የተገደሉበት ሁለቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ኢብራሂም አቂል እና አህመድ ዋህቢ መሆናቸው ይፋ አድርጓል።

እስራኤልም በአየር ድብደባው ከሞቱ በርካታ የሄዝቦላህ ቁልፍ ሰዎች መካከል ኢብራሂም አቂል አንዱ ነው ብላለች።

ቀደም ብሎ የሊባኖስ ባለሥልጣናት የእስራኤል የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች የሚኖሩበትን ዳሂህ የተባለ ሥፍራ ከደረሰ በኋላ ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ተናግረው ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል “በቤሩት ዒላማውን የጠበቀ የአየር ጥቃት” ማካሄዱን አስታውቋል።

መከላከያ ኃይሉ የሄዝቦላህ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆነው ኢብራሂም አቂል ከተገደሉት መካከል መሆኑን ጠቅሶ “ሌላ ከፍተኛ” ተዋጊ መሞቱንም ገልጾ ነበር።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመበት ሥፍራ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ ነው ተብሎ ይታመናል።

ከጥቃቱ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ወደ ሥፍራው አምርተው በጥቃቱ ከተደረመሱ ሕንጻዎች ውስጥ በሕይወት የተረፉትን ለማውጣት ሲረባረቡ ታይተዋል።

በጥቃቱ ቢያንስ አንድ የመኖርያ ሕንጻ የተደረመሰ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የሄዝቦላህ አባላት መንገዶችን የዘጉ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ ጥቃቱ መገረምን እና ድንጋጤን ፈጥሮባቸው ታይተዋል።

በዚህ ሳምንት እስራኤል የሄዝቦላህ አባላትን ዒላማ ባደረገ ጥቃት የመልዕክት መቀበያ መሳርያዎቻቸው፣ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎቻቸው ፈንድቶ ጉዳት እንዲያደርስ ማድረጓ ይታወሳል።

በዚህ እስራኤል አቀነባብረዋለች ተብሎ በስፋት በታመነው ጥቃት በርካቶች ሲሞቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል።

አርብ ዕለት የተፈፀመው የአየር ድብደባ የሄዝቦላህ አዛዥ የሆኑት ፉአድ ሹክር ከተገደሉበት ከሐምሌው ጥቃት ወዲህ ቤሩት ላይ የደረሰ የመጀመርያው ጥቃት ነው።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ በመግለጫቸው ላይ የሄዝቦላህ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ የነበረው አቂል ከሌሎች ከፍተኛ የቡድኑ አመራሮች ጋር ተገድሏል ብለዋል።

ሃጋሪ “ በምዕራብ ቤሩት በሚገኘው እና ሰላማዊ ዜጎች በሚኖሩበት ዳሂህ በተባለ ሥፍራ በሚገኝ የመኖርያ ሕንጻ ምድር ቤት፣ ሰላማዊ ዜጎችን እንደ መከላከያ ለመጠቀም በማሰብ፣ ተሰባስበው ተደብቀው ነበር።” ብለዋል።

የአቂልን ሞት በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ ያረጋገጠው ሄዝቦላህ “ታላቁ የጂሃድ መሪ” ሲል አወድሶታል።

ሄዝቦላህ አርብ ዕለት ሰሜናዊ እስራኤል በሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መክፈቱን አስታውቆ ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ ወደ ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል140 ሮኬቶች መተኮሳቸውን ሲገልጽ፣ የእስራኤል ፖሊስ በበኩሉ መንገዶች መውደማቸውን ለነዋሪዎች አስታውቆ የማስጠንቀቅያ መልዕክት አስተላልፏል።

ይህ የተሰማው እስራኤል ሊባኖስ የሚገኙ 100 የሄዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ሌሎች “የሽብር ቦታዎች” እንዲሁም የመሣሪያ ማከማቻዎች መምታቷን ካስታወቀች በኋላ ነው።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አክለውም የተገደሉት ወታደራዊ አመራሮች “ ሄዝቦላህ ‘ገሊላን እንውረር’ የተሰኘ ጥቃት ለመፈጸም እና እስራኤላውያን ወደ’ሚገኙበት ሰርጎ በመግባት ንፁኀንን ለመግደል እቅዶችን እያዘጋጀ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ እቅድ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰማው እአአ በ2018 ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ግዛት ገብቶ ንፁኀንን አግቶ ለመውሰድ እና ለመግደል አቅዶ ያዘጋጀው ነው የተባለ መተላለፍያ ዋሻ አግኝቶ መዝጋቱን መከላከያ ኃይሉ በገለፀበት ወቅት ነበር።

በሚያዝያ ወር አሜሪካ አቂል ወይንም ደግሞ በሌላ ስሙ ታህሲንን እየፈለገች መሆኗን ገልጻ፣ ያለበትን ለጠቆመ አልያም በቁጥጥር ሥር እንዲውል ላደረገ ጠቀም ያለ የገንዘብ ጉርሻ ማዘጋጀቷን ገልጻ ነበር።

አሜሪካ ይህንን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር በጥብቅ የምትፈልገው በእስራኤል፣ ዩኬ፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ሄዝቦላህ ጋር ባለው ግንኙነት ነው።

አቂል በ1980ዎቹ በቤሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም የባሕር ኃይል ላይ ጥቃት የፈጸመው ቡድን አባል ነበር።

በ1980ዎቹ አቂል በቤሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም የባሕር ኃይል ላይ ጥቃት በመፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት የሆነው ቡድን አባል ነበር።

በዚህ ሳምንት በመላው ሊባኖስ ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ የመልዕክት መለዋወጫ መሣርያዎች ፈንድተው በርካቶች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ካደረሱ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት ነግሷል።

ለጥቃቱ የሄዝቦላህ እና የሊባኖስ ባለሥልጣናት እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ለቀረበባቸው ክስ ማስተባበያ አልሰጡም።በርካታ ተንታኞች ግን እስራኤል ከጥቃቱ ጀርባ መኖሯን ይስማሙበታል።

የኤሌክትሮኒክ መልዕክት መቀባበያ ፔጀሮቹ የፈነዱት ለሄዝቦላህ ከመላካቸው በፊት ጥቂት መጠን ያለው ፈንጂ ተጨምሮባቸው ነው የሚል ጥርጣሬ አለ።

የሄዝቦላህ መሪ “ለእስራኤል ክትትል ያጋልጠናል።” በሚል ስጋት የቡድኑ አባላት በተንቀሳቃሽ ስልክ እንዳይጠቀሙ ካዘዘ በኋላ አባላቱ በአመዛኙ የሚጠቀሙት በጥሪ ማቀባበያዎቹ ፔጀሮች እንደነበር ተገልጿል።

እስራኤልን ለመቃወም በማሰብ የተቋቋመው ሄዝቦላህ የተመሰረተው እአአ በ1980ዎቹ በሺአ ሙስሊሞች ነው።

በወቅቱ ሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የነበረች ሲሆን የአገሪቱን ደቡባዊ ክፍልም እስራኤል ተቆጣጥራ ነበር።