ከፈነዱት የመገናኛ መሳርያዎች የተሰበሰቡ ቅሪቶች

21 መስከረም 2024, 08:40 EAT

በሊባኖስ በሁለት የተለያዩ ሥፍራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ፔጀሮች እና የሬድዮ መገናኛ መሳርያዎች ፈንድተው ቢያንስ 37 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

እስካሁን ድረስ እንዲህ ዓይነት ጥቃት እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ለማወቅ ጥረት እየተደረገ ነው።

ሊባኖስ እና የመገናኛ መሳርያዎቹ ዒላማ የተደረጉበት ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።በእርግጥ እስራኤል ያለችው ነገር የለም።

ቢቢሲ ይህንን ጉዳይ ይዞ ስማቸው የተነሳ አምራቾችን ለማናገር ታይዋን፣ ጃፓን፣ ሀንጋሪ ፣ እስራኤል ከዚያም ሊባኖስ ክትትል አድርጓል።

እነዚህ ጉዳዮች ግን እስካሁን ድረስ መልስ አላገኙም።

ፔጀሮቹን ማን ነው ያመረታቸው?

መጀመርያ ላይ ፔጀሮቹ ውስብሰብ በሆነ መንገድ ተጠልፈው እንዲፈነዱ ተደርገዋል የሚል ግምት ነበር። ባለሙያዎች ግን ይህንን ግምት ውሃ አያነሳም በሚል ውድቅ ያደረጉት ወድያውኑ ነው።

ባለሙያዎችም በዚህ መጠን ውድመት ለማድረስ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት መቀበያ ፔጀሮቹ በሄዝቦላህ እጅ ከመግባታቸው በፊት ፈንጂ ተጨምሮባቸው ነው የሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በፍንዳታው የወደመው የመልዕክት መቀባባያ ላይ የታይዋን ኤሌክትሮኒክስ አምራቹ ጎልድ አፖሎ ዓርማ ይታያል።

ቢቢሲ የኩባንያው ቢሮ ይገኝበታል ወደ ተባለው ሥፍራ አምርቶ ነበር።

የኩባንያው ቢሮ የሚገኘው ታይዋን የንግድ መንደር ውስጥ ታይፔይ የተባለ አካባቢ ነው።

የኩባንያው መሥራች ሕሱ ቺንግ-ኩዋንግ ኩባንያቸው ከሊባኖሱ ጥቃት ጋር ፈጽሞ ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል።

ኩዋንግ ከቢሯቸው ውጪ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች “ከሊባኖስ የተገኙትን ምስሎች አይታችሁ ከሆነ በላያቸው ላይ በታይዋን የተመረተ የሚል ጽሑፍ የለባቸውም፤እነዚያን ፔጀሮች እኛ አላመረትናቸውም” በማለት ጣታቸውን ወደ ሀንጋሪው ኩባንያ ቀስረዋል።

ኩባንያው እንደሚለው የግንኙነት መሳሪያዎቹን ለማምረት የንግድ ምልክቱን እና ስሙን እንዲጠቀም ሀንጋሪ ውስጥ ለሚገኘው ‘ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ’ የተባለ ኩባንያ ፈቃድ ሰጥቷል።

ኃላፊው አክለውም ከሦስት ዓመት በፊት የጎልድ አፖሎን የንግድ ምልክት ቢኤሲ በሚያመርታቸው ፔጀሮች ላይ እንዲጠቀም መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ጨምረውም ሁለቱ ኩባንያዎች ለደረሱት ስምምነት ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ ገንዘብ የሚከፍልበት መንገድ “እምብዛም ያልተለመደ” መሆኑን እና በክፍያ በኩል ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር አመልክተዋል።

ክፍያው ሲፈጸም የነበረው በመካከለኛው ምሥራቅ በኩል መሆኑን በመጥቀስ ሕሱ ቺንግ-ኩዋንግ ለጋዜጠኞች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የሀንጋሪው ኩባንያ እዚህ ውስጥ ሚናው ምንድን ነው?

ቢቢሲ ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ ወደ ተመዘገበበት፣በሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት በሚገኝ የመኖርያ ሥፍራ ወደሚገኝ አድራሻው ሄዶ ነበር።

በዚህ አድራሻ ሌሎች 12 ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን ቢኤሲ ኮንሰልቲንግ ማን ነው? ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ማንም ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም።

የሀንጋሪ ባለሥልጣናትም ኩባንያው እኤአ በ2022 መመዝገቡን አስታውሰው በአገሪቱ ውስጥ “ ምንም ዓይነት የማምረቻ ሥፍራ ወይንም ፋብሪካ የሌለው እና የንግድ ወኪል” መሆኑን ገልጸዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያው ሊንክዲን ላይ ቢቢሲ ያገኘው የድርጅቱ መረጃ ከቢኤሲ ጋር ስምንት ድርጅቶች መስራታቸውን ይጠቁማል።

ከእነዚህም መካከል የዩናይትድ ኪንግደሙ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዲፊድ (DFID) ይገኝበታል።የዩኬ የውጪ ጉዳይ መሥርያ ቤት ለቢቢሲ እንደገለጸው ጉዳዩን በመመርመር ላይ ነው። ነገር ግን መጀመርያ ላይ ከመሥርያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በነበረው ንግግር ከቢኤሲ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው መረዳት ተችሏል።

የቢኤሲ ድረ ገጽ ክርስቲያና ባርሶኒ አርሲዲያኮኖ የተሰኘች ሴትን መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ አስቀምጧል።

ቢቢሲ በተደጋጋሚ የተባለችውን ግለሰብ ለማግኘት ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሊሳካለት አልቻለም።

ይኹን እንጂ ኤንቢሲ የተባለው የዜና አውታር ላይ ቀርባ “እኔ ፔጀሮችን አላመርትም።በመካከል ያለሁ ወኪል ነኝ” ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

ታድያ ከቢኤሲ ኮንሰልቲንግ ጀርባ ያለው ማን ነው?

ኒውዮርክ ታይምስ ኩባንያው የእስራኤል የደኅንነት መሥርያ ቤት የቀኝ እጅ ነበር ሲል ዘግቧል።

ጋዜጣው የእስራኤል ሦስት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ፔጀሮቹን ማን እንዳመረታቸው ለመደበቅ እንዲቻል ሁለት ሌሎች ኩባንያዎች በሽፋንነት መከፈታቸውን ዘግቧል።

በርግጥ ቢቢሲ የዚህን ዘገባ እውነተኛነት ከገለልተኛ ወገን ማጣራት እና ማረጋገጥ አልቻለም።

የቡልጋርያ ባለሥልጣናት ግን ከቢኤሲ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ሌላ ድርጅት ላይ ምርመራ መጀመራቸውን ማወቅ ተችሏል።

የቡልጋርያ መገናኛ ብዙኃን – ቢቲቪ፣ ሐሙስ እለት እንደዘገበው ከሆነ ሊባኖስ ላይ ጥቃት ካደረሰው መሳርያ ጋር በተገናኘ 1.6 ሚሊዮን ዩሮ በቡልጋርያ በኩል አልፎ ወደ ሀንጋሪ ተሸጋግሯል ብሏል።

የመገናኛ ሬድዮኖቹ እንዴት ሊጠለፉ ቻሉ?

የታጣቂው ሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታዎች ናቸው በሚባሉት በዋና ከተማይቱ ቤሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች እና በደቡባዊ ሊባኖስ ቡድኑ የሚጠቀምባቸው ‘ዎኪ-ቶኪዎች’ (የሬዲዮ መገናኛዎች) ፈንድተዋል።

እነዚህ በእስራኤል ሁለተኛ ዙር ጥቃት ዒላማ የተደረጉት የሬድዮ መገናኛዎቹ ከየት እንደመጡ ብዙ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ከፈነዱት የተወሰኑት ሞዴላቸው IC-V82 የሆነ እና በጃፓኑ ኩባንያ ኤኮም መመረታቸውን ማወቅ ተችሏል።

ሄዝቦላህ እነዚህን የሬድዮ መገናኛዎች ከአምስት ወራት በፊት እንደገዛቸው ሮይተርስ የደኅንነት ምንጮችን አናግሮ ዘግቧል።

አሶሼትድ ፕሬስ የኩባንያውን የአሜሪካ ወኪል አናግሮ እንደዘገበው ከሆነ ሊባኖስ ውስጥ የፈነዱት የሬድዮ መገናኛዎች በጃፓኑ ኩባንያ የተመረቱ ሳይሆኑ ተመሳስለው የተሰሩ ናቸው።

እንደዚህ ዓይነት ምርቶችን ደግሞ በኦንላየን ላይ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል ሲል ገልጿል።

ቢቢሲ አይኮም አይሲ-ቪ82 (Icom IC-V82) የተሰኘውን ሞዴል በኦንላይን መገበያያዎች ላይ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ተረድቷል።

አይኮም በበኩሉ እነዚህን ሞዴሎች ማምረትም ሆነ መሸጥ ካቆመ አስር ዓመት እንዳለፈው በላከው መግለጫ ላይ አስታውቋል።አክሎም መገናኛ ሬድዮኖቹን ለማንቀሳቀስ የሚረዳውን ባትሪ ማምረት ማቆሙንም ገልጿል።

ኩባንያው በተጨማሪ እነዚህን ምርቶች ሌሎች አምርተው እንዲሸጡ ምንም ዓይነት ፈቃድ አለመስጠቱን ገልጾ፣ሬድዮኖቹ በሙሉ የተመረቱት በምዕራብ ጃፓን በሚገኘው ፋብሪካችን ውስጥ ነው ብሏል።

ኬዮዶ የዜና ተቋም እንደዘገበው ከሆነ የአይኮም የበላይ ኃላፊ ዮሺኪ ኢኖሞዮ፣ የፈነዱት የሬድዮ መገናኛዎችን ምስልን በመመልከት በባትሪው አካባቢ የደረሰው ጉዳት በፈንጂ ተሞልተው እንደነበር ያሳያል ብለዋል።

የመገናኛ መሳርያዎቹ እንዴት ፈነዱ?

ጥቃቱ በመንገዶች፣ በመገበያያ ሥፍራዎች እና በመኖርያ ቤቶች ውስጥ በደረሰበት ወቅት የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ማየት እንደተቻለው መሳርያዎቹ ከመፈንዳታቸው ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ተጎጂዎች ወደ ኪሳቸው እጃቸውን ሲሰዱ ይታያል።

ሮይተርስ በተባበሩት መንግሥታት የሊባኖስ መልዕክተኛ የተጻፈ ደብዳቤን ተመልክቶ እንደዘገበው ከሆነ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የመረጃ መለዋወጫዎቹ የፈነዱት “የኤሌክትሮኒክ መልዕክት” ከተላከላቸው በኋላ ነው ሲሉ ደምድመዋል።

ኒው ዮርክ ታይምስ በበኩሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ መሳርያዎቹ ከመፈንዳታቸው በፊት ከሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሮች የመጣ መልዕክት ደርሷቸው ነበር ብሏል።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ ግን ይህ መልዕክት መሳርያዎቹ እንዲፈነዱ የሚያደርግ ነበር።ወደ ሬድዮ መገናኛዎቹ ግን ምን ዓይነት መልዕክት እንደተላከ እስካሁን ድረስ ማወቅ አልተቻለም።

ሌሎች መሳርያዎችስ የእስራዔል ዒላማ ሆነው ይሆን?

በአሁኑ ሰዓት በርካታ ሊባኖሳውያን እየጠየቁት ያለው ጥያቄ ይህ ነው።

ሌሎች ካሜራዎች፣ ላፕቶፖች፣ ስልኮች በእስራኤል የደኅንነት መሥርያ ቤት ዒላማ ተደርገው ፈንጂ ተጠምዶባቸው ሊሆን ይችላል የሚል ፍራቻ በሰፊው አለ።

የሊባኖስ መከላከያ ኃይል በቤሩት ጎዳናዎች ላይ የፈንጂ አምካኝ ሮቦት ይዞ ሲንቀሳቀስ ታይቷል።

በሊባኖስ የሚገኙ የቢቢሲ ባልደረቦች በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት የደኅንነት መሥርያቤቱ ሰዎች አስቁመዋቸው ስልካቸውንም ሆነ ካሜራቸውን እንዳይጠቀሙ ተነግሯቸዋል።

ጊዳ የተባለች ነዋሪ ለቢቢሲ “ሁሉም ሰው ተሸብሯል. . . ከላፕቶፓችን፣ ከስልካችን ጎን መሆን እንዳለብን እና እንደሌለብን ማወቅ አልቻልንም። በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ነገር አደገኛ ነው የሚመስለው።ማንም ምን ማድረግ እንዳለበት አያውቅም።” ብላለች።

ጥቃቱ አሁን ለምን ሊደርስ ቻለ?

የመገናኛ መሳርያዎቹ በዚህ ሳምንት ለምን እንዲፈነዱ ተደረገ የሚለው ላይ በርካታ መላምቶች ይነገራሉ።

አንደኛው መላምት ሄዝቦላህ የእስራኤል እና የሐማስን ጦርነት ተከትሎ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ከተሞች ሲተኩስ የቆየ ሲሆን፣ እስራኤል ለሄዝቦላህ ተስፋ እንዲቆርጥ መልዕክት ማስተላለፍ ፈልጋ ነው የሚለው ቀዳሚ ነው።

ሌላው መላምት ደግሞ እስራኤል በአሁኑ ሰዓት ይህንን እቅዷን መተግበር አላሰበችም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሴራ ሊደረስበት ይችላል የሚል ስጋት በማየሉ የፈጸመችው ነው የሚለው ነው።

አክሲዮስ የተሰኘው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል የመጀመርያ እቅድ እነዚህ የፔጀር ጥቃቶች የሄዝቦላህ ተዋጊዎችን ለማሽመድመድ እና ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለማስቀረት ያለመ ነበር ብሏል።

ነገር ግን እስራኤል ሄዝቦላህ ጥርጣሬ እንዳደረበት መረጃ ስለደረሳት ጥቃቱን ቀድማ ፈጽማለች ሲል ይተነትናል።