የትሬቪስ ኪንግ ፎቶ

21 መስከረም 2024, 13:57 EAT

ባለፈው ዓመት ከደቡብ ወደ ሰሜን ኮርያ በሕገ ወጥ መንገድ አቋርጦ የተያዘው ትሬቪስ ኪንግ፣ በትናንትናው ዕለት የአንድ ዓመት እስር ተፈርደበት።

ትሬቪስ ኪንግ የተባለው የአሜሪካ ወታደር ወደ ሰሜን ኮርያ ከሸሸ በኋላ ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ተደርጎ ክስ የተመሰረተበት ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር።

በትናንትናው ዕለት ከሥራ ገበታው ላይ በመጥፋት እና ባልደረባው ላይ ጥቃት በመፈጸም በሚሉት ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ትሬቪስ፣ የአንድ ዓመት እስር እና ከውትድርና ያለምንም ጥቅም እንዲሰናበት በሚል ተወስኖበታል።

ሆኖም የፍርድ ጊዜውን በማጠናቀቁ እና በዚህ ጊዜ ባሳየው መልካም ሥነ ምግባር ምክንያት የ24 ዓመቱ ኪንግ ነጻ እንዲወጣ መደረጉን ጠበቆቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኪንግ አርብ ዕለት በቴክሳስ ፎርት ብሊስ በተካሄደው ችሎት ከተመሰረቱበት 14 ወታደራዊ ክሶች መካከል በአምስቱ ጥፋተኛ መሆኑን ያመነ ሲሆን ሌሎቹ ውድቅ ተደርገዋል።

በችሎቱ ላይ ኪንግ ለጦሩ ዳኛ ሌተናንት ኮሎኔል ሪክ ማቴው፣ የአሜሪካን ጦር ጥሎ ለመውጣት የወሰነው “በሥራው ባለመርካቱ” እንደሆነ እና ወደ ሰሜን ኮሪያ ከመሸሹ አንድ ዓመት በፊት ጥሎ ለመውጣት ሲያስብ እንደነበር ተናግሯል።

በችሎቱ ተገኝተው እንደዘገቡት ጋዜጠኞች ከሆነም “ከአሜሪካ ጦር መውጣት እና አለመመለስ እፈልግ ነበር” ብሏል ኪንግ።

ከዚህም በተጨማሪ ምንም እንኳን ችሎት ለመቅረብ እና ክሶቹን ለመረዳት ብቁ ቢሆንም የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የኪንግ ጠበቃ ፍራንክሊን ሮሰንብላት በመግለጫቸው እንዳሉት ደንበኛቸው ለተፈጠረው ክስተት ሙሉ ኃላፊነቱን መውሰዱን ገልጸው፣ ኪንግ የልጅነት አስተዳደጉ፣ ወንጀል በሚፈፀምበት አካባቢ ማደጉ እና የአዕምሮ ጤና ችግርን ጨምሮ በሕይወቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገጠሙት አውስተዋል።

“እነዚህ ችግሮችም በጦሩ ውስጥ ያለውን ፈተና እንዳይቋቋም አድርገውታል” ብለዋል ጠበቃ ሮሰንብላት።

ኪንግ የአሜሪካ ጦር ሠራዊትን የተቀላቀለው በአውሮፓውያኑ 2021 ሲሆን ደቡብ ኮሪያ ያለው ካምፕ ውስጥ ነበር።

ወደ ሰሜን ኮሪያ የተሻገረውም ከባድ ጥበቃ በሚደረግለት እና በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ባለ ነጻ ቀጠና በምትገኘው ፓንሙንጆም መንደር ጎብኝዎችን በመቀላቀል በሕገ ወጥ መንገድ ነበር።

ኪንግ ቀደም ብሎ ሁለት ሰዎችን በመሳደብ እና የፖሊስ መኪናን በመምታት ወንጀል በደቡብ ኮሪያ እስር ቤት ወደ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ታስሮ ተለቅቋል።

ከእስር ከተለቀቀ በኋላም ወደ ፎርት ብሊስ የጦር ሰፈር እንዲመለስ እና የሥነ ምግባር ቅጣት እንዲወሰድበት ወደ አየር ማረፊያ ተወስዶ ነበር።

ነገር ግን ኪንግ አውሮፕላኑ ውስጥ በመግባት ፋንታ ጎብኝዎችን በመቀላቀል ሰሜን ኮሪያ ሊገባ የቻለ ሲሆን እዚያም በአካባቢው ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

በወቅቱ የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን፣ ኪንግ የሸሸው በአሜሪካ ጦር ውስጥ ባለው ‘ዘረኝነትና ኢሰብዓዊ አያያዝ’ ምክንያት እንደሆነ ዘግበዋል።

በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሰሜን ኮሪያ የታሰረ የመጀመሪያው አሜሪካዊም ሆኗል።

በወቅቱ የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ በተደረገ “ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት” ከሁለት ወራት እስር በኋላ መለቀቁንና በደቡብ ኮሪያ ወደሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር በአውሮፕላን መወሰዱን አስታውቀዋል።

ከዚያም እአአ መስከረም 28 /2023 ወደ ቴክሳስ ተወስዷል።

በሚቀጥለው ወርም ከጦሩ በመሸሽ ፣ሌሎች የጦር መኮንኖችን በመደብደብ ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የአልኮል መጠጥ ይዞ በመገኘት ፣ ሐሰተኛ መግለጫ በመስጠት እና በወሲብ ተግባር ላይ የተሰማራች ሕፃን ቪዲዮ ይዞ በመገኘት በአሜሪካ ጦር ክስ ተመስርቶበታል።

ኪንግ ከሥራ ገበታው በመጥፋት፣ የጦር መኮንንን ባለመታዘዝ እና ባልታወቀ መኮንን ላይ ጥቃት መሰንዘርን ጨምሮ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

ሌሎች የቀረቡበት ክሶች ግን ውድቅ ተደርገዋል።

አሶሺየትድ ፕረስ የኪንግ ጠበቃ ይግባኝ ለመጠየቅ ከወታደራዊ አቃቤያነ ሕግ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ሐምሌ ወር ላይ ዘግቦ ነበር።

የመጀመሪያው ችሎት በዚያው ወር ውስጥ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች እንዲደራደሩ ቀጠሮው እንዲራዘም ተደርጎ ነበር።

ጠበቃ ሩሰንበላት በመግለጫቸው ምንም እንኳን ደንበኛቸው ነጻ እንደሚወጣ ቢያምኑም ‘አሉታዊ የሕዝብ አመለካከት’ እና ኪንግ በቁም እስር ያሳለፈው ጊዜ በወደፊት ሕይወቱ የሚገጥመውን ቀጣይነት ያለውን ቅጣት ይወክላል ብለዋል።