የእስራኤል ወታደሮች አልጄዚራ በቀጥታ ሥርጭት ላይ ሳለ ወደ ራማላ ቢሮው ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤል ወታደሮች አል ጀዚራ በቀጥታ ሥርጭት ላይ ሳለ ወደ ራማላ ቢሮው ሲገቡ

ከ 8 ሰአት በፊት

የእስራኤል ወታደሮች በወረራ ስር ባለው ዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኘውን የአል ጀዚራ ቢሮን በመውረር ለቀጣዮቹ 45 ቀናት የቴሌቪዥን ጣቢያው ቢሮ እንዲዘጋ አዘዙ።

የታጠቁ እና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ የእስራኤል ወታደሮች በቀጥታ ሥርጭት ላይ የነበረውን የአል ጀዚራ የራማላ ቢሮን የወረሩት እሁድ ማለዳ ላይ ነው።

ወታደሮቹ በዌስት ባንክ የሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያው ቢሮ እንዲዘጋ የሚያዘውን ደብዳቤ ለቢሮው ኃላፊ ዋሊድ አል-ኦማሪ ሲሰጡ እና እሱም ሲያነበው በቀጥታ ሥርጭቱ ተላልፏል።

እስራኤል በኳታር ባለቤትነት ሥር የሚገኘውን የአል ጀዚራ ቴሌቪዥን ሥርጭት “የብሔራዊ ደኅንነቴ ስጋት ነው” በማለት ባለፈው ግንቦት ወር በምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና ናዝሬት ውስጥ የሚገኙትን ቢሮዎቹን በመውረር ተቆጣጥራ ነበር።

እንዲዘጋ ትዕዛዝ የተላለፈበት የአል ጀዚራ የራማላ ቢሮ ኃላፊ ኦማሪ ክስተቱን ተከትሎ “ጋዜጠኞችን በዚህ ሁኔታ ዒላማ ማድረግ ዓላማው እውነትን ማጥፋት እና ሕዝብ ሃቁን እንዳያውቅ መከልከል ነው” ማለቱን ጣቢያው ዘግቧል።

ወታደሮቹ በከተማዋ የቴሌቪዥን ጣቢያው ያለውን የመጨረሻውን ማይክሮፎን እና ካሜራ የወሰዱ ሲሆን፣ ኃላፊውንም ከቢሮው እንዲወጣ ማስገደዳቸውን የጣቢያው ጋዜጠኛ ሞሐመድ አላፊን ተናግሯል።

ጋዜጠኛው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው መልዕክት፣ ወታደሮቹ ዌስት ባንክ ውስጥ የእስራኤል ኃይሎች የሚያካሂዱትን ዘመቻ እየዘገበች ሳለ የተገደለችውን የአል ጀዚራ ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላ ፎቶምን አንስተዋል።

በወቅቱ አል ጀዚራ እና የዓይን እማኞች ፍልስጤማዊ-አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ የተገደለችው በእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት መሆኑን ተናግረው ነበር። ግድያውን ተከትሎ እስራኤል ሺሪን የተተኮሰባት ከፍልስጤማውያን በኩል ነው ያለች ቢሆንም፣ ከወራት በኋላ ግን ከወታደሮቿ መካከል በአንዱ ሊተኮስባት የሚያስችል “ከፍ ያለ አጋጣሚ” ሊኖር እንደሚችል አምናለች።

በእስራኤል መንግሥት እና የኳታር ንብረት በሆነው በአል ጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ መካከል ያለው ግንኙነት ለረጅም ጊዜ በውጥረት የተሞላ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በጋዛ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ግን የበለጠ ተበላሽቷል።

ባለፈው ዓመት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች በኋላ የውጭ ጋዜጠኞች ወደ ስፍራው እንዳይገቡ አግዳለች። በዌስት ባንክ የሚገኙት የአል ጀዚራ ሠራተኞች እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ከስፍራው በቀጥታ ከሚዘገቡ ጥቂት ጋዜጠኞች መካከል ናቸው።

በዚህም የተነሳ እስራኤል የቴሌቪዥን ጣቢያውን የሽብርተኞች ልሳን ነው በማለት ብትከሰውም፣ አል ጀዚራ ግን ይህንን ክስ ያስተባብላል።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ የእስራኤል ፓርላማ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ወቅት የአገሪቱ ደኅንነት ስጋት ናቸው የሚባሉ የውጭ አገራት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በጊዜያዊነት ለመዝጋት የሚያስችል ሕግ ማጽደቁ ይታወሳል።

አሁን ዌስት ባንክ ራማላ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የአልጄዚራ ቢሮ ላይ የተላለፈው የመዝጋት ትዕዛዝ ለ45 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የዕገዳ ጊዜው ሲጠናቀቅ ሊራዘም ይችላል።

እስካሁን የቴሌቪዥን ጣቢያው ቢሮ መዘጋትን በተመለከተ ከእስራኤል በኩል በይፋ የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

ባለፈው ግንቦት ወር በናዝሬት እና በወረራ ሥር በምትገኘው ምሥራቅ ኢሩሳሌም ውስጥ በሚገኙት የአልጄዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሮዎች ላይ በተለያየ ጊዜ በእስራኤል ኃይሎች ወረራ ተፈጽሞባቸው ነበረ።