አንቶኒን ፓኔንካ

ከ 8 ሰአት በፊት

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ሽርሽር ለመሄድ ጓጉተዋል።

በአውሮፓውያኑ 1976 የተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ይሄዳል ብሎ ማንም አልጠበቀም።

የቀድሞው የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም በወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት የነበረችው ምዕራብ ጀርመን ቼኮዝሎቫኪያን እንደምትረታ የተጠራጠረ አልነበረም።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ያሳሰባቸው ዋንጫውን ካነሱ በኋላ የሚያደርጉት ሽርሽር ነው።

መጀመሪያ ዕቅዱ የነበረው ግጥሚያው አቻ ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀናት በኋላ ድጋሚ ይደረግ የሚል ነበር። ዌልሳዊው ዳኛ ክላይቭ ቶማስ ቶሎ ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ተነገራቸው።

ነገር ግን ጨዋታው ሊጀመር ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት አዲስ ሐሳብ መጣ።

“ጥያቄውን ያቀረበው የምዕራብ ጀመርን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነበር” ይላል አንቶኒን ፓኔንካ።

“ተጫዋቾቻችን ሽርሽር ወደሚሄዱበት ቦታ ሆቴል ይዘዋል ምናምን ምናምን. . . አሉን። ከሁለት ቀናት በኋላ ድጋሚ ከምንጫወት ለምን በፍፁም ቅጣት ምት አንለያይም የሚል ሐሳብ አመጡ።”

ለጨዋታው ዝቅተኛ ግምት የተሰጣት ዜኮዝሎቫኪያ ሁለተኛ ጨዋታ ከማካሄድ ይልቅ በፍፁም ቅጣት የተሻለ ዕድል እንዳላት ታውቃለች። ቡድኖቹ ተስማሙ።

ጨዋታ አቀጣጣይ የሆነው ፓኔንካ ለፍፁም ቅጣት ምት የሚሆን ዕቅዳ በሐሳቡ ይነድፍ ጀመር።

ይህን ንድፍ ሲያወጣ ሲያወርድ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ የፍፁም ቅጣት ምት አመታት ታዋቂ እና አጨቃጫቂ፣ ጀግና እና ጠላት እንደሚያደርገው አልተጠራጠረም። ተሳካም አልተሳካም አከራካሪ እንደሚሆን አሳምሮ ያውቃል።

ፓኔንካ ታዋቂዋን ፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር

ፓኔንካ በፕራግ ከተማ የቦሄሚያንስ ቡድን አማካይ ነበር። ከክለቡ በረኛ ጋር አንድ ልማድ ያዙ። ሁሌም ከልምምድ በኋላ ወደኋላ ቀርተው ይፎካከራሉ።

ፓኔንካ አምስት ፍፁም ቅጣት ምት ይመታል። አምስቱንም ማስቆጠር አለበት። በረኛው ዝዴኔክ ህሩስካ ደግሞ አንድ ብቻ መመለስ ነው የሚጠበቅበት። የተሸነፈ ሰው ቢራ አሊያም ቼኮሌት ይጋብዛል።

“ሁሌም እንደጋበዝኩት ነበር” ይላል ፓኔንካ።

“ሁሌም ከልምምድ በኋላ አዳዲስ የፍፁም ቅጣት ምት አመታቶችን እሞክራለሁ። ግብ ጠባቂው የኔን እንቅስቃሴ አይቶ ወደ አንዱ ጎን ይወድቃል። ለምን መሐል ላይ አልመታውም? ብዬ አሰብኩ።”

ፓኔንካ ሞከረው። ተሳካለት። ለወትሮው ፍፁም ቅጣት ምት ወይ ወደቀኝ አሊያም ወደ ግራ ነበር የሚመታው። ፓኔንካ ይህ አዲስ ‘ስታይል’ በልምምድ ሜዳ ብቻ እንዲቀር አልፈለገም።

መጀመሪያ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ሞከረው። ቀጥሎ ደግሞ የከተማው ተቀናቃኝ ቡድን የነበረው ዱክላ ፕራግ የተሰኘው ቡድን ላይ ሞክሮት ተሳካለት።

የፍፃሜው ጨዋታ ተጀመረ። ጀርመን 2፤ ቼኮስሎቫኪያ 2። ይሄኔ ነው ሁሉም ዓይኑን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ያደረገው።

ተራው የደረሰው ፓኔንካ ፈጠን ፈጠን እያለ ወደ ፍጽም ቅጣት ምት ሳጥኑ ይራመድ ጀመር። አንድ ሁለት ሦስት እርምጃ ወደኋላ ተስቦ አነጣጠረ። ወደ ቀኝ ወይስ ወደ ግራ?

ፓኔንካ ኳሷን በቅንጦት መልክ መሐል ለመሐል መትቷት ገና መረብ ሳትነካ እጆቹን ዘርግቶ ደስታውን መግለፅ ያዘ። የጀርመኑ በረኛ ከተጋደመበት ተነስቶ ሲመለከት ኳሷ መረቡን ታካለች። ፓኔንካም እጆቹን ያውለበልባል።

ፓኔንካ እና ማዬር
የምስሉ መግለጫ,ፓኔንካ እና ማዬር ለእርዳታ ማሰባሰቢያ ሲጫወቱ

“ማናችንም የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት መሆናችንን አላመንንም” ይላል ፓኔንካ።

የፕራግ ነዋሪዎች ነቅለው ወጡ። በሶቪዬት ኅብረት የተሰማረው ታንክ በአገሪቱ የነበረውን ኮሚዩኒዝም ለማዳከም የነበረውን ሙከራ ከደመሰሰ ከስምንት ዓመታት በኋላ ነው ይህ ደስታ የመጣው።

ፕራግ ስፕሪንግ ተብሎ ከሚጠራው ከዚህ ክስተት በኋላ ሰብሰብ ብሎ አደባባይ ላይ መውጣት ክልክል ነበር። ነገር ግን የቼኮዝሎቫኪያ ብሔራዊ ቡድን ዋንጫውን ይዞ ሲመጣ ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን ከመግለፅ ያገደው አልነበረም።

“ይህ ሁሉ ሕዝብ ነቅሎ ወጥቶ በፍቅር ይቀበለናል ብለን ጭራሽ አልጠበቅንም ነበር።”

የፓኔንካ ድፍረት የተሞላበት እና ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ፍፁም ቅጣት ምት የሰው ዓይን ውስጥ እንዲገባ አደረገው። ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ባለሥልጣናትም ትኩረታቸውን ሰጡት።

ቼኮዝሎቫኪያዎች በወቅቱ “ኖርማላይዜሽን” የተሰኘ ፕሮግራም ተጭኖባቸው ነበር። ማንም ሰው ወጣ ያለ ነገር እንዲያደርግ አይፈለግም። ከአውሮፓ ዋንጫ ከሦስት ወራት በፊት ነው አንድ የሮክ ባንድ አባላት በምሥጢራዊው ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት። ረዥም ፀጉር እና ፀረ-ባሕል የሆነ ግጥም ማሰማት የማይታሰብ ነው።

ከተለመደው የፍጹም ቅጣት ምት አመታት ወጣ ያለው የፓኔንካ ፍፁም ቅጣት ምት ዓይን ውስጥ የገባው ለዚህ ነበር።

ፓኔንካ ፍፁም ቅጣት ምቱን ማስቆጠሩ ጠቀመው። ባይሳካለት ኖሮ መጨረሻው የፋብሪካ አሊያም የማዕድን አውጪ ሆኖ ሠራተኛ መሆን ነበር።

በማስቆጠሩ ደግሞ ጠላት አፈራለት።

የጀርመኑ በረኛ ማዬር ሽንፈት አይወድም። ሽንፈትን የሚወድ አለ ባይባልም የእሱ ግን ይለያል። በዚያ ላይ ማሸነፍ ልምዱ ነው። የባየርን በረኛ ሆኖ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን በልቷል።

መሸነፉስ ይሁን፤ በዚያ መንገድ ተዋርዶ መሸነፉ ግን አንገብግቦታል። ፓኔንካ እና ማዬር ከዚህ ክስተት በኋላ ለ35 ዓመታት አላወሩም።

ነገር ግን ዓመታት ዓመታትን ሲወልዱ ጠባቸው በረደ። የፓኔንካን ስም የያዘችው የፍፁም ቅጣት ምት አመታት ታዋቂ ሆነች።

ዚነዲን ዚዳን በአውሮፓውያኑ 2006 የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጣሊያን ላይ ያስቆጠራት እንዲሁም በ2012 ጣሊያናዊው አንድሪያ ፒርሎ እንግሊዝ ላይ የተራቀቀባት የፍጹም ቅጣት ምት አመታት ፓኔንካ የሚረሱ አይደሉም።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሊዮኔል ሜሲ፣ ቲየሪ ሄንሪ፣ ኔይማር እና ዝላታን ኢብራሂሞቪችም ሞክረው ተሳክቶላቸዋል።

ፓኔንካ አንድ ጥያቄ ተጠየቀ። ድጋሚ ይህን ዕድል ብታገኝ እና በአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ለፍፁም ቅጣት ምት ብትደርስ፤ እንዴት ትመታለህ? ፓኔንካ ወይስ ሌላ? የሚል።

“እንዴ በደንብ ነው እንጂ የምደግመው። ሌላ ነገር የምሞክር አይመስለኝም” ሲል መልሷል።