በዓለማችን በርካታ ተከታዮች ያሉት ዩቲዩበሩ ሚስተር ቢስት

ከ 7 ሰአት በፊት

ግማሽ ቢሊዮን ተከታዮች ያሉት ሚስተር ቢስት በኢንተርኔት ዓለም ‘እጅግ መልካም’ ከሚባሉ ሰዎች መካከል ነው።

ጂሚ ዶናልድሰን በተባለ የመዝገብ ስሙ የሚታወቀው ሚስተር ቢስት ፕራይም ቪድዮ በተሰኘው የቪድዮ ማሠራጫ ላይ በቅርቡ በሚተላለፈው ‘ጌም ሾው’ ምክንያት ነው ክስ የቀረበበት።

የዚህ ‘ጌም ሾው’ ተሳታፊ የሆኑ አምስት ሴቶች ናቸው የሚስተር ቢስትን ኩባንያ እና የፕራይም ቪድዮ ባለቤት የሆነውን አማዞን የከሰሱት።

እስከ ዛሬ ከታዩ ‘የጌም ሾዎች’ በእጅጉ ትልቁ የተባለው እና አንድ ሺህ ተሳታፊዎች ያሉት ይህ ውድድር ለአሸናፊው 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይሰጣል። ነገር ግን በክሱ ምክንያት ይህ የቴሌቪዥን ዝግጅት ይሠራጫል ወይ የሚለው አጠያያቂ ሆኗል።

54 ገፆች ያሉት ይህ ክስ ለሚድያ ክፍት ያልሆኑ በርካታ ዓረፍተ-ነገሮችን የያዘ ቢሆንም፤ አምስቱ ሴት ከሳሾች በዝግጅቱ “ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚያይ እና ፆታን መሠረት ያደረገ መገለል ላለበት ሁኔታ ተጋልጠናል” ማለታቸው ተመልክቷል።

በዚህ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ሰዎች “በቂ ምግብ አልተሰጣቸውም እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ እንዲሠሩ ተደርጓል” የሚል ክስም ሰፍሯል።

በአብዛኛው ለሕዝብ ይፋ ባልሆነው በዚህ ክስ ላይ ከሳሾቹ “ለወሲባዊ ትንኮሳ እና ለከፋ የሥራ ሁኔታ” ተጋልጠናል ሲሉ የሚስተር ቢስት ኩባንያን እና አማዞንን ከሰዋል።

ባለፈው ነሐሴ ወር ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በርከት ያሉ ያልተለቀቀው ጌም ሾው ላይ የተሳተፉ ሰዎችን አናግሮ ዘገባ የሠራ ሲሆን፣ አንድ ግለሰብ ለ20 ሰዓታት ያክል ምንም ምግብ ሳይቀምስ መቆየቱን በመጥቀስ ቅሬታውን ለጋዜጣው ተናግሯል።

የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በውድድሩ ወቅት በሚገባው ሰዓት የሕክምና አገልግሎት አልተሰጠንም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሚስተር ቢስት

ክሱ የታዋቂውን ‘ዩቲዩበር’ ስም ያጎድፈው ይሆን?

እርግጥ ነው ሚስተር ቢስት በሥራዎቹ አሁን ለቀረበበት ክስ እና ለመሰል ቅሬታዎች እንዲሁም ወቀሳዎች አዲስ አይደለም።

ከዩቲዩብ በሚያገኘው ገንዘብ በመላው ዓለም እየተዘዋወረ በጎ ሥራዎችን በመሥራቱም ትችት ገጥሞት ነበር።

በለተይ ደግሞ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ንፁህ ውሃ የሚያወጣ መሣሪያ በመግጠሙ እንዲሁም መስማት ለተሳናቸው እና ለዓይነ ስውራን የቀዶ ህክምና ወጪን በመሸፈኑ ያደነቁት ቢኖሩም የወቀሱትም አልጠፉም።

ነገር ግን የሚስተር ቢስት ተፅዕኖ እየሰፋ እንጂ እየኮሰመነ አልመጣም። ከዩቲዩብ እና ከሌሎች መድረኮች የሚያገኘው ገቢም እየጨመረ ነው።

ኔትፍሊክስ በተሰኘው የፊልም ማሠራጫ ጣቢያ የተላለፈው ታዋቂው ‘ስኩዊድ ጌም’ የተባለ ተከታታይ ድራማ ላይ ተመሥርቶ የሠራው ‘ጌም ሾው’ በዩቲዩብ ገፁ 652 ሚሊዮን ጊዜ ታይቶለታል። በዚህ ጌም ሾው በጠቅላላው ለሽልማት የቀረበው ገንዘብ 456 ሺህ ዶላር ነው።

ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የሚያደርገው በጎ ሥራ ብዙ ትችት ሲገጥመው አይታይም። ለምሳሌ ለሰዎች መኖሪያ ቤት፣ መኪና እና ጥሬ ገንዘብ ሲሰጥ ይታያል። ይህን ተከትሎ ነው የኢንተርኔት ‘መልካሙ ሰው’ የተሰኘ ቅፅል ስም የተሰጠው።

አሁንም በርካታ ሰዎች ወደ ተለያዩ የማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ እየጎረፉ እየተከተሉት ነው። በዚህም ምክንያትም በዓለማችን በርካታ ሰዎች የሚከተሉት የዩቲዩብ ቻናል ያለው ግለሰብ ለመሆን ችሏል።

ሶሻልብሌድ የተባለው የበይነ መረብ መረጃ ሰብሳቢ ድርጅት እንደሚለው ሚስተር ቢስት ባለፉት 30 ቀናት ብቻ 5 ሚሊዮን የዩቲዩብ ሰብስክራይበሮችን አግኝቷል።

በርካታ ተከታዮች ያሏቸው ዩቲዩበሮች እንዲሁ በተመሳሳይ አወዛጋቢ ድርጊት ሲፈፅሙ ቢገኙም አብዛኛዎቹ በይፋ ይቅርታ ጠይቀው ሥራቸውን ሲቀጥሉ ታይተዋል።

ለዚህም ነው ዩቲዩበሮች በፍጥነት ይቅርታ የሚደርግላቸው የሚባለው። ነገር ግን ሚስተር ቢስት በዚህ ክስ ምክንያት ምን ሊገጥመው እንደሚችል አይታወቅም።