ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,ትራምፕ ከካማላ ሃሪስ ጋር ሁለተኛ ዙር ክርክር እንደማያደርጉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል

ከ 7 ሰአት በፊት

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ጋር ሁለተኛ ዙር የቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ለማድረግ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ።

ጥቅምት አጋማሽ ላይ ሲኤንኤን ቴሌቪዥን ሊያካሂድ ያቀደውን የፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ሁለተኛ ዙር ክርክር ካማላ ሃሪስ ሲቀበሉት፣ ትራምፕ ግን ክርክር ለማድረግ “ጊዜው በጣም ረፍዷል” በማለት በክርክሩ እንደማይሳታፉ ለደጋፊዎቻቸው ገልጸዋል።

ትራምፕ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፊላዴልፊያ ውስጥ በተካሄደው ክርክር አሸናፊ ነኝ ብለው ከተናገሩ፣ የቀረበላቸውን የሁለተኛ ዙር የምርጫ ክርክርን መቀበል ይገባቸዋል ሲሉ የካማላ ሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት ጥሪ አቅርበዋል።

ነገር ግን ቀደም ካለው ክርክር በኋላ የተደረጉ የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች እንዳመለከቱት ክርክሩን የተከታተሉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የበላይነት አግኝተዋል ብለው ያምናሉ።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ዊልሚንግተን፣ ኖርዝ ካሮላይና ውስጥ ባካሄዱት የምርጫ ቅስቀሳ በቀደመው ክርክር የበላይ መሆናቸውን በመጥቀስ አሁን ሌላ ዙር ክርክር ለማድረግ ረፍዷል ብለዋል።

“ድምፅ መስጠት ተጀምሯል” ያሉት ትራምፕ፣ ሃሪስ “ሌላ ዙር ክርክር ለማድረግ የፈለገችው” በቀደመው ክርክር ላይ “ክፉኛ በመሸነፏ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የካማላ ሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ ጠቅላላ ምርጫ ታሪክ ዕጩዎች አንድ ጊዜ ብቻ ክርክር ማድረጋቸው ያልተለመደ በመሆኑ፤ ሊካሄድ የሳምንታት ጊዜ ከቀረው ምርጫ በፊት የአሜሪካ ሕዝብ የሃሪስ እና የትራምፕ ክርክርን የሚመለከትበት “ሌላ ዕድል ሊሰጠው ይገባል” ብሏል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ በኤክስ ገጻቸው ላይ ለክርክር የቀረበላቸውን ግብዣ “በደስታ” እንደተቀበሉት እና ትራምፕም የሲኤንኤን ጥሪን ተቀብለው እንደሚሳተፉ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው ነበረ።

ሁለቱ ዕጩዎች ቀደም ባለው ክርክር ወቅት የተካሰሱ ሲሆን፣ ትራምፕ ሃሪስን “ጽንፈኛ ግራ ዘመም” እና “አሜሪካንን ለማውደም የተነሳች ማርክሲስት” ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ሲኤንኤን ባለፈው ሰኔ ወር የዲሞክራቶች ዕጩ በነበሩት በፕሬዝዳንት ባይደን እና በትራምፕ መካከል የተካሄደ ክርክርን ያስተናገደ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በሃሪስ እና በትራምፕ መካከል ተመሳሳይ ክርክር ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም. ለማድረግ አቅዶ ነበር።

በተለይ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ከምርጫ ፉክክሩ ከወጡ በኋላ ድምጻቸውን ለማን እንደሚሰጡ ያልወሰኑ አሜሪካውያን በዕጩዎች መካከል ሌላ ዙር የምርጫ ክርክር እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ሲዘገብ ቆይቷል።

እስካሁን ባለው የቅስቀሳ ሂደት ካማላ ሃሪስ በትራምፕ ላይ ጠባብ የበላይነት እንዳለቸው በብሔራዊ ደረጃ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ያመለክታል።

ከስድስት ሳምንታት በኋላ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ከባድ ፉክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በቀሩት ሳምንታት ውስጥ ሁለቱ ዕጩ ፕሬዝዳንቶች በይፋ ድጋፋቸውን ከገለጹላቸው መራጮች ባሻገር ድምጻቸውን ለማን እደሚሰጡ ያልወሰኑ መራጮችን ለመማረክ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በተለይም ቁልፍ በሆኑት ውስጥ ወሳኝ የሆነውን ቅስቃሳ ኣካሂዳሉ።