አብርሃም ሊንከን እና ዶናልድ ትራምፕ

ከ 8 ሰአት በፊት

ከጆርጅ ዋሽንግተን እስከ ጆ ባይደን 46 ፕሬዝዳንቶች የተፈራረቁባት አሜሪካ ጥቂቶቹ በሥልጣን ላይ እያሉ ተገድለውባታል። ጥቂቶቹ ደግሞ ከግድያ ሙከራ ተርፈዋል።

ከዛሬ 160 ዓመት በፊት አብርሃም ሊንከን በሰው እጅ ተገድለዋል። ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ደግሞ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተወዳደሩ ያሉት ትራምፕ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች ገጥሟቸዋል።

ከጥቂት ወራት በኋላ የሪፐብሊካኖች ዕጩው ሆነው ድጋሚ ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተፎካከሩ ያሉት ትራምፕ በሁለት ወራት ውስጥ ሁለት የግድያ ሙከራ ተቃጥቶባቸዋል።

በጀመሪያው የግድያ ሙከራ ለጭንቅላታቸው የተተኮሰው ጥይት ጆሯቸውን አቁስሎ “በተዓምር ከሞት ተርፌያለሁ” ብለዋል።

ከዚህ ክስተት 64 ቀናት በኋላ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ከሌላ አድፍጦ ጥቃት ሊፈጽማባቸው ከነበረ አጥቂ በጠባቂዎቻቸው መትረፋቸው ተዘግቧል።

ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት በፕሬዝዳንትነት መንበር ላይ ሳሉ ይህ ክሰተት ባያጋጥማቸውም፤ በርካታ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በሥልጣን ላይ እያሉ ወይ ተገድለዋል ወይም የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።

ከአብርሃም ሊንከን እስከ ዶናልድ ትራምፕ የተፈፀሙ ግድያዎችን እና ተቃጡ የግድያ ሙከራዎችን እንመልከት።

አብርሃም ሊንከን – ግድያ፡ 1857 ዓ.ም

መሳሪያ አቀባብሎ የተኮሰባቸው ተዋናይ ነው። የተተኮሰባቸው ደግሞ ቲያትር ቤት ውስጥ ሳሉ ነበር። አብርሃም ሊንከን አስቂኝ ዘውግ ያለው ትዕይንት ለመመከት በተገኙበት ስፍራ አሜሪካውያንን መሪር ሐዘን ላይ በጣለ ክስተት ክፉኛ ቆስለው ከቲያትር ቤቱ ወጥቷል።

ከጥብቅና ሙያ ተነስተው ወደ ፖለቲካ የገቡት አብርሃም ሊንከን በተገደሉበት ወቅት 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ።

ከአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ አሸናፊውን የአንድነት ኃይል የመሩት ሊንከን፣ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው የቀረቡት በ1853 ዓ.ም ነበር።

160ኛ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ወራት የቀሩት ይህ ክስተት ዓርብ መጋቢት 9/1957 ነበር የተፈጸመው። ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው “ፎርድ” በተሰኘው ቲያትር ቤት ጆን ዊልከስ ቡዝ የተባለው ታዋቂ ተዋናይ እና የኮንፌዴሬሽን ደጋፊ ፕሬዝዳንቱ ወደ ተቀመጡበት መከለያ (ሳጥን) ገብቶ ጭንቅላታቸው ላይ ተኩሶባቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ማለዳ ሕይታቸው አልፏል።

ይህ ከሆነ ከ12 ቀናት በኋላ ገዳያቸው ቡዝ፣ ቨርጂንያ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ተይዞ ተገድሏል።

ሊንከን ከተፈፀመባቸው ግድያ አራት ዓመታት በፊት ከግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር። ያኔ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ዳግም የተመረጡት ሊንከን ቃለ መሃላ ለመፈጸም እየተጓዙ ሳለ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው ነበር ግድያው የተቃጣባቸው።

አብረሃም ሊንከን
የምስሉ መግለጫ,ቲያትር ቤት ሳሉ በተፈጸመባቸው ጥቃት የተገደሉት አብረሃም ሊንከን

ጄምስ ጋርፊልድ – ግድያ፡ 1874 ዓ.ም

ጋርፊልድ 20ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ነበሩ። ሆኖም በተፈፀመባቸው ግድያ ምክንያት በሥልጣን የቆዩት ለ200 ቀናት ብቻ ነበር።

ጋርፊልድ በአሜሪካ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለዘጠኝ የሥራ ዘመናት ቆይተዋል። ከዚያም ወደ ዋይት ሐውስ አመሩ።

ሆኖም በሥልጣን መንበራቸው ላይ ብዙም ሳይቆዩ ቅዳሜ፣ ሰኔ 26/1874 ዓ.ም. እንደተገደሉ ዋይት ሐውስ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። ይህ ከሆነ 143 ዓመታት ተቆጥረዋል።

የዚያች መጥፎ ዕለት ያቄመባቸው ዐቃቤ ሕግ ነው ዋሽንግተን ዲሲ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ሆድ እና ትከሻቸው ላይ ተኩሶ ለሞት ያበቃቸው።

ቻርልስ ጊቶ የተባለው ግለሰብ በፕሬዝዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አስተዋጽኦ እንደነበረው በመግለጽ ሥልጣን ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም ነበር። በዚህም ምክንያት ፕሬዝዳንቱ ላይ ተኩሷል። ግለሰቡ የአዕምሮ ጤና እክል ገጥሞት እንደነበር የጻፉም አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከሁለት ወር በላይ በህክምና ሲረዱ ቢቆዩም መትረፍ ግን አልቻሉም።

በህክምናው ወቅት ስልክን የፈጠረው አሌክሳንደር ግርሃም ቤል ከፕሬዝዳንቱ ሰውነት ውስጥ ጥይቶቹን ለማውጣት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ ዋይት ሐውስ መዝግቧል።

መስከረም 10/1874 ዓ.ም. ሕይወታቸው አልፏል። ገዳያቸው በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በስቅላት ተቀጥቷል።

ዊልያም ሜክንሊይ – ግድያ፡ 1894 ዓ.ም

ሜክንሊይ በፈረንጆቹ 1901 ሲገደሉ 25ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ። እጅ ለመንሳት አስመስሎ የቀረባቸው ሊዮን ቾጎዝ በተኮሰባቸው ሁለት ጥይት እንደተገደሉ የዋይት ሐውስ ድረ ገጽ አስፍሯል።

ቾጎዝ የያኔው ፕሬዝዳንት ጨቋኝ ነበሩ ብሎ ያምን ነበር። በዚህ ምክንያት ግድያውን እንደፈጸመ ይታመናል።

ግለሰቡ ፕሬዝዳንቱን ‘ፓን አሜሪካን’ የተባለ መድረክ ለመታደም እየገቡ ሳሉ የተኮሰባቸው ሲሆን፣ ከ8 ቀናት በኋላ መስከረም 4/1894 ሕይታቸው አልፏል።

ይህ ከመሆኑ በፊት ፕሬዝዳንቱ እያገገሙ ነው የሚል ከፍ ያለ ተስፋ የነበረ ቢሆንም፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ የጤናቸው ሁኔታ አሽቆልቁሎ ሕይወታቸው አልፏል።

ገደያቸው በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፣ በፈጸመው ድርጊት ጸጸት እንደማይሰማው ገልጿል።

ለፈጸመው የግድያ ወንጀልም በኤለክትሪክ ወንበር የሞት ቅጣት ተፈጽሞበታል።

ኬኔዲ የተገደሉበት ጥቃት ከመፈጸሙ ከአጭር ጊዜ በፊት
የምስሉ መግለጫ,ኬኔዲ የተገደሉበት ጥቃት ከመፈጸሙ ከአጭር ጊዜ በፊት

ጆን ኤፍ ኬኔዲ – ግድያ፡ 1956 ዓ.ም

ኬኔዲ ኅዳር 12/1956 በክፍት ተሽከርካሪ በቴክሳስ ዳላስ ጓዳና ላይ ሳሉ ነበር ቀትር 6 ላይ በተተኮሱባቸው 2 ጥይቶች ሕይወታቸው አልፏል።

የተተኩሰባቸው ጥይቶች ጭንቅላት እና ጀርባቸው ላይ ያረፉ ሲሆን፣ ከአንድ ሰዓት በታች በሆነ ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸው እንዲያለፍ ምክንያት ሆኗል።

በ35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ግድያ ዙሪያ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መጽሐፍት፣ ዘጋቢ ፊልሞች፣ ፖድካሳት እና ፊልም ቢሰራም የኬኔዲ ግድያ ግልጥ ያለ ነገር እስካሁን የለውም።

በርካታ መላምቶች እና የሴራ ትንታኔዎች ቢቀርቡም የፕሬዝዳንቱን ግድያ ምሥጢር አልገለጹም።

ከግድያው አንድ ዓመት በኋላ አጣሪ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው መረጃ ያኔ በስፋት ሲወራ የነበረውን አሉባልታ ውድቅ አድርጓል።

አሉባልታው ከኬነዲ ግድያ ጀርባ ሶቪየት ኅብረት አለች የሚል ነበር።

ከግድያው ጥቂት ቆይታ በኋላ ሊ ሃቫሪ ኦስዋልድ የተባለ ከሶቪየት ኅብረት የሸሸ እና በዳላስ የሚኖር ባሕረኛ ተጠርጥሮ ተይዟል። መርማሪ ኮሚሽኑ ግለሰቡ ማንም ተልዕኮ ሳይሰጠው በራሱ ተነሳሽነት ግድያውን እንደፈጸመ ደምድሟል።

ይህንን ድምዳሜ ቸል ብለው አሁንም ድረስ የራሳቸውን መላምት እና የሴራ ትንታኔ የሚሰጡ በርካቶች ናቸው። የሆነ ሆኖ ተጠርጣሪው ከአንድ እስር ቤት ወደ ሌላ ሲሸጋገር በአንድ የፖሊስ መኮንን ተገድሏል።

ሮናልድ ሬገን ላይ የግድያ ሙከራ በተደረገበት ጊዜ
የምስሉ መግለጫ,ሮናልድ ሬገን ላይ የግድያ ሙከራ በተደረገበት ጊዜ

ሮናልድ ሬገን – የግድያ ሙከራ፡ 1973 ዓ.ም

ሬጋን 40ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ። መጋቢት 21/1973 ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ሂልተን ሆቴል እየወጡ ሳለ በተተኮሰባቸው ጥይት ደረታቸው አከባቢ ተመተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከ43 ዓመታት በፊት የግድያ ሙከራ የተቃጣባቸው ገና ቢሯቸውን እንኳን በቅጡ ሳይለምዱት ነበር።

ፕሬዝዳንት በሆኑ በ69ኛው ቀን ጆን ሂንክሊ በተባለ ግለሰብ የተኮሰባቸው ጥይት ከሞት መለስ ከፍተኛ ጉዳት እና ስቃይ አደርሶባቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ለ12 ቀናት ህክምና ከተደረገለቸው በኋላ አገግመዋል። ከዚያ በኋላ ሬገን እስከ 1981 ዓ.ም. ለሁለት የሥልጣን ዘመን አሜሪካን መርተዋል። በ1996 ዓ.ም. በ93 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።

የግድያ ሙከራውን ያደረገው ጆን ሂንክሊ የአዕምሮ ጤና መታወክ እንዳለበት ስለተረጋገጠ በነጻ ተለቋል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ዶናልድ ትራምፕ

ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ፡ 2016 እና 2017 ዓ.ም

የአሁኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወራት ልዩነት ውስጥ ሁለት የግድያ ሙከራዎች ተቃጥቶባቸዋል።

ሐምሌ 8/2016 ዓ.ም. ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ በነበረበት መድረክ ላይ ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተባለ የ20 ዓመት ወጣት ተኩሶ አቁስሏቸዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንትን ጆሯቸው ላይ ተኩሶ ያቆሰላቸው ወጣት ከትራምፕ ጠባቂዎች በተተኮሰ ጥይት በስፍራው ተገድሏል።

ክሩክስ ነዋሪነቱ እዚያው ፔንሲልቬኒያ ውስጥ በትራምፕ ላይ የመግደል ሙከራ ካደረገበት 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቤቴል ፓርክ ነዋሪ ነበር።

45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካዋ ፔንስልቬኒያ ግዛት ከደጋፊዎቻቸው ፊት ቆመው የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር እያደረጉ ሳለ ነበር የተተኮባቸው።

ይህ ከሆነ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ትራምፕ እሁድ መስከረም 5/2017 ዓ.ም. ሌላ የግድያ ሙከራ እንደተቃጣባቸው በስፋት ተዘግቧል።

ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኘው የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ ላይ ሳሉ የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ ቡድን (ሲክሬት ሰርቪስ) ባልደረቦች አንድ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ ተመልክተው ተኩስ እንደከፈቱበት ተናግረዋል።

ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ተጠርጣሪው ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን ተቆርቋሪ ነበር። ራያን ሩት ይህ ግለሰብ የውጭ ተዋጊዎች ለዩክሬን ተሰልፈው ሩሲያን እንዲወጉ ይወተውት ነበር ተብሏል።

አሁን በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ነው።

ሌሎች የግድያ ሙከራዎች

ቢል ክሊንተን – የግድያ ሙከራ (1987 ዓ.ም) ፡ ፍራንሲስኮ ማርቲን ዱራን የተባለ ወንጀለኛ 42ኛውን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ላይ የግድያ ሙከራ ፈጽሟል።

ጥቃት ፈጻሚው ጥቅምት 1987 ዓ.ም. ፕሬዝዳንቱ ዋይት ሐውስ ውስጥ ሳሉ በታጠቀው ጠመንጃ በተደጋጋሚ ቢተኩስባቸውም አንዱም ጥይት ሳያገኛቸው ተርፈዋል።

ዱራን በፕሬዝዳንት ክሊንተን ላይ ለፈጸመው የግድያ ሙከራው 40 ዓመት ተፈርዶበታል።

ጆርጅ ደብሊው ቡሽ – የግድያ ሙከራ (1997 ዓ.ም)፡ ክሊንተንን የተኩት 43ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ግንቦት 2/1997 ዓ.ም. የግድያ ሙከራ ተቃጥቶባቸው ነበር።

ቭላድሚር አሩትዩኒየን የተባለ የጆርጂያ ዜግነት ያለው ግለሰብ በጆርጂያ ዋና ከተማ ቲብሊሲ ከተማ ውስጥ ቡሽ ንግግር እያደረጉ ሳለ ፈንጂ ወርውሮ ለመግደል ሙክሯል። ነገር ግን በጥቃቱ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረሰም።

ግለሰቡ በዚህ ድርጊቱም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።