በሄዝቦላህ ጥቃት የደረሱ አደጋዎችን የሚያሳዩ ቪድዮዎች በማኅበራዊ ሚድያ ተለጥፈዋል

ከ 6 ሰአት በፊት

ኢንዱስትሪያዊ እና ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ “በርካታ” የሄዝቦላህ ሮኬቶች ቅዳሜ ሌሊት ወደ ሰሜናዊ እስራኤል መተኮሳቸውን የእስራኤል ጦር ሠራዊት አስታወቀ።

ከ105 ሮኬቶች መካከል አብዛኞቹ መክሸፋቸውን ያስታወቀው ጦሩ፤ ነገር ግን አንዳንድ ቤቶች በጥቃቱ መመታቸውን ገልጿል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳለው በጥቃቱ ምክንያት የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሎች ሌሊቱን ሙሉ ሲጮሁ ነው ያደሩት።

ሄዝቦላህ ባለፈው ሳምንት ሊባኖስ ውስጥ ለደረሱት የፔጀር እና ዎኪ ቶኪ የግንኙነት መሳሪያዎች ፍንዳታ ጥቃቶች ምላሽ በሚል በደርዘን የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ተኩሷል።

እስራኤል በበኩሏ ሊባኖስ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ባደረስኩት ጥቃት ነባር የሚባሉ የሄዝቦላህ አዛዦችን ገድያለሁ ብላለች። ሊባኖስ ደግሞ ሦስት ሕፃናትን ጨምሮ 37 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቃለች።

ቢቢሲ ማጣራት ያላካሄደባቸው ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የተለቀቁ ቪድዮዎች ሀይፋ ተብሎ በሚታወቀው የእስራኤል አካባቢ በሄዝቦላህ ሮኬት ጥቃት ምክንያት የእሳት ቃጠሎ መነሳቱን ያሳያሉ።

“ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ግዛት ጥቃት ሊሰነዝር መሆኑን ተከትሎ” ቅዳሜ ዕለት በደርዘን የሚቆጠሩ ተዋጊ ጄቶች በደቡባዊ ሊባኖስ “ከፍተኛ” ጥቃት አድርሰዋል ሲሉ የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ቃል-አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሀጋሪ ተናግረዋል።

ቅዳሜ ሌሊት ከፈጸመው ጥቃት በፊት የእስራኤል መከላከያ ኃይል “180 የሚሆኑ ወታደራዊ ማዕከላትን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን” ማውደሙ ተገልጿል።

በተገባደደው ሳምንት መባቻ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የሚጠቀምባቸው ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ የተባሉ የመገናኛ መሳሪያዎች ፈንድተው 39 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ሐሙስ ዕለት መግለጫ የሰጡት የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን የወቀሱ ሲሆን “ቀይ መስመር የተላለፈውን” ጥቃት ለመበቀል “ፍትሐዊ ምላሽ” እንደሚሰጡ ዝተው ነበር።

እስራኤል እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት አልወሰደችም።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ ቮከር ተርክ በፔጀር እና ዎኪ እና ቶኪ ምክንያት የደረሱት ጥቃቶች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን የጣሱ ናቸው ብለዋል።

እሑድ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኙ እና ከሊባኖስ ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ እንዲሁም ሌሎች ዕግዶችን ጥሏል።

በዚህ መመሪያ መሠረት ግልፅ በሆነ ቦታ ከ10 ሰው በላይ መሰብሰብ እና ዝግ በሆኑ ሥፍራዎች ደግሞ ከ100 በላይ ሰዎች መሰብሰብ አይችሉም። ትምህርት ቤቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ሲነገራቸው ወደ ሥራ መሄድ የሚቻለው ደኅንነቱ የተጠበቀ ሲሆን ብቻ ነው መሆኑ ተነግሯል።

እነዚህ አዳዲስ መመሪያዎች ተግባራዊ የሚሆኑት በሀይፋ እና በሌሎች ሰሜናዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ነው።

በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ግጭት ወደለየለት ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት መጫሩን ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊባኖስ ለሚገኙ ዜጎቹ የጉዞ መመሪያ አውጥቷል።

ቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ሥራ ከማቋረጡ በፊት ዜጎች ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል። ኤምባሲው አክሎም “መቆየት የሚሹ ዜጎችን መርዳት ሊሳነው እንደሚችል” አስጠንቅቋል።

የጎረቤት አገር ጆርዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በተመሳሳይ ለዜጎቹ ባስተላላፈው ማስጠንቀቂያ በተቻላቸው መጠን በፍጥነት ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ሐማስ እስራኤል ላይ ካደረሰው ጥቃት በኋላ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል በድንበር አካባቢ ያለው ግጭት እየተባባሰ መጥቷል።