በጣሊያን የሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ነው ተብሎ የሚታመነው መግነዘ ጨርቅ
የምስሉ መግለጫ,በጣሊያን የሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ነው ተብሎ የሚታመነው መግነዘ ጨርቅ

ከ 8 ሰአት በፊት

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላ ተገንዞ የተቀበረበት እንደሆነ የሚታመን ጨርቅ ጣሊያን ውስጥ ይገኛል።

በጣሊያን የሚገኙ ተመራማሪዎች የመግነዘ ጨርቁ (የቱሪን ሽሮድ) ኢየሱስ ክርስቶስ በኖረበት ዘመን የተሠራ እንደሆነ በትክክል አረጋግጠናል ብለዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የታተመው ጥናታቸው መግነዘ ጨርቁ በመካከለኛው ዘመን የተሠራ እና ሐሰተኛ ነው የሚለውን እሳቤ ይሞግታል።

የተመራማሪዎቹ ጽሑፍ በከፍተኛ ሁኔታ በበይነ መረቦች የተጋራ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአሜሪካ እና የአየርላንድ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሰጥተውታል።

በዓለማችን ላይ የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በጣሊያን የሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶች መግነዘ ጨርቅ ወይም የቱሪን ሽሮድ እንዲሁም ቅዱስ ሽሮድ በመባል የሚታወቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ተገንዞ የተቀበረበት እንደሆነ ያምናሉ።

ይህ ከተልባ እግር ፈትል የተሠራው የኢየሱስ ክርስቶስ መግነዘ ጨርቅ በዓለም ላይ በቅርበት ከተጠኑ ታሪካዊ ቅርሶች አንዱ ነው።

የኢየሱስ መግነዘ ጨርቅ ታሪክ

የኢየሱስ ክርስቶስ መግነዘ ጨርቅ 4.42 ሜትር ርዝመት እንዲሁም 1.21 ሜትር ስፋት ያለው የተልባ እግር ጨርቅ ነው።

ጨርቁ በደም የቀለመ፣ ከኋላውም ከፊቱም ዓይኑ ሰርጎድ ያለ የአንድ ሰው አካል ምሥል በደብዛዛው መልኩ የታተመበት ነው።

አብዛኞቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች በጨርቁ ላይ በተዓምራዊ ሁኔታ የታተመው የኢየሱስ ክርስቶስ ገጽታ እና አካል ነው ብለው ያምናሉ።

በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅላቱ ወቅት የደረሰበት ቁስለቶች በተመሳሳይ መልኩ በዚህ መግነዘ ጨርቅ ላይ ያረፉትም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ።

እየሱስ ከመሰቀሉ በፊት በሮማ ወታደሮች የብረት ቁርጥራጮች እና የሾሉ አጥንቶች ባሉት ጅራፍ በተደጋጋሚ ተገርፏል።

በዚህም ጨርቅ ላይ በጀርባው ያረፉት የግርፋት ምልክቶች፣ መስቀሉን የተሸከመበት የሰውነት መብለዝ፣ እንዲሁም በጭንቅላቱ ላይ ያጠለቁለት የእሾህ አክሊል ያደረሰው መድማት እና መቁሰል እንደሚታዩም ያስረዳሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ከመስቀል አውርዶ በጨርቅ ጠቅልሎ ገንዞ የቀበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ እንደሆነ ያመለክታል።

 ከኢየሱስ ስቅለት ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው የተባሉት በመግነዘ ጨርቁ ላይ የሚታዩት አሻራዎች
የምስሉ መግለጫ,ከኢየሱስ ስቅለት ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው የተባሉት በመግነዘ ጨርቁ ላይ የሚታዩት አሻራዎች

በኢትዮጵያ በወንጌላውያን አማኞች ስም እየተበራከቱ የመጡት “ሐሰተኛ ነብያት እና ፓስተሮች”27 የካቲት 2023

ይህ መግነዘ ጨርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው በአውሮፓውያኑ 1350ዎቹ ሲሆን ጂኦፍሬይ ዲ ቻርኒይ የተባለ የጦር አበጋዝ በፈረንሳይ ምሥራቃዊ ክፍል ለምትገኝ ሊሬይ ለተባለች ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ በሰጠበት ወቅት ነው።

የጦር አበጋዙ የኢየሱስ ክርስቶስ መግነዘ ጨርቅ መሆኑንም በወቅቱ አውጆ ነበር።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 1389 ፒየር ዲ አርሲስ የተሰኙት የትሮይስ ጳጳስ ጨርቁ የኢየሱስ አይደለም ሐሰተኛ ነው ሲሉ ለመጀመሪያ ጊዜ አወግው ነበር።

ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1578 በጣሊያኗ ከተማ ቱሪን ወደሚገኘው ሳን ጂዮቫኒ ባቲስታ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን እንዲዛወር ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በክብረ በዓላት ጊዜ ብቻ በልዩ ሁኔታ ምዕመናን እንዲያዩት ይደረጋል።

በአውሮፓውያኑ 1988 ከስዊዘርላንድ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከአሜሪካ የመጡ ሳይንቲስቶች የመግነዘ ጨርቁ ቁራጭ ላይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ዕድሜ የሚወስነውን የራዲዮካርበን ምርመራዎች አደረጉ።

በዚህም ጨርቁ በአውሮፓውያኑ 1260 – 1390 መካከል ባለው ዕድሜ እንዳለው ድምዳሜ ሰጥተዋል።

የቅርብ ጊዜ ግኝቶችስ ምን ያሳያሉ?

የጣሊያን የብሔራዊ የምርምር ምክር ቤት አካል የሆነው የሞለኪውሎችን መዋቅር የሚያጠናው የአገሪቱ ክሪስታሎግራፊ ተቋም ሳይንቲስቶች መግነዘ ጨርቁ በተሠራበት በተልባ እግር ትናንሽ ክሮች ላይ ጥናት አድርገዋል።

ጨርቁ የተሠራበትን ዘመን ለማወቅ የኤክስሬይ (ጨረር) ቴክኖሎጂ ተጠቅመዋል።

የምርምሩ ውጤቶች ከሁለት ዓመት በፊት ሄሪቴጅ በተሰኘው ጆርናል ላይ ቢታተምም በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ እና በአየርላንድ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው በቅርቡ ነው።

ሳይንቲስቶቹ ጨርቁ የተሠራበትን ተልባ ሞለኪውሎች መዋቅር በዓመታት ውስጥ እንዴት እንደተቀየሩ እና እንደተሰባበሩ ለክተዋል።

ተመራማሪዎቹ የመግነዘ ጨርቁን ዕድሜ ለማወቅ ሌሎችን መለኪያዎችንም ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ጨርቁ የተቀመጠበትን የሙቀት እና የእርጥበት መጠን በመለካት ለዘመናት የነበረውን መጠን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

እነዚህን ሳይንሳዊ መለኪያዎች በመጠቀም ጨርቁ ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት ማለትም ኢየሱስ በኖረበት ዘመን አካባቢ እንደተሠራ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

እንደ ተልባ እግር ያሉ ጨርቆች የመበላሸት አዝማሚያ ስላላቸው ከራዲዮካርበን ምርመራ በበለጠ ሳይንቲስቶቹ የተጠቀሙባቸው የመለኪያ ዘዴዎች የበለጠ አስተማማኝ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ።

የኢየሱስ መግነዘ ጨርቅ (የቱሪን ሽሮድ) ሽመና ዓይነት በጥንት ጊዜ ይሠራ እንደነበር ጠቅሰው፣ በመካከለኛው ዘመን ነው የሚለውን እሳቤ ትክክል አይደለም ብለዋል።

በጣሊያን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው ተብሎ የሚታመነው መግነዝ ጨርቅ የተቀመጠበት ቤተ ክርስቲያን
የምስሉ መግለጫ,በጣሊያን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው ተብሎ የሚታመነው መግነዝ ጨርቅ የተቀመጠበት ቤተ ክርስቲያን

በመግነዘ ጨርቁ ላይ የሚነሳው ክርክር የት ይደርዳል?

የጣሊያናውያኑ ተመራማሪዎች መግነዘ ጨርቁ (የቱሪን ሽሮድ) ኢየሱስ ተገንዞ የተቀበረበት ጨርቅ ነው የሚለውን አልጠቆሙም።

ሳይንቲስቶቹ እያሉት ያለው መግነዘ ጨርቁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት በነበረበት ዘመን ነው የተሠራው ብቻ ነው ያሉት። ተመራማሪዎቹ አሁን የሠሩት ጥናት ስለ ቅርሱ ቀደም ሲል በተደረጉ ጥናቶች ላይ ተጨማሪ ሆኗል።

በመግነዘ ጨርቁ ላይ ከአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ጀምሮ 170 ያህል የምርምር ጥናቶች ታትመዋል። አብዛኞቹ የኢየሱስ እንደሆነ ሲያረጋግጡ ሌሎች ደግሞ ሐሰተኛ ነው ብለዋል።

የሮማው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መቀመጫ ቫቲካን ራሷ መግነዘ ጨርቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገንዞ የተቀበረበት ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳቧን በተደጋጋሚ ቀይራለች።