ሔለን ተስፋዬ

September 22, 2024

የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ሲያቀርቡ

መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር ካደረገ በኋላ፣ በሁሉም ደንበኞችና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርግ ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

ኩባንያው ይህንን ያስታወቀው ሐሙስ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የበጀት ዓመቱን ዕቅድ አስመልክቶ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡

መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር ከሆነ በኋላ ኩባንያው ወዲያውኑ ማሻሻያ ያላደረገው፣ ገበያው የተረጋጋና ጤናማ እንዲሆን በማሰብ መሆኑንና ዕቅዱን መከለስ አስፈላጊ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደተናገሩት፣ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ታሳቢ በማድረግ ሁሉም ደንበኞችና አገልግቶች ላይ ጭማሪ እንደማይደረግ፣ ነገር ግን የደንበኞችን የመክፈል አቅም በማገናዘብ በአንዳንድ አገልግሎቶችና በዝቅተኛ ተከፋዮች (የመግዛት አቅም በሌላቸው) ላይ ምንም ጭማሪ አይደረግም፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ያለበትን ወጪ በሚገባ በማስተዳደር፣ ወጪ ቆጣቢ የሆነ አሠራር በመከተልና የደንበኞችን የመክፈል አቅም ታሳቢ በማድረግ መጠነኛ የዋጋ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ሥራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ሳቢያ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የኩባንያው የሥራ ድርሻ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት ተገቢ አይደለም፤›› ሲሉ ሥራ አስፈጻሚዋ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡  

ነገር ግን በተወሰኑ ቦታዎች የአገልግሎት መቋረጥ መኖሩን፣ ተጠቃሚዎችን ወይም ደንበኞችን ለተፈጠረው አገልግሎት መቆራረጥ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

‹‹አገልግሎት ሲቋረጥ የተገዙ ፓኬጆችን ሳይጠቀሙ ለሚቀሩ ደንበኞቻችን ላልጠተቀሙበት አገልግሎት ምንም ዓይነት ክፍያ አናስከፍልም፤›› ብለዋል፡፡ ደንበኞች የገዙትን ፓኬጅ መጠቀማቸውና አለመጠቀማቸው ከተረጋገጠ በኋላ እንደሚመለስና ከዚህ ቀደምም መመለሱን አስረድተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን፣ ለዚህም ዓለም አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማስፋትና ተወዳዳሪ አገልግሎት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ሥራዎች ያከናውናል ብለዋል፡፡

በተለይ የዓለም አቀፍ አገልግሎትና የረሚታንስ (የሐዋላ) አገልግሎትን በማሻሻልና አጋሮችን በማስፋት፣ በ2017 በጀት ዓመት ከውጭ ምንዛሪ 282.85 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በማጎልበት በ2017 በጀት ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት ለመጠቀም መታሰቡን፣ በጀቱን ለማግኘት የተለያዩ የቢዝነስ ሞዴሎች ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ዋና ዋና የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን የታቀደ ሲሆን፣ ለሞባይል ኔትወርክ 1,298 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት መታሰቡን አክለዋል፡፡

የ4ጂ ኔትወርክ በ500 ከተሞች ማስፋፊያ እንደሚደረግ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ 15 ከተሞች የ5ጂ ኔትወርክ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአዲሱ ዓመት በነበረው የደንበኞች ጨዋታ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቹን መሸለሙን፣ ይህም አዳዲስ ደንበኞችን ለማግኘት በሚገባ ያገዘው እንደሆነ ገልጿል።

ኩባንያው ከተመሠረተ 130 ዓመታትን ማስቆጠሩን አስመልክቶ በተያዘው ዓመት ለስድስት ወራት የሚቆይ ‹‹ኢትዮ 130›› የተሰኘ ጨዋታ ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

ኩባንያው በስትራቴጂው የመጨረሻ ዓመት ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ተግባራት ላይ በሰጠው ማብራሪያ፣ በ2016 በጀት ዓመት የተገኘውን 93 ቢሊዮን ብር ገቢ በ74.7 በመቶ በማሳደግ 163.7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን ገልጿል፡፡

የደንበኞችን ብዛትንም በስድስት በመቶ በመጨመር 83 ሚሊዮን ለማድረስ፣  የሞባይል ደንበኞችን በ5.5 በመቶ በመጨመር 79.7 ሚሊዮን ለማድረስ፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በ16 በመቶ በመጨመር 47.4 ሚሊዮን ለማድረስ፣  የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኞችን በ25 በመቶ በመጨመር 934 ሺሕ ለማድረስ፣ በአጠቃላይ የቴሌኮም ሥርዓት መጠኑን 73 በመቶ ለማድረስ ማቀዱ ተጠቁሟል፡፡ 

ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ሊድ›› የተሰኘ የሦስት ዓመታት ስትራቴጂውን በ2015 በጀት ዓመት ማስተዋወቁ ይታወሳል። የ2017 በጀት ዓመት የስትራቴጂ ዘመኑ ሦስተኛ ዓመት ይሆናል ተብሏል።