ተመስገን ተጋፋው

September 22, 2024

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አማራጭ መፍትሔ ሳያዘጋጅና በቂ ጥናት ሳያካሂድ፣ ‹‹ከ30 ዓመት በላይ አገልግሎት የሰጡ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች፣ አገልግሎት እንዳይሰጡ›› ብሎ ውሳኔ ማስተላለፉ፣ አግባብነት የሌለውና ከትራንስፖርት ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚዊ ጥቅም የሚያሳጣ ነው ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቅሬታቸውን ያሰሙት ዓርብ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻዎች ጋር ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

የኅብረት ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ባይሳ አየለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የትንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ግልጽ የሆነ መመርያ ሳያወጣ፣ ለዓመታት አገልግሎት የሰጡ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ማለቱ አግባብነት የለውም፡፡

ሚኒስቴሩ በዋናነት እነዚህ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ያለበት ምክንያት፣ የአየር ብክለትን ለመከላከል አስቦ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አሠራር ሲዘረጋ የብድር አገልግሎትና ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡  

‹‹በኢትዮጵያ 60 በመቶ የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች ከ30 ዓመታትና ከዚያ በላይ አገልግሎት የሰጡ ናቸው፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ደግሞ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚቀጥሉት የሚለውን መንግሥት ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ጠለቅ ያለ ውይይት ማድረግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ለከባድ ተሽከርካሪዎች የሚሆን የመሠረተ ልማት በአግባቡ ሳይሟላ መንግሥት በፍጥነት ተሽከርካሪዎቹ ወደ ኤሌክትሪክ ይቀየሩ ማለቱ ትክክለኛ አካሄድ አለመሆኑን፣ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎቹ የማጓጓዝ አገልግሎት እንዳይሰጡ ፈቃድ በመከልከላቸው፣ እንዲቆሙ መገደዳቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ በብቃትና በጥንካሬ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አስተማማኝ አቅርቦት እስኪኖር ድረስ ተሽከርካሪዎቹ እንዲሠሩ መደረግ አለበት ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዓመታዊ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማደስ ጥያቄ ያቀረቡ አብዛኛዎቹ አክሲዮን ማኅበራት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች መግዛት ባለመቻላቸው ፈቃዳቸው አለመታደሱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም ምክንያት አክሲዮን ማኅበራቱ ለጭነት አገልግሎት ሥራ በማንኛውም ጨረታ እንዳይሳተፉ ስለሚከለከል ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ለመግዛት ያለው የአቅም ውስንነት ታሳቢ በማድረግ የጊዜ ገደብ እንዲራዘምላቸው መደረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡   

ከ30 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጡ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ፣ የተሻለ አሠራር እንዲፈጠርና የንብረቱ ባለቤቶችም ምቹ ሁኔታ እንዲያገኙ ፌዴሬሽኑ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘታቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡