ዮሐንስ አንበርብር

September 22, 2024

ተግባራዊ የሆነው ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራና ድርጅቱ ያሉበትን የንግድ ብድር ዕዳዎች ታሳቢ በማድረግ፣ መንግሥት የድርጅቱን ካፒታል ለማሳደግ መወሰኑ ተሰማ፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር መረጃ የጠየቃቸው የኢትዮጵያ ነዲጅ አቅራቢ ድርጅት ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ፀጋዬ፣ ‹‹መንግሥት የድርጅቱን ካፒታል ለማሳደግ ቃል ገብቷል፤›› ሲሉ አረጋግጠዋል።

ነገር ግን ጉዳዩ ገና ያልፀደቀና በዝግጅት ምዕራፍ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ መንግሥት የድርጅቱን ካፒታል በምን ያህል መጠን እንደሚያሳድገው አሁን ማወቅ እንደማይቻል ገልጸዋል።

መንግሥት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትን ካፒታል ለማሳደግ ያቀደው፣ ድርጅቱ ያሉበትን የንግድ ብድር ዕዳዎችና ከውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የሚመነጩ ኪሳራዎችን ማጣጣት በሚያስችል መልኩ ነው።

ይህንንም መንግሥት ለዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) አሳውቋል፡፡ መንግሥት ለዓለም የገንዘብ ድርጅት ባሳወቀው መሠረት፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. አንስቶ ተግባራዊ መሆን በጀመረው ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት የደረሰበት ኪሳራ፣ ድርጅቱ ያሉበትን የንግድ ብድር ዕዳዎችን አካቶ 120 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቷል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2012 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደ አዲስ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ በደንቡ የተደነገገው የድርጅቱ የተፈቀደ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ አምስት መቶ ሚሊዮን ብር ነው። ሪፖርተር የተመለከተው እ.ኤ.አ. የ2022 ኦዲት ሪፖርት ደግሞ ድርጅቱ 207 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ላሉት ሦስት ወራት የሚያስፈልገውን የነዳጅ ፍጆታ ድርጅቱ መፈጸም እንዲችል፣ በልዩ ሁኔታ በቀድሞው የውጭ ምንዛሪ ተመን 670 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጠው ፈቅዷል። ይህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል እንዲፈጸም በታዘዘው መሠረት ተግባራዊ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

‹‹በመንግሥት ቃል የተገባውን 670 ሚሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ እኛ የባንክ ሒሳብ አስተላልፎ ግዥ እየተፈጸመበት ነው፤›› ሲሉ፣ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኑነት ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

መንግሥት የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋን ለማረጋጋት ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 2021 ጀምሮ ማንሳቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን የጀመረው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ከፍኛ የዋጋ ንረትን እንዳይቀስቀስ በመሥጋት የነዳጅ ምርት ችርቻሮን ለመደጎም ተገዷል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት የሚያደርገው ድጎማ በየወሩ አምስት በመቶ የዋጋ ጭማሪን እንደሚያካትት፣ ድጎማውም እስከ ከአንድ ዓመት በላይ ሊዘልቅ እንደማይችል ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር ያደረገው ስምምነት ሰነድ ያስረዳል።