ዜና
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብ በድጋሚ ታገደ

ታምሩ ጽጌ

ቀን: September 22, 2024

በከሳሽ እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ (4 ሰዎች) የክስ አቤቱታ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ተረኛ ችሎት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሁሉም የባንክ ሒሳብና ኮሚቴው ያደረጋቸው የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔዎች እንዲታገዱ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ትዕዛዝ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

የፍርድ ቤቱ የዕግድ ትዕዛዝ ተከብሮ የቆየው ለአራት ቀናት ማለትም እስከ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ሲሆን፣ ዕግድ የተጣለበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ሁከት ተረኛ ችሎት፣ የይግባኝ አቤቱታውን መርምሮ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በሌላኛው ፍርድ ቤት በኮሚቴው ላይ ተጥሎ የነበረውን ዕግድ በማንሳት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

የሥር ፍርድ ቤቶች ዕግድ በመጣልና ዕግድ በማንሳት ያስተላለፉት ትዕዛዝ መቆየት የቻለው ለአራት ለአራት ቀናት ብቻ ነው፡፡

የክስ አቤቱታ ያቀረቡት እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ፣ የሥር ፍርድ ቤት መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. አንስቶት በነበረው የዕግድ ትዕዛዝ ላይ፣ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ብይንና ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የሥር ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ የሰጡትን ዕግድ የመጣልና ዕግድ የማንሳት ትዕዛዝ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሰጠው ትዕዛዝም፣ ከሳሾች እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ባቀረቡት የፍትሐ ብሔር የክስ አቤቱታ ማለትም፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 6 እና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕግንና መመርያን በጣሰ መንገድ ባደረገው ጉባዔ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች፣ ተጣርቶ የኦዲት ምርመራ እንዲደረግበት የቀረበውን ጥያቄ ለመደበቅና መረጃ ለማጥፋት መሆኑን በማብራራት፣ ውሳኔው እንዳይተገበርና ተቋሙ በሁሉም የንግድ ባንኮች ያለው ሒሳብ እንዲታገድ የቀረበውን አቤቱታ  መመርመሩን አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾች እነ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (5 ሰዎች) ያቀረቡትን ዕግድ ይነሳልን የክስ አቤቱታ ማለትም፣ ተቋሙ በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ቻርተርና ቻርተሩን ተከትሎ በፀደቀው የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፣ የተቋቋመና በመንግሥት የስፖርት ፖሊሲ መሠረት ስፖርቱን የሚመራና በመንግሥት ድጋፍ የሚተዳደር መሆኑን አብራርተው ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሯል፡፡ በማከልም በተቋሙ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተ የባንክ ሒሳብና ኮሚቴው ግንቦት 6 እና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ያስተላለፈው ውሳኔ ታግዶ ቢቆይ፣ የተቋሙን አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴዎችን የሚገድብና የተቋሙ ቢሮ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ የሚያደርግ መሆኑን ዘርዝረው ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ዕግድ ያስነሳበትን ትዕዛዝም፣ ይግባኝ ሰሚው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መርምሯል፡፡

ሁለቱ የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የተሰጠውን ዕግድና መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የተነሳውን የዕግድ ትዕዛዞችን የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ የተነሳውን ዕግድ እንደገና በማገድና ለሠራተኞች በፔሮል የሚከፈል የደመወዝ ወጪ እንዲደረግ በመፍቀድ፣ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የተሰጠው ‹‹ዕግዱ ይነሳ›› ትዕዛዝን በመሻር፣ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የተሰጠውን የዕግድ ትዕዛዝ አጽንቷል፡፡ የተከሳሾችን አስተያየት (ምላሽ) ለመስማት ለመስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡