የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው

ዜና ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ አትሚስን በተመለከተ ከአገሮች ጋር እንደምትመክር ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 22, 2024

ከሰሞኑ መካሄድ በጀመረው 79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን በተመለከተ ከአገሮች ጋር እንደምትመክር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በመሆን የተሾሙትና  በኢትዮጵያ የአልጄሪያ የቀድሞ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ሐሙስ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጉባዔው መሳተፍ አለመሳተፋቸውን የገለጹት ነገር የለም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደሚሳተፉ ግን አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ (አምባሳደር) የኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ጽሕፈት ቤት ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ከመስከረም 14 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ‹‹ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ሰላም ዘላቂ ልማትና ሰብዓዊ ክብር በጋራ መሥራት›› በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ቀጣይ ሥራዎችን በሚመለከት፣ ሠራዊት ከሚያዋጡ አገሮች ጋር የጎንዮሽ ውይይት ለማድረግ ዕቅድ መያዟን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉባዔ ለአትሚስ ሠራዊት የሚያዋጡ አገሮች በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ጂቡቲና ኬንያ የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ለመለዋወጥና ቀጣይ አቅጣጫ ምን ሊሆን ይችላል በሚለው ላይ ለመነጋገር፣ ከተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን፣ ከእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ በሚቀጥሉት ጊዜያት የሚኖሩትን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎችን ያሳውቃልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት መንገድ የሚከፍትላትን የመግባቢያ ስምምነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) እና በሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ መካከል ከተፈረመ በኋላ፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥት መካከል የፖለቲካ መካረር መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም ሶማሊያ ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ካደረገች በኋላ፣ የግብፅ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ማረፋቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅሜን አደጋ ላይ የሚጥሉ ኃይሎችን እያስጠለለች ነው በማለት ክስ አቅርባለች፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ወቅታዊው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ  የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከወትሮው ወጣ ብሎ በርካታ ጉዳዮች እየተነሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላምና በመረዳዳት በእጅጉ የተቆራኘን ስለሆንን፣ ጎረቤቶቻችን ሰላም ካልሆኑ ኢትዮጵያ ሰላም ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ፈታኝ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ ከዚያ ባለፈ የምታደርገው ዲፕሎማሲ የሰከነና መርህን መሠረት ያደረገ፣ ችግሮች ሲከሰቱ የጋራ መፍትሔ ላይ ያተኮረ ስለሆነ፣ በየጊዜው ከተለያዩ አካላት ለሚነሱ አስተያየቶችና ትንኮሳዎች እንካ ሰላንትያ ውስጥ መግባት አስፈላጊ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከሰሞኑ መስመር ለማሳት የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን ወደ ጎን በመተው፣ መፍትሔ ላይ ያተኮረና በበጎ መንፈስ የተቃኘ ዘላቂ ትብብርና ስትራቴጂያዊ ዕይታ ያለው ዲፕሎማሲ አበክረን እንከተላለን፤›› ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ከሰሞኑ ከአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ከኔት ዌብር፣ ከአሜሪካ የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ አና ቴቴ፣ እንዲሁም ከፈረንሣይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ ወዳጅነት ቡድን አባላት ጋር በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢኮኖሚም ሆነ በቁጥር እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ለመልዕክተኞቹ እንደገለጹላቸውና ይህንንም ፍላጎት በሰጥቶ መቀበል መርህና በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት እያደረገች ያለውን ጥረት ማብራራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ግብፅ ተጉዘው ባደረጉት ውይይት፣ ኢትዮጵያና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ እንዲነጋገሩ፣ ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን እንዳይጎዳ ከስምምነት እንዲደርሱ ከሁለቱም አገሮች ጋር መነጋገራቸውን መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በአፍሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ግብፅና አሜሪካ በትብብር እንደሚሠሩና አሜሪካ የግብፅን ሉዓላዊነት እንዲከበር እንደምትፈልግ መናገራቸው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በመግለጫቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትን በተመለከተ እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውሰው፣ አሁን ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጉርብትናና መልካም ወዳጅነትን መሠረት ያደረገ ዲፕሎማሲ የምታካሂድ በመሆኑ ሁኔታው በዚህ መንገድ ይቀጥላል ብለዋል፡፡