አቶ ብርሃኔ ዘሩ

ዜና ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ግብር ጥናትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ተጠየቀ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: September 22, 2024

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ ሲሄዱም ሆነ ከጂቡቲ ወደ ተለያዩ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች የሚጓዙ አሽከርካሪዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚከፍሉት ግብር ጥናትን መሠረት ያላደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

ከጂቡቲ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ጭነት  የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎች ለተለያዩ አገልግሎቶችና ለግዢዎች ለሚያወጧቸው ከፍተኛ ወጪዎች ሕጋዊ ደረሰኝ እንደማያገኙ እየታወቀ፣ ተመዛዛኝ የገቢና ወጪ መግለጫ ሰነድ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩ በተሽከርካሪ ባለንብረቶች መጉላላት ከመፍጠር ባሻገር እንደ አገርም ሰላማዊ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ጤናማ ፍሰትን ወደ ማስተጉጎል በማምራቱ፣ ፌዴሬሽኑ ለአባላቱ መብትና ለአገራዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ዕድገት ካለበት ኃላፊነት አንጻር ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች የሚጓጓዙ አሽከርካሪዎች በየአካባቢው ‹‹የኮቴ ክፈሉ›› ከመባላቸውም በዘለለ፣ ሰብዓዊ መብታቸው በየጊዜው እየተጣሰ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተለይም አሽከርካሪው ለዓመታት ከለመደው የቁርጥ ግብር ክፍያ አፈጻጸም ተላቆ፣ መመርያው በወጣ ማግስት ከተተበተበበት ኢመደበኛና ሰነድ አልባ አክሳሪ ወጪዎች ተፅዕኖ፣ በእመርታ ወጥቶ መመርያውን እንዲተገበር ጫና ከመፍጠር ይልቅ፣ ቁርጥ ግብር አከፋፈሉ ካለው የኢኮኖሚ ግሽበት አንጻር ሲከፈል የነበረው መጠን ተመዝኖና ተሰልቶ ማሻሻያ ተደርጎበት እንዲከፈል ለማድረግ ፌዴሬሽኑ ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ከጂቡቲ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች የሚጓዙ አሽከርካሪዎች፣ ትክክለኛ አሠራርን ተከትለው ግብር እንዲከፍሉ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን ቢያናግርም፣ መፍትሔ ሳያገኝ መቅረቱን አስርድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለመከላከያ ሠራዊቱ የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጡ አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች፣ እስካሁን ድረስ 100 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት እንደ መደበኛ ሥራ ያህል በማሰብ ከመከላከያ ጎን ተሰልፈው የሠሩበት፣ የአገልግሎት ክፍያ ዋጋ ተጣርቶ ከታወቀ በኋላ፣ ክፍያውን እንዲከፍሉ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም እስካሁን ክፍያው እንዳልተፈጸመላቸው አብራርተዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት አገራዊ ግዴታ ሲኖር የመከላከያ ሠራዊቱን በማመላለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የተወጡ የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ክፍያ ባለማግኘታቸው ምክንያት፣ ከሥራ ገበታቸው እየወጡ መሆኑን የፌዴሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ መኮንን እርቄ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በአዲስ አበባ መውጫ በር የሚገኙ መናኸሪያዎችን እንዲዘጉ በማድረግ፣ እንደ ግዴታ ለመከላከያ ሠራዊቱ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡