ዜና የደኅንነትና የመከላከያን ጨምሮ የበርካታ ተቋማት ዕቃዎች የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ እንዳይጣልባቸው መመርያ ወጣ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 22, 2024

የገንዘብ ሚኒስቴር ወደ አገር በሚገቡ ዕቃዎች ላይ በጣለው የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ለመወሰን የወጣ መመርያ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደኅንነት፣ የጤና፣ የትምህርትና የዕርዳታ ስጦታዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ወሰነ፡፡

በተያዘው የመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. የወጣውና የገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላለፈው መመርያ፣ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከቀረጥና ከታክስ ነፃ ሆነው ወደ አገር እንዲገቡ የተፈቀዱ ዕቃዎችን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ተቋማት፣ የብሔራዊ መረጃና ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሳንቲሞች፣ የገንዘብ ኖቶች፣ የብርና የወርቅ ጠገራዎች ከቀረጥ ነፃ ተደርገዋል ይላል፡፡

መመርያው ለኅብረተሰቡ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ለማስፋፋት፣ እንዲሁም በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት ከውጭ አገር በዕርዳታ የሚላኩ ዕቃዎችንም ይመለከታል፡፡ እነዚህ ዕቃዎች የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የተጣለበትን ዓላማ ለማሳካት የሚያግዙ በመሆናቸው ከቀረጥ ነፃ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ያሉ ወይም ለኅብረተሰቡ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ የሕፃናት፣ የሴቶችና የአረጋውያን የአዕምሮ ሕመምተኞችና የአካል ጉዳተኞች መርጃ ድርጅቶች ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ የተደረጉ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለሚሰጡ ድርጅቶች ከውጭ በዕርዳታ የሚላኩ ዕቃዎች ነፃ ተደርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ በመመርያው መሠረት ከስምንት መቀመጫ በላይ ያላቸው አውቶሞቢሎችና መለዋወጫዎች፣ ባለአንድ ወይም ባለሁለት ጋቢና ተሽከርካሪዎች፣ መለዋወጫቸው ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችና መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንደማይሆኑ በመመርያው ተደንግጓል፡፡

ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ አገር ለሚገቡ ዕቃዎች አስመጪዎቹ ማስረጃ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ማስረጃዎቹ ዕቃዎቹ በዕርዳታ የተገኙ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የዕርዳታ የምስክር ወረቀት፣ የዕቃዎችን ዝርዝርና ዋጋ የሚያሳይ ኢንቮይስ፣ ዕቃዎች ለተገለጸው ዓላማ የሚውሉ መሆኑናቸው ስለአጠቃቀማቸው ለጉምሩክ ኮሚሽንና ገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት የሚያቀርቡ እንደሆነ አግባብ ካለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተጻፈ የድጋፍ ደብዳቤ ይጠይቃሉ፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 519/2014 መሠረት ነፃ ከተደረጉ ዕቃዎች በስተቀር፣ በጉምሩክ ታሪክና ደንብ የተዘረዘሩት ማናቸውም ዕቃዎች ወደ አገር በሚገቡበት ጊዜ፣ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ሦስት በመቶ እንደሚከፈልባቸው ተደንግጓል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎች አምስት ዓይነት ቀረጦች ይከፈልባቸዋል። ከእነሱ መካከል የጉምሩክ ቀረጥ፣ የኤክሳይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ሱር ታክስና ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ ናቸው፡፡

ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሚሰበሰበው ገቢ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመጠገን በማስፋፋትና በማሻሻል የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታስቦ የሚሰበሰብ ነው፡፡