የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከግብፅ አቻቸው በድር አብደላቲ ጋር በካይሮ መግለጫ በሰጡበት ወቅት

ዜና ግብፅ በደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ልታሰማራ እንደምትችል ተነገረ

ዮናስ አማረ

ቀን: September 22, 2024

በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ጦር ለማስማራት እንቅስቃሴ የጀመረችው ግብፅ፣ በደቡብ ሱዳንም የሰላም አስከባሪ ልታሰማራ እንደምትችል ተነገረ፡፡

ከሰሞኑ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድር አብደላቲ ከአሜሪካ አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ጋር በጋራ ሆነው በሰጡት መግለጫ፣ ግብፅ እንደ ደቡብ ሱዳንና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመሳሰሉ አገሮች ሰላም አስከባሪ በማዋጣት ልትሳተፍ እንደምትችል ተናግረዋል፡፡

አንቶኒ ብሊንከን በካይሮ ባደረጉት ጉብኝት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የግብፅ ባለሥልጣናትን አግኝተው በቀጣናዊ ሰላምና በፀጥታ ትብብሮች ጉዳይ ላይ መምከራቸው ታውቋል፡፡ ከሊቢያ እስከ ጋዛ፣ ከሱዳን እስከ ሶማሊያ ጉዳዮች ግብፅ ገንቢ ሚና ልትጫወት እንደምትችል ሁለቱ ወገኖች መምከራቸው ነው የተሰማው፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ ባለፈ ሁቲዎች በቀይ ባህር የባብኤል መንደብ መተላለፊያ የፈጠሩትን ቀውስ በማስተካከል፣ ግብፅ ሚና እንዳላትም ብሊንከን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የፀጥታ ትብብሮችን ስለማጠናከር ጉዳይ መክረናል፡፡ ግብፅ እንደ ደቡብ ሱዳን፣ እንዲሁም ዴሞክራቲክ ኮንጎ ባሉ አገሮች ውስጥ ጦር በመላክ የሰላም ማስከበር ሚና ልትጫወት ትችል እንደሆነ መክረናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ የብሊንከን ንግግር ግብፅ በፀረ ሽብር ዘመቻና በሰላም ማስከበር ጉዳዮች ዋና የአሜሪካ አጋር እየሆነች መጥታለች የሚል ድምዳሜ እያሰጠ ነው፡፡

ብሊንከን ሰሞኑን ወደ ካይሮ ከማቅናታቸው በፊት፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለግብፅ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ለአንድ ዓመት መፍቀዱን ይፋ ማድረጉም ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ግብፅ በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፣ በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በኩል ለሚሰማራው ኃይል፣ የሰላም አስከባሪ ጦር እንደምታዋጣ ይፋ መደረጉም ይታወሳል፡፡ ግብፅ በሶማሊያ ታሰማራዋለች የተባለው ከአሥር ሺሕ በላይ ጦርም በዚያ ተልዕኮውን ጨርሶ ወደ አገሩ ተመላሽ እንደሚሆን የሚጠበቀውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ቦታ እንደሚተካ ሲነገርለት ቆይቷል፡፡

ሆኖም በዚህ ጉዳይ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የግብፅ በሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ላሰማራ ማለት፣ የቀጣናውን ችግር ሊያወሳስብ የሚችል አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ ጉዳዩ ኢትዮጵያን በጦር ከበባ በማስፈራራት ጫና ውስጥ ለመክተት የሚደረግ ሙከራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የግብፅ መንግሥት ከዚያ ወዲህም ቢሆን የኢትዮጵያ ጎረቤት ከሆኑ አገሮች ጋር የወታደራዊና የደኅንነት ግንኙነቶችን ማጠናከርን ገፍቶበታል፡፡ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የግብፅ የስለላ ተቋም ዋና ኃላፊ አባስ ከማልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በድር አብደላቲ ወደ ኤርትራ መሄዳቸው ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ በሱዳን ሰላም፣ በቀይ ባህር ቀጣና ቀውስ ጉዳዮች ሁለቱ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መምከራቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡

በዚሁ የሁለቱ ባለሥልጣናት የአስመራ ጉብኝት ወቅት የሶማሌላንድን ጉዳይ ማዕከል ያደረገውና እየተባባሰ የመጣው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ውዝግብ ተነስቶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ሁለቱ ባለሥልጣናትም ሆኑ የኤርትራ መሪዎች በወቅቱ ለሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መረጋገጥ የፀና ድጋፍ እንዳላቸው ስለመግለጻቸው በሰፊው ተዘግቦ ነበር፡፡

ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ልዩነት አንቶኒ ብሊንከን ካይሮን በረገጡበት ወቅት፣ ግብፅ እንደ ደቡብ ሱዳን ባሉ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ዋነኛዋ የሰላም አስከባሪ ጦር ላኪ አገር ልትሆን እንደምትችል ይፋ ተደርጓል፡፡ በግብፅና በአንዳንድ ጎረቤት አገሮች እንቅስቃሴ ላይ ያላትን ሥጋት ስትገልጽ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ለዚህ ምን ምላሽ ትሰጣለች የሚለው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከወዲሁ ግን ግብፅና ሸሪኮቿ በኢትዮጵያ ላይ የከበባ ስትራቴጂ እየተከተሉ ነው የሚል ግምት እያሰጠ ነው፡፡