ዝንቅ ትዝታዋ የቀረው የፒያሳዋ ዳላስ

አንባቢ

ቀን: September 22, 2024

ፍቅረኛህን ‹‹ማሀሙድ ጋር ጠብቂኝ›› ስትላት ተሳስታ ማዶ ተሻግራ ከጠበቀችህ እድለኛ ናት፡፡ ካንተ በላይ የሚያስደስቷትን ሙዚቃዎች እየሰማች ነው ማለት ነው፡፡ ከዳላስ ሙዚቃ ቤት፡፡ ይህ ቤት የየመን ዝርያ ባላቸው ሐበሾች የተያዘ ነው፡፡ ከፒያሳ ፍቅር እንዲይዝህ ከሚያስችሉ አዚሞች አንዱ ነው፤ ዳላስ፡፡

በማለዳ ፒያሳ ከመጣህ በነ‹‹ያኒ›› ዜማ ትታደሳለህ፡፡ በሩቅ ምሥራቅ ረቂቅ ሙዚቃዎች ትፈወሳለህ፡፡ ረፋድ ላይ ፒያሳ ከደረስክ በነ መሀመድ ወርዲ፣ በነ አህመድ ሙስጠፋ፣ በነ ከማል ተርባስ በነ ሳይድ ከሊፋ ሱዳንኛ ዜማ ትደንሳለህ፡፡ በሱዳን ዜማ ለመደነስ አትሽኮርመም እንኳን አንተ ጠቅላይ ሚኒስትርህም ደንሰዋል፡፡

ከቀትር በኋላ ፒያሳን ከረገጥክ ደግሞ ዳላስ በብሉይ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች አቅልህን ያስትሃል፡፡ በነ ሳም ኩክ፣ በነ ሬይ ቻርለስ፣ በነ ኢታ ጀምስ፣ በነ ዶና ሰመር፣ በነ ዳያና ሮዝ፣ በነ ማርቪንጌ፣ በነ ቲና ቻርለስ፣ በነ ሮድ ስቴዋርት ዜማዎች ትሰክራለህ፤ ትሳከራለህ፡፡ ደግሞ ማምሻ ላይ እነ ዶን ዊሊያምስ፣ እነ አለን ጃክሰን፣ እነ ሩኒ ሚልሳፕ፣ እነ ዶሊ ፓርተን፣ እነ ኬኒ ሮጀርስ በአገረ-ሰብ ሙዚቃ አለምህን ያስቀጩኻል፡፡

ዳላስ ብሉይ በኾኑ ነገር ግን በሚጣፍጡ ሙዚቃዎች የፒያሳን ዜጎች የማዝናናት ተግባር ላይ የተሰማራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ይመስለኛል፡፡ ዛሬም ድረስ ሳይታክት ጆሮ ገብ ሙዚቃዎችን ያስኮመኩማል፡፡ በነፃ!

ከዚህ ቤት የሚደመጡ ሙዚቃዎች ዘፋኞቹ በሕይወት የሌሉ ወይም ደግሞ ዘፋኞቹ ራሳቸው የረሷቸው ሙዚቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ኦልዲስ-በት-ጉዲስ››፡፡ ታዲያ በቲቪ የምታውቀው ጥቃቅንና አነስተኛ ጀማሪ ዘፋኝ እዚህ ዳላስ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ሲያንዣብብ ካየኽው አንድ ነገር ጠርጥር፡፡ ሊከትፍ ወይ ሊመነትፍ ነው፡፡

ዳላስ በብሉይ ሙዚቃዎች በይበልጥ ይታወቅ እንጂ በዓለም ላይ ዝናው ከፍ ያለ የሮክ፣ የጃዝ፣ የብሉዝ ወዘተ ሙዚቀኛን ሲዲ በመያዝም ይታወቃል፡፡ ዳላስ ገብተህ በትክክል የዘፈን ስም ከጠራህ ሲዲው ያለምንም ጥርጥር ይሰጥኻል፡፡ ድንገት እንኳ ሲዲው አልቆ ቢኾን ስለ አቀንቃኙ አንዳንድ ማብራሪያዎች ተሰጥቶህ ሌላ ጊዜ ብትመለስ ግን ሲዲው ከነልባሱ እንደሚዘጋጅልህ ተነግሮህ ነው የምትሰናበተው፡፡ ዳላስ ከተወለደ ጀምሮ ሙዚቃ አድናቂን አስቀይሞ አያውቅም፡፡ ሙዚቃ በእውቀት የሚነገድበት ቤት ነው፡፡

በነገርህ ላይ እዚያ አካባቢ የሚሠሩ የታክሲ ወያላዎች ዳላስ ሙዚቃ ቤት ተፅዕኖ ስላሳደረባቸው ይመስለኛል ተሳፋሪ ሲጠሩ ራሱ በዜማ ነው፡፡ የወያላዎቹን ድምፅ በደንብ አስተውህ ካዳመጥከው ሙዚቃዊ ቅላፄ አለው፡፡ ይስረቀረቃል፡፡ ‹‹22 ካዛንቺስ…መገናኛ!!!…መገናኛ ካዛንቺስ 22!!፣ አምስት ኪሎ…ቅድስት ማርያም…አምስት ኪሎ!!!››

ፒያሳ ከመጣህ እንደ ወይን እያደር የሚጣፍጥ ዘፈኖችን ከዳላስ ሙዚቃ ዘወትር ትኮመኩማለህ፡፡ አምስት ሳንቲም ሳትከፍል፡፡ በዚህ ዘመን አንድን ሙዚቃ ሦስት ታክሲ ውስጥ ተከፍቶ ከሰማኸው እጅ እጅ ማለት እንደሚጀመር አንተም ሳትገነዘብ የቀረህ አይመስለኝም፡፡ የድሮ ሙዚቃ ግን ውብ ነው፡፡ ሄዶ ልብህ ላይ ነው የሚቀመጠው፡፡ አይጎረብጥህም፡፡ ካላመንከኝ ፒያሳ ዳላስ ሙዚቃ ቤት ደጅ ላይ ተሰየም፡፡

አንድ ድረ-ገጽ አንባቢዬ ዳላስ ሙዚቃ ቤትን እንዴት ገለጸው መሰለህ፤ ‹‹The soundtrack of Piassa››

– መሐመድ ሰልማን ‹‹ፒያሳ መሓሙድ ጋ ጠቢቅኝ›› (2004)