ሠዓሊ ወንድወሰን ከበደ

ኪንና ባህል ያልተተኮረው የሥዕልና ሠዓሊያን ተግዳሮት

የማነ ብርሃኑ

ቀን: September 22, 2024

ጥልቅ መልዕክቶች ከሚተላለፉባቸው የጥበብ ዘርፎች አንዱ ሥዕል ነው፡፡ በሥዕል ጥበብ ኑሯችን ይቀልማል፡፡ በብሩሽ፣ ሸራና ወረቀት ላይ ሕይወታችን ይኳላል፡፡ ዕንባችን እንደጅረት ይፈሳል፣ ሳቃችንም እንደ አደይ እንደ መፀው (አበባ) ይደምቃል፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎቻችንን እንዲሁም ውድቀታችንን ከሚነግሩን የሥነ ጥበብ ውጤቶች መካከል ሥዕልን ከቀዳሚዎቹ ረድፍ የሚመድቡት አሉ፡፡ የታሪክ እጥፋቶቻችንና የማንነት ስብራቶቻችን በቀለም እየተዋዙና እየተኳሉ የሚቀርቡበት የጥበብ ዘርፍ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡

ያልተተኮረው የሥዕልና ሠዓሊያን ተግዳሮት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ሠዓሊት ዜና ሞገስ

ከሸራ፣ ብሩሽና ወረቀት ባሻገር በዘመናዊ የሥዕል ጥበብ ውስጥ አሸዋ፣ የሸክላ አፈርና የመሳሰሉ ቁሶችን በመጠቀም ጥበቡ እንዲረቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ ሆኗል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሥዕል ጥበብ በአገራችን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? የሥዕል ዓውደ ርዕይ ማሳያ ሥፍራዎች በጥራትና በብዛት አሉን ወይ? የሥዕል ሥራን የመግዛት ልምድና ባህል በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዴት ያለ ነው? ሲል ሪፖርተር የተለያዩ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

 የኢትዮጵያ ሠዓሊዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆነው ሠዓሊ ወንድወሰን ከበደ እንደሚናገረው፣ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ የዓለም የዲፕሎማቲክ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሦስተኛ ከተማ እንደመሆኗ መጠንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች እንደሚገኙባት ከተማ የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴዋ ከዛሬው ዓለም ጋር ተስተካካይ አካሄድ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡

በዛሬው ዓለም ሰዎች 70 በመቶ ሀብታቸውን ለኢንተርቴይመንት (መዝናኛ) ያውላሉ፡፡ በዚህም ከሙዚቃና ሲኒማ ቀጥሎ ትልቁን የመዝናኛ ፋይናንስና አገራዊ ዓመታዊ ገቢ (ጂዲፒ) የሚይዘው ሥዕል ነው፡፡ ጥቂት ዓመታትን ባስቆጠረ ጥናት በዓለማችን በአንድ ቀን ውስጥ በደቂቃ አንድ ሚሊዮን የሚሆን የሥዕል ሽያጭ ዝውውርና መቶ ሺሕ የጥበብ ትርዒቶች እንደሚከናወኑ እንደሚናገረው ሠዓሊው፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ውስጥ ድርሻዋ ምን ያህል ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ እዚህ ግባ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም ደግሞ ዋነኛው ምክንያት አገረ መንግሥቱን የሚመራው ሥርዓት ኢትዮጵያ ያላትን ጥንታዊና ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ሀብት በአገረ መንግሥትና ትውልድ ግንባታ እንዲሁም ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ፋይዳ ተገንዝቦ የሥነ ጥበብ ፖሊሲ ቀርፆ ጥበቡ ወደ ኢንዱስትሪ የሚያድግበትንና በዓለም የጥበብ መድረክ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መታየት የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡

እንደ አገር የሥዕል ጥበብ መንግሥታዊና ተቋማዊ ዕገዛ የሌለው በመሆኑ በጥበብ ወዳድ ግለሰቦችና በግሉ ኢንቨስትመንት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህም ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ብዛትና ከከተሞች ዕድገት አንፃር በዓይነትና በብዛት ተስተካካይ ሆኖ እንዳይራመድ አድርጎታል፡፡

እንደ ሠዓሊ ወንድወሰን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴ ከትርዒት ዝግጅት አንፃር ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡

መንግሥት ለድግስና ሪፖርት ማሟያ የሚያዘጋጃቸውን የሥዕል ትርዒትና ትልልቅ ባዛሮችን ትተን በግሉ ዘርፍ በተቋቋሙ ቤተ ሥዕል ማሳያዎች (ጋለሪ)፣ ሆቴሎች፣ ሙዚየሞችና ኤምባሲዎች ውስጥ የሚደረጉ ጊዜያዊ የሥዕል ትርዒቶች ቢሰሉ ቁጥራቸው እያደገና ተመልካቻቸውም በዚያው ልክ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በዓመት ውስጥ ከ70 በላይ የግልና የቡድን የሥዕል ትርዒቶች ይታያሉ፡፡ ‹‹ፈንድቃ›› የባህል ማዕከል በዓመት መርሐ ግብሩ ውስጥ 16 የግልና የቡድን የሥዕል ትርዒቶችን ወጪ በመሸፈን ያለ አንዳች ክፍያ ያካሂዳል፡፡ ባሳለፍነው 2016 ዓ.ም. ሦስቱን ትውልድ ባማከለ መልኩ 23 የሥዕል ትርዒቶችን ማሳየቱንም ሠዓሊው ይናገራል፡፡

በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች፣ ሙዚየሞች፣ ኤምባሲዎች፣ ሆቴሎች፣ በግል ቤተ ሥዕል ማሳያዎች እንደ አዲስ ፋይን አርት፣ ኢቲ ሜትሮፖሊታን፣ ዓለም ጋለሪ፣ ላፍቶ ሞል ጋለሪ፣ አትሞስፌር ጋለሪ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋለሪ፣ ሬድ ዶር ጋለሪ እንዲሁም በታላላቅ ዲፕሎማቲክ ባዛሮች እንደ ቢግ አርት ሴልና አርቲዛን ባዛር ላይ የሚደረጉ የሥነ ጥበብ ክዋኔዎች ቢደመሩ በአማካይ ከ70 በላይ ይሆናሉ፡፡ ይህ እየሆነ ያለው አገሪቱ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች እየተናጠች ባለችበት ወቅት ነው የሚለው ሠዓሊ ወንድወሰን፣ አገር ብትረጋጋና የመንግሥት ድጋፍ ጥበቡ ላይ ቢታከልበት ዘርፉ ከዚህ በላቀ ሊነቃቃ የሚችል መሆኑን ይናገራል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ቀደምትና ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ታሪክ እንዳላት አገር በስሟ፣ በታሪኳና በሕዝቧ ምጣኔ ልክ የሥዕል ማሳያ ብቻ ሳይሆን ገቢረ ሙሉ የሆነ ሙዚየም የሌላት አገር ናት ሲል ይገልጻል፡፡

እንደ ሠዓሊ ወንድወሰን፣ አገሪቱ ከአሥር የማይዘሉ ቤተ ሥዕል ማሳያዎች የሚገኙባት ሲሆን፣ እነሱም ቢሆን ለጥበቡ ፍቅር ባላቸው ግለሰቦች ኢንቨስትመንት ላይ የተንጠለጠሉ እንጂ መንግሥታዊ ድጋፍ ያላቸው አይደሉም፡፡

እነኚህ ያሉትም ቢሆኑ ከከተሞች ዕድገት፣ ከኪነ ሕንፃ ግንባታና ከብዛት አንፃር ቁጥራቸው ማደግ ሲኖርበት፣ ከማሳያ ቦታ ኪራይ ውድነትና አሸማቃቂ በሆነው የመንግሥት ቀረጥ እየተዳከሙ ከገበያ ወይም ከሥነ ጥበቡ መድረክ በመገለል ላይ ናቸው፡፡ እየተገነቡና ተፈጥረው ያየናቸው አዳዲስ ጋለሪዎችም አሁን ባለው አገራዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምስቅልቅልና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ብዙም ሳይቆዩ እየከሰሙ መሆኑን ያክላል፡፡

እንደ ሠዓሊው፣ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞች የሥዕል ማሳያ ቦታዎች ሊኖሩና ጥበቡ ለመላው ሕዝብ ተደራሽ ሊሆን የሚገባው ነው፡፡

መንግሥት ነጫጭ ዝሆኖች የሚያክሉ ፓርኮች ገንብቶ በውስጣቸው የሥነ ጥበብና አምፊቴያትር ይገኛል እያለ ቢለፍፍም፣ እውነታው ግን ሌላ ነው የሚለው ወንድወሰን፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ የግብር ገንዘብ የተገነቡ ፓርኮችንና ሌሎች ተቋማትን የተቆጣጠሩት ከበርቴዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሊደረግ ለታሰበ የሥዕልም ይሁን መሰል የጥበብ ዝግጅት ለቀን ኪራይም ሆነ ለሰዓታት ቆይታ የሚጠየቀው ክፍያ ከካድሬያዊ ቢሮክራሲ፣ የመነጨ ዓይን ያወጣ ዘረፋና አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡

እንደ ሠዓሊው በቀደመው ልማድም ሆነ አሁን በስሱ በሚታየው ግንዛቤ በሥዕል ጥበብ ሙያተኛው ሕይወቱን መርቶ መኖር የሚችል አይመስልም ነበር፡፡ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከቀድሞው ጊዜ በእጅጉ የተለየና አስገራሚ ለውጥ የሚታይበት ነው፡፡ ዛሬ ላይ እንድ ጥበበኛ ሥራውን አክብሮ አምራች ሆኖ መገኘት ከቻለ ከራሱም አልፎ ለሌላው መትረፍ የሚችልበት ዕድል አለው፡፡

በአሁኑ ወቅት የአንድ ሥዕል ዋጋ እንደ ጥበበኛውና ገዥው ፍላጎት መሠረት ከአምስት ሺሕ እስከ 1.7 ሚሊዮን ብር፣ ከዚያም ሲያልፍ ከ1‚500 እስከ 20 ሺሕ ዶላር የተሸጡባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል የሚለው ወንድወሰን፣ በዚህም ዘመናዊ መኪኖችን መንዳትና ቅንጡ ቤቶችን መገንባት የቻሉ ጥበበኞች ጥቂት የሚባሉ አለመሆናቸውን ይገልጻል፡፡

ኢትዮጵያውያን የሥዕል ሥራን የመግዛት ልምድና ባህላቸው እያደገ መምጣቱንና ሥዕል የክብር (የደረጃ) መለኪያ እየሆነ መሄዱን የሚናገረው ባለሙያው፣ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች ለአንድ ሥዕል እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ሲከፍሉ ዓይናቸውን የማያሹ ሆነዋል፡፡ ከታላላቅ ነጋዴዎች እስከ አካዴሚክ ምሁራን፣ ከጥቃቅን ባለሀብቶች እስከ መንግሥት ሠራተኛው ባላቸው አቅም ሥዕል ለመግዛት የሚያሳዩት ፍላጎትና ለመግዛት ያላቸው የመወሰን ድፍረት በመጪው የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ዕድገትና ጉዞ ላይ ተስፋ የሚጥል ነው ሲልም አክሎ ይገልጻል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ የሥዕል ዓውደ ርዕይ የሚደረግባቸው ቦታዎች አብዛኛዎቹ በግል ኢንቨስትመንት የለሙና በዋጋ ደረጃም ውድ የሚባሉ ናቸው የምትለው ሠዓሊት ዜና ሞገስ ናት፡፡ ይህ መሆኑም ታላላቅ ሠዓሊያንን እንጂ ጀማሪዎች የሚበረታቱበት አይደለም፡፡

እንደ ሠዓሊዋ፣ በኢትዮጵያውያን ሠዓሊያን የተሠሩ የጥበብ ሥራዎችን በአብዛኛው የሚገዙት የውጭ አገር ዜጎችና ዳያስፖራዎች በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ካለችበት አለመረጋጋትና ከቱሪዝም ዘርፍ መቀዛቀዝ ጋር ተዳምሮ የሥዕል ገበያው አጥጋቢ ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የሥዕል ጥበብ ሁለት ዓይነት መልክ አለው የምትለው ሠዓሊት ዜና፣ አንደኛው ነገር ሠዓሊው በራሱ ሥራውን ለማስተዋወቅ የሚያደርገው ጥረትና የሥዕል ማሳያ ጋለሪዎች መበራከት ሲሆን፣ ሁለተኛውና ሌላኛው ፅንፍ ደግሞ የሥዕል ሙያ እንደሌላው የጥበብ ዘርፍ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት አነስተኛ መሆን ነው፡፡

ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የወጡ፣ የሥዕል ሙያን የተማሩና ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች ለስሜታቸው የሚሠሩት እንጂ ገቢ እያገኙበት አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እንደ ሌሎች ቁሶች ሥዕልን ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ብሎ የሚገዛ ባለመኖሩ ነው የምትለው ዜና፣ በዚህም የተነሳ ሠዓሊያን ሙያቸውን ለመቀየር እየተገደዱ ስለመሆኑ ትገልጻለች፡፡

እንደ ሠዓሊዋ፣ ለሥዕል ሥራ የሚያገለግሉ እንደ ቀለምና መሰል ግብዓቶች እጥረት፣ የሥዕል ማሳያ የቦታ ችግር፣ በመንግሥት አካላት ስለ ጥበቡ ያለው አረዳድና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ዘርፉ እንደ አገር በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ አግዶታል፡፡

‹‹ሙዚቃ አንድ ስቱዲዮ ውስጥ ሪከርድ ተድርጎ ሙሉ ዓለም እንዲሰማው ማድረግ ይቻላል፣ ተደራሽነቱም ብዙ ነው፤›› የምትለው ዜና፣ ሥዕል በፎቶም ሆነ በቪዲዮ ተደጋግሞ የመታየት ዕድል ቢያገኝ እንኳ ፊት ለፊት ወይም በአካል ቀርቦ እንደሚታየው ሊሆን አይችልም፡፡

በተጨማሪም ማኅበረሰቡ በሥዕል እንዲመሰጥ፣ እንዲዝናና፣ ሥዕል እንዲገዛ፣ ጥበቡ እንዲያድርበትና ለዘርፉ ፍቅር እንዲኖረው የተሠራ ሥራ የለም ስትል ታክላለች፡፡

ስለሆነም ሥዕል ምንድን ነው? ምን ጥቅም ይሰጣል? ለሥዕል ምን ያስፈልጋል? ሥዕል ስለምን ይሣላል? የሚለውን ትውልድ ሊያውቅና ሊረዳ ይገባዋል፡፡ ይህ አረዳድና ግንዛቤ እንዲሁም የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት ከቻለ እንደ ውጭ ዜጎች ኢትዮጵያውያንም ሥዕልን የማጣጣምና የመግዛት ልማዳቸው እየዳበረ መምጣት የሚችል መሆኑን ሠዓሊት ዜና ትገልጻለች፡፡