በፓሪስ ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበው በሪሁ አረጋዊ ሽልማቱን ሲቀበል (ፎቶ ኦሊምፒክ ኮሚቴ)

ስፖርት ‹‹ክርክሩና ውዝግቡ ለስፖርቱም ሆነ ለአትሌቱ መሠረታዊ ችግር በሆነው የማዘውተሪያና የትራክ ጉዳይ አለመሆኑ…

ደረጀ ጠገናው

ቀን: September 22, 2024

ብሔራዊ አትሌቶች ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመጣ ቁጥር፣ በተለይም በአመራሮች መካከል የሚስተዋለው ውዝግብ ሕግና ሥርዓትን ባከበረ መልኩ፣ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ብሔራዊ አትሌቶችና አሠልጣኞች ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በማሪዮት ሆቴል ባዘጋጀው የዕውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ የታደሙ ብሔራዊ አትሌቶችና አሠልጣኞች ስለተደረገላቸው ዕውቅናና የገንዘብ ሽልማት አመስግነው፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ የተመዘገበውን ውጤት ተከትሎ በሁለት ወገኖች ማለትም በቀድሞ አትሌቶችና በኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች መካከል የሚስተዋለው መካሰስና መወዛገብ ‹‹እንቆረቆርለታለን›› ለሚሉት አትሌቲክስ የሚፈይደው አንዳች ነገር ስለሌለ፣ ውዝግቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡

ከነባሮቹ አሠልጣኞች ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ፣ ገመዶ ደደፎ፣ ሐጂ አዴሎና ቶሌራ ዲንቃ በየበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ሁሉ ውዝግብና ክርክር እውነት ለአትሌቲክሱ ቢሆን ሁላችንም ምንኛ ደስ ባለን፣ ግን አይደለም፡፡ መወዛገቡና መከራከሩ ለስፖርቱ ከሆነ፣ አሁን ላይ ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር የሚገባን ስለስፖርት መሠረተ ልማትና ለአትሌቶቻችን ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ ለሚገኘው የትራክ ጉዳይ በሆነ ነበር፤›› ብለው፣ በየአራት ዓመቱ የሚስተዋለውን ለአትሌቲክሱ አንዳች ፋይዳ የሌለው ጉንጭ አልፋ ክርክርና ውዝግብ ‹‹ሰልችቶናል›› ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

በማራቶን ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው ታምራት ቶላ፣ በሪሁ አረጋዊና ጽጌ ድጉማ በየበኩላቸው፣ ‹‹ችግሮች እንኳ ቢኖሩ መነጋገርና መፍትሔ ማበጀት እየተቻለ፣ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መሄድ በዋናነት የሚጎዳው አትሌቱንና ስፖርቱን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከሰሞኑ እኛን አትሌቶቹን ጨምሮ ለብዙዎች ግራ እያጋባ ባለው ጉዳይ፣ በግሌ በጣም የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ክርክርና ውዝግብ ውስጥ አትሌቶች እየተቸገርንበት ስላለው የስፖርት ማዘውተሪያና በዋናነት የትራክ ጉዳይ ‹‹ጉዳያችን›› ነው የሚል ተከራካሪ አለማየቴ ነው፤›› በማለት የተናገረው በሪሁ አረጋዊ፣ ‹‹ልብ ልንል የሚገባው የምንወዳደረው የስፖርቱ መርህ ገብቷቸው፣ አስፈላጊው የመሠረት ልማት ከተሟላላቸው አገሮች አትሌቶች ጋር ነው፤›› ብሎ፣ ‹‹እባካችሁ መሠረታዊ ችግራችን እየሆነው በመጣው ማዘውተሪያና ትራክ እንዴት እንገንባ? በሚለው ጉዳይ ተነጋገሩ፣ ተወቃቀሱ፣ መነጋገርና መከራከር ተገቢ ነው ከተባለም መሆን ያለበት አሁን ላይ ለስፖርቱም ሆነ ለአትሌቶች መሠረታዊ ችግር በሆነው ማዘውተሪያ ነው መሆን ያለበት፡፡ የትራክ ጉዳይ ለክርክሩና ለውዝግቡ መነሻ ምክንያት ለምን እንዳልሆነ አስገርሞኛል፤›› በማለት ነበር ለተከራካሪ ወገኖች ተማፅኖውን ያቀረበው፡፡

በ800 ሜትር ሴቶች የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጽጌ ድጉማ በመርሐ ግብሩ ያነሳችው ነጥብ ቢኖር፣ ‹‹በፓሪስ ኦሊምፒክ ወቅት ከግል አሠልጣኟ ጋር ተያይዞ ሲነገር ስለነበረው ጉዳይ፣ እውነታውንና የሆነውን ነገር በቅርቡ ይፋ የማደርገው ይሆናል፤›› ብላለች፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ባዘጋጀው የዕውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር፣ በፓሪስ  ኦሊምፒክ ላይ በማራቶን ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው ታምራ ቶላ ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ሦስቱን የብር ሜዳሊያ ያስመዘገቡት በማራቶን ትዕግሥት አሰፋ፣ በ800 ሜትር ሴቶች ጽጌ ድጉማና በ10 ሺሕ ሜትር ወንዶች በሪሁ አረጋዊ እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በማራቶን ሴትና ወንድ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበው አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ 1.8 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ለሜቻ ግርማ፣ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃና ሐጂ አዴሎ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ሌሎች የልዑካን ቡድኑ አባላት በየደረጃው ለሚገኙ ሁሉም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡