ሲሳይ ሳህሉ

September 22, 2024

ቆይታ

አብዛኛውን ጊዜ በግል ሥራ በመሰማራት፣ ኮሌጅ በባለቤትነት በማስተዳደር፣ በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ ባለያነትና በማማከር ሥራ ይታወቃሉ፡፡ ለፉት አሥር ዓመታት  ደግሞ በኢነርጂና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዘርፍ በግል ኩባንያዎች ውስጥ በማርኬቲንና በቢዝነስ ልማት ኃላፊነት ርተዋል፡፡ በአንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ባንያ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያና በአፍሪካ በኤክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ያሉ ሁታዎች በመከታተል ጥናት በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሚጀምረው የሁለተኛ ዲግሪ የኤሌክትሪክ ሞቢሊቲ ፕሮግራም በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፀሐይ ኢነርጂና ማገዶ ቆጣቢ ፕሮጀክት ለጀርመን ልማት ድርጅት (ጂአይዜድ) አማካሪ በመሆን እየሠሩ ናቸው፡፡ አቶ በረከት ተስፋዬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብቻ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያስተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ግሪን ኢኮኖሚ ምንድነው? በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መንግሥት እያለ ያለው ምንድነው?

አቶ በረከት፡- አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ (CRGE) የሚባል እ.ኤ.አ. በ2011 የታቀደ ፕሮግራም አዘጋጅታለች፡፡ ይህ ፕሮግራም በአገራችን በአየር ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያግዙ በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ በተለይ በኢነርጂና በትራንስፖርት ዘርፍ ታዳሽና ጭስ አልባ የሆኑ የኢነርጂ ምንጮችን መጠቀም የፕሮግራሙ ዋና ምሶሶ አድርጎ የያዘ ሰነድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያደጉ አገሮች አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በማንፀባረቅ በተለይ ከአካባቢ ብክለት አንፃር በአደጉት አገሮች ላይ ግፊት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ለአካባቢ ብክለት ዋነኛ የችግሩ ምንጮች ያደጉ አገሮች ሆነው ሳለ ኢትዮጵያን የሚያስጨንቃት ምንድነው?

አቶ በረከት፡- ኢትዮጵያ ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የሚጣጣሙ ፕሮግራሞች ቀርፃ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ የ‹‹GTPI (2011-2015), GTPII (2016-2020)›› የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ (10 Years Development Plan (2020-2030)፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፓሪስ ስምምነት የፈረመች አገር ናት፡፡ ይህ ማለት በራሷ ተነሳሽነት በትራንስፖርት፣ በኢነርጂና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለኃይል የምትጠቀማቸውን በካይ ጋዞች እንድትቀንስና ታዳሽ  ኃይልን በአማራጭነት ለመጠቀም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ CRGE ዕቅድ መሠረት በሥራ ላይ ለማዋል ቃል ገብታለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቶችን ትወስዳለች፣ ጥቅምም ታገኛበታለች፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የምትለይበት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ የፈራሚ አገሮች አባል እንደ መሆኗ ዕቅዶችን ለመተግበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገች ነው፡፡ መሰናክል አይኖርም ወይ ከተባለ ምንም ጥያቄ የለውም መልሱ አዎ አለ ነው፡፡ ብዙ አገሮችም ያለፉበትና እያለፉበት ያለ ጉዳይ ስለሆነ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ካልሆነ ወደ አገር ውስጥ መግባት አይችልም ብሎ ሲወስን፣ ምን ዓይነት አስቻይ ሁኔታን ተማምኖ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ በረከት፡- አገሮች ማትም አብዛኞቹ ማለት እንችላለን ዓላማ ይዘው በነዳጅ ይጠቀሙ የነበረበትን ማንኛውም ዘርፍ፣ ታዳሽ ኃይል ወይም አነስተኛ በካይነት ያላቸውን የኢነርጂ ምንጭ አማራጮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መጠቀም የሚደረገው የሽግግር ጊዜ አንዱ አካል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሒደት ሰፊ ዕቅድ፣ ሀብትና ትልቅ ፕሮግራም ይፈልጋል፡፡ በሒደት ቀስ በቀስ ሊደረግ የሚችል እንጂ በአንዴ የምትፈጽመው አይደለም፡፡ መንግሥታት በተሽከርካሪ አጠቃቀም ረገድ የነዳጅ መኪኖች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ሙሉ ለሙሉ እናስቀራለን በሚል እ.ኤ.አ. በ2030፣ 2040፣ 2050፣ እንደ አገሮቹ አቅም ዕቅድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያም በተወሰነ መጠን እ.ኤ.አ. በ2020 የወጣው ዕቅዷ መጀመርያ ላይ 160 ሺሕ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን፣ እንዲሁም ከ2,000 እስከ 5,000 አውቶብሶችን ወደ ገበያ አስገባለሁ የሚል ነበር፡፡ አሁን 100 ሺሕ የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ይመስሉኛል፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የኤሌክትሪክ ላስገባ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ በሒደት ቀስ በቀስ ትልቅ ፕሮግራም ተቀርፆ የሚፈጸም እንጂ በአንዴ አደርገዋለሁ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ፓሪስ ስምምነት ፈራሚዎች በሚደረጉ ጉባዎች ያደጉ አገሮች የአየርን ንብረት ቀውስን ለመከላከል ሀብት ለመለገስ የሚደረጉ፣ በተለይም አዳጊና እያደጉ ላሉ አገሮች ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ የለጠ እንዲሠሩ በሚል በየዓመቱ ገንዘብ ለመስጠት ቃል ይገባሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነት ላይ ችግር ይስተዋላል፡፡ ድጋፍ በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገሮች የሚተገብሯቸው የምዕራባዊያኑንና የአሜሪካን ጫና የሚመስሉ አገራዊ ፕሮጀክቶች እንዴት ያዩዋቸዋል?

አቶ በረከት፡- ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀም የኢነርጂ ምንጮችን መጠቀም ከጀመረች ስንብታለች፡፡ ይህ በጠቅላላ ከሚያስፈልጋት የኢነርጂ መጠን በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው ወይም ስምንት በመቶ በመሆኑ፣ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ያደጉ አገሮች በገቡት ቃል መሠረት ቢለግሱ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ይሆን ነበር፡፡ አሁንም በየዓመቱ በሚደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎችና መድረኮች በተደጋጋሚ የሚነሳው ይኸው ጥያቄ ነው፡፡ ቃል እየተገባ ገንዘቡ እየተለቀቀ አይደለም በሚል ወቀሳ ይሰማል፡፡ ይህን ለማስተካከል ጥረትና ግፊት አለ፡፡ እነዚህ ጭስ አልባ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚረደጉ ጥረቶች ቢሆኑም በታሰበው ልክ ግን ሲፈጸም አይታይም፡፡እ.እ.አ. 2021 የአየር ንብረት ለውጥን ተግባራዊ ለማድረግ በተሻሻለው ዕቅድ (NDC 2021)  መሰረት  ጠቅላላ ከሚያስፈልው ገንዘብ መጠን ውስጥ እስከ 20% ድረስ (63 ቢሊዮን ዶላር) በሃገር ሃብት ሃብት ነው ይሸፈናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አብላጫው 80% ግን ከለጋሽ ሀገራት ይሰበሰባል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በቅርቡ የጀመረችው ኤሌክትሪክ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሏ በሚገባ የተጠና ነው? በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል አገር አለ?

አቶ በረከት፡- በመንግሥት ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ዕቅድ ይዞ መመጣቱ መልካም ነገር ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን ጊዜውና የተደረሰበት ውሳኔ ተገቢነት በሚገባ ሊጤን ይገባ ነበረ፡፡ ምክንያቱም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን ለማስገባት ስታስብ በቅደም ተከተልና ጎን ለጎን ልታደርጋቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ትግበራ ዋና ዋና ማነቆ ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡት ጉዳዮች የመጀመሪያው መሠረተ ልማት ሲሆን፣ አስተማማኝ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለ ወይ የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አገራችን በአብዛኛው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚያጋጥማት አገር ናት፡፡ በከተሞች ጭምር እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የኃይል መቆራረጥ አለ፡፡ ይህ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሌለበት፣ ብዙ ድርጅቶችና መኖሪያ ቤቶች ኤሌክትሪክ በማያገኙበት ሁኔታ፣ አይደለም ከአዲስ አበባ ወጥተን በአዲስ አበባ ጭምር ችግሩ በግልጽ እየታየ ባለበት ሁኔታ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ሊሳካ ይችላል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛው የቤት መኪና ማታ ቤት ሲያርፍ ቻርጅ ልታደርገው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን የሕዝብና የንግድ ተሽከርካሪ የሆኑ ታክሲዎችን፣ በራይድ አገልግሎት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችንና ትልልቅ አውቶቡሶችን ቻርጅ ለማድረግ በርካታ ፈጣን ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ሊገነቡ ይገባል፡፡ አሁንም ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ፈጣን የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ልገንባ ብትል በዚያ አካባቢ በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለ ወይ የሚለው መልስ ይፈልጋል፡፡ ውሳኔው ይዟቸው የሚመጣ ትልልቅ በርከት ያሉ ትራንስፎርመሮችና ሌሎች የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች ስለሚያስፈልጉ እነዚህ ተሟልተዋል ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ የቻርጂንግ ጣቢያ መሣሪያዎችና ተጓዳኝ ቁሳቁሶች ጉዳይ አለ፡፡ ሦስተኛው በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለ ወይ የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ ነው በቴክኒክ ሙያ የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሉ ወይ? የሚያሠለጥን ተቋም ራሱ ስለመኖሩ መታሰብ አለበት፡፡ በተለመደው መንገድ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን የሚጠግኑ የተማሩ ባለሙያዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የራሱ የሆነ ሥሪት ያለው በመሆኑ ለዚህ የሚሆን ባለሙያ ጋራዥና መለዋዋጫ አለ ወይ ብለህ መጠየቅ አለብህ፡፡ አራተኛው የፋይናንስ ምንጭ መኖርና አለመኖር የሚለው ሲሆን፣ በተለይም በአደጉት አገሮች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንዲለመድ ያደረገው ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ የድጎማና የማበረታቻ ሥርዓቶች ተዘርግተው በመሠራቱ ነው፡፡

ከታክስ ነፃ የማድረግ መመርያ በሥራ ላይ ማዋል፣ እንደ ጉምሩክ ቀረጥ፣ ሱር ታክስ፣ ኤክሳይስ ታክስና ተጨማሪ እሴት ታክስ ዓይነቶችን መቀነስ በጎ ጅምር ቢሆንም ይህ ብቻ በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌሎች የፋይናንስ ውጪ የሆኑ አማራጮች፣ ድጎማዎችና ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህን የአገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሒደትና በቅደም ተከተል የምታደርጋቸው ናችው፡፡ አምስተኛው ጉዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መለዋወጫን ጨምሮ አስፈላጊ ጥሬ ዕቃ ለማስመጣት አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አላት ወይ ሲባል አሁንም ሌላ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ባንኮች ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ብድር ያቀርባሉ ወይ በሚል ገበያውን ዘወር ዘወር ብለህ እስካሁን ያለውን ስትመለከት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ ያሉት አበረታች ፖሊሲዎችና የባንኮች አሠራር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ለምሳሌ አብዛኞቹ የባንክ ተቋማት የአሥር ዓመት የመኪና ባትሪ ዋስትና ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን የመኪናው ባትሪ መኪናውን በሚጠቀመው ሰው አያያዝ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አምራቹ የባትሪውን የአገልግሎት ዘመን (Charege Lifecycle) ሊያቀርብ ይችላል እንጂ፣ መኪናውን ለሸጠለት ሰው ሁሉ እንዴት ለባትሪው የአሥር ዓመት ዋስትና መስጠት ይቻለዋል? ይህ አሠራር ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መንግሥት ከሰጠው ማበረታቻ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ስድስተኛው የቴክኖሎጂ ጉዳይ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂው በየጊዜው እያደገ የመጣ ነው፡፡ በርካታ ታዳጊ አገሮች በሁለት እግር ተሽከርካሪ ጀመሩ፡፡ ከዚያም በሦስት እግር፣ ቀጥለውም በአራት እግር የቤት መኪና ላይ እያለ ትልልቆቹ ጋ የመጣ ነው፡፡ እዚህ አገር ትልልቅ ተሽከርካሪዎች በተለይም አውቶብስና ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ፍላጎቱንም ገበያውንም እያየን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቴክኖሎጂው ገና ልጅ የሚባልና እያደገ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ጨቅላ በሆነበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ሪስክ መውሰድ አስፈላጊ ነው ወይ ተብሎ አይታሰብም፡፡ አካሄዱ በደረጃ ነው ወይስ በአንዴ መወሰን አለበት የሚለው በግልጽ መታየት አለበት፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የጠቀስኩዋቸውንና ዝግጁነት በግልጽ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ስትመለከት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ብቻ ነው አሁን ማስገባት ያለብን የሚለው አዋጭ ላይሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ቅሬታዎችን በተለያየ መድረክ እየሰማን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዶች መንግሥት የነዳጅ ወጪ ስለበዛበት እንጂ ውሳኔው አዋጭ አይደለም ይላሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ውሳኔው የቸኮለና የሽግግር ጊዜ ሳይኖረው ተፋጠነ ው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

አቶ በረከት፡- ሁሉም ነገር ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አገር ውስጥ ያሉ የውጭ ድርጅቶች አንድ ተሽከርካሪ ከፈለጉ አሁን ባለው የእኛ አገር  አሠራር መጀመሪያ ጥያቄ አስገብተህ፣ ትዕዛዝ ፕሮሰስ ተደርጎና ጂቡቲ ወደብ ደርሶ፣ የጉምሩክ ሒደት አልፎ አገር ውስጥ እስኪገባ በትንሹ እስከ ስድስት ወር ወይም ከዚያም በላይ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሚቀጥለው ዓመት አገር ውስጥ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ከአንድ ዓመት በፊት የታዘዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  ስለዚህ ዛሬ ሕግ አውጥተህ ወዲያውኑ ይፈጸም ስትል ብዙ ትርምስ ይፈጥራል፣ መጉላላት ያስከትላል፡፡ ሁለተኛ የቻርጂንግ ጣቢያዎች መሠረተ ልማት መዘጋጀት አለበት፡፡ ይህንን ለማዘጋጀትና ከውጭ ማሽኖችን ማስመጣትን ጨምሮ ብዙ ሥራዎች አሉበት፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ፋሲሊቲም ይፈልጋሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች እነዚህ አካላት ይህንን ውሳኔ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በተጀመረው መንገድ መንግሥት ወስኖ ወደ ሥራ አስገብቼያለሁ በማለት ለሁሉም ተቋማት ደብዳቤ ልኳል፣ ይህንን ማስቀጠል ይችላል?

አቶ በረከት፡- እሱን ነው እያልን ያለነው፣ ለአፈጻጸም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ታስቦበታል ወይ? ሰዎች ጭንቀታቸውን እየገለጹ ያሉትም ለዚያ ነው፡፡ ሁሉም አስፈላጊ ነገሮች በደንብ ባልተዘጋጁበትና መሬት ላይ በሌሉበት ሁኔታ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለው ነገር ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ታስቦበት ቢሆን እንኳን ለሽግግሩ በቂ ጊዜ ባልተሰጠበትና አስቻይ ሁኔታ በሌለበት ውሳኔው እንዲሳካ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት የሽግግር ጊዜ ሊሰጥ ይገባል ይላሉ?

አቶ በረከት፡- ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ስናይ እያንዳንዱ ነገር ደረጃ በደረጃና በሒደት ነው የሚሠራው፡፡ ለምሳሌ እስያ ውስጥ በብዛት የምናየው ሞዴል ከአነስተኛዎቹ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከባለሁለት እግር ጀምረው መሥራታቸውን ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ በጣም በቀላሉ የምታገኘው በመሆኑ በተለይ በአብዛኛው ወጣት ያለበት ማኅበረብ ውስጥ አንድ ሞተር ሳይክል አንስቶ ሥራው ላይ ደርሶ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሒደት ሥራውንም ስኬታማ ያደርገዋል፣ ኢኮኖሚውንም በቀላሉ ያግዛል፡፡ ብዙ ኃይል የሚፈልግ የቻርጅ ጣቢያ አያስፈልግም፡፡ በየቦታው ሊገጠምና ማንም በቀላሉ ቻርጅ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ቻርጅ ጣቢያ ባይኖር እንኳን ባትሪ የሚቀይሩ ድርጅቶች ይኖራሉ፡፡ በዚያ መንገድ ለመጀመሪያ ያህል ባለሁለትና ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ቴክኖሎጂውን ማለማመድ ትችላለህ፡፡ አፈጻጸሙን በየደረጃው እያየህ በሒደት ባለ አራትና ትናንሽ የቤት ተሽከርካሪዎች ላይ ትቀጥላለህ፡፡ አፈጻጸሙን እያየህ ትልልቅ አውቶብሶችና መሰል ተሽከርካሪዎችን ታስቀጥላለህ ማለት ነው፡፡ አውቶብሶች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አንድ አውቶቡስ እስከ 400 ኪሎ ዋት ድረስ ሊጠቀም ይችላል፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ኢነርጂ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በአንዴ ልፈጽም ስትል ይህን ትልቅ ኢነርጂ ማቅረብ እችላለሁ ወይ ለሚለው ጥያቄ መጀመሪያ ምላሽ መስጠት አለብህ፡፡ ብዙ አገሮች ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ፈጅቶባቸዋል፡፡ በእዚህ ደረጃ ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ውጪ አንጠቀምም ካሉ አገሮች ምናልባት እ.ኤ.አ. በ2025 ላይ ትጀምራለች ተብላ የምትጠበቀው ኖርዌይ ነች፡፡ የኖርዌይ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው ላለፉት 30 ዓመታት ሠርታ ነው፡፡ ሌሎች ትልልቅ የሚባሉት አገሮች ለምሳሌ ቻይና እንኳን ትልቅ አቅም አላት የምትባለው እዚህ ውሳኔ ላይ አልደረሰችም፡፡ እ.ኤ.አ. 2025 ቻይና ውስጥ ከሚሸጡ አነስተኛና ቀላል መኪኖች ውስጥ 20 በመቶ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ይህን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ይደግፍልኛል የሚለውን ፖሊሲ እንዴት ማዘጋጀት አለበት ይላሉ?

አቶ በረከት፡- ይህ ግልጽ የሆነ ፕሮግራም ያስፈልገዋል፡፡ የተቀናጀ ሰፋ ያለ ፕሮግራምና አፈጻጸሙ እንዴት መሄድ እንዳለበት በደረጃ ማስቀመጥና ማሳየት አለበት፡፡ ለእነዚህ ሒደቶች የሚሆን መሠረተ ልማት፣ የፋይናስ አቅርቦት ሥርዓት፣ የሰው ኃይል፣ ቴክኖሎጂና የመሳሰሉ የገበያ ሥርዓቶችና አስቻይ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች በተባለውና በታቀደው መሠረት እንዲፈጸሙ ደረጃ በደረጃ የተቀመጠ ሒደት ካለ ለፖሊሲው በትክክለኛ መንገድ መፈጸም ዕድል ይሰጡታል፡፡ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ተነስተህ የነዳጅ መኪና ክልክል ነው፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ብቻ አስገቡ ማለት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔተ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት የተወሰነ ሊያስኬድ ይችላል፣ መመለሱ ግን አይቀርም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ውሳኔው በዜጎች አኗኗርና በትራንስፖርት ዘርፍ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል?

አቶ በረከት፡- ትራንስፖርት ከተስተጓጎለ ትልቅ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከኢኮኖሚ ችግር ባለፈ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል፡፡ መንግሥት ይህን ውሳኔ ለማሳካት ምን ዓይነት የፖሊሲ ዝግጅት አድርጓል የሚለውን ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በሥርዓት ካልተመራ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ አበዳሪና ለጋሽ አገሮች የመንግሥትን ውሳኔና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን መንግሥት ሲናገር ይደመጣል፡፡ እነዚህ ለጋሾች እንዲህ ዓይነት ዱብ ዕዳ የሚመስሉ ውሳኔዎች መሬት ላይ ሲወርዱ በአፈጻጸሙ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አይገምቱም?

አቶ በረከት፡- ድርጅቶች ወይም የውጭ አገር መንግሥታት አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠርና ፖሊሲዎች እንዲኖሩ፣ በመንግሥት ጥያቄ ወይም በራሳቸው አመንጪነትና ከመንግሥት ጋር በተስማሙበት መንገድ ሕጋዊ ሒደቶችን ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ ሥልጠና መስጠት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ፣ ገበያውን ለማሳካት የሚረዱ ድጋፎችና ትልልቅ አበረታች እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ወጪ እነሱ ይደግፋሉ ማለት አይደልም፡፡ በአገር ውስጥ ሀብት ነው ገሚሱ የሚሸፈነው፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሠረተ ልማት ለመገንባት ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን ለማደራጀት መንግሥት ካለው ሀብት እንዲጠቀም ነው የሚፈለገው፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ለአማካሪዎች ሰጥቶ አማካሪዎቹ የተሻለ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ደረጃ በደረጃ ምን በየትኛው ጊዜ መፈጸም እንዳለበትና በየትኛው ቅደም ተከትል ሊፈጸም እንደሚገባ፣ ምን ያህል ሀብት ሊመደብና የመሳሰሉትን ነገሮች ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሲቀርቡ መንግሥት ሊቀበላቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ያደጉ የሚባሉ አገሮች ከዚህ ቀደም ታዳሹንም ታዳሽ ያልሆነውንም ኃይል ተጠቅመው አሁን ለዚህ ደረጃ እንደደረሱ ሁሉ ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ለመጠቀም ጊዜዋ አልፏል ማለት ነው?

አቶ በረከት፡- እንደ ዕድል ሆኖ ኢትዮጵያ ባልሳሳት ከስምንት በመቶ ያላነሰ ኢነርጂዋን ከታዳሽ ኃይል ነው የምታገኘው፡፡ 92 በመቶ ኢነርጂ የምታገኘው ታዳሽ ካልሆኑ የኃይል ምንጮች ነው፡፡ ታዳሽ የሚባለው ኃይልም በዋነኛነት ከውኃ ምንጭ የሚገኘው የኃድድሮ ፓወር ኢነርጂ ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ወደፊት ታዳሽ ኃይል ምንጭ ማስፋት ትፈልጋለች፡፡ በተለይም ከፀሐይ፣ ከነፋስ፣ ከጂኦ ተርማልና ከሌሎች ምንጮች የሚገኙ ኢነርጂዎች ይኖራሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ የፀሐይ ኃይልን ለመጠቀም የሚችሉ ትንንሽ ተሽከርካሪዎች ሥራ ላይ መዋል ይችላሉ፡፡ ለትልልቅ ተሽከርካሪዎች ግን ይህን ልታውለው አትችልም፣ በትልልቅ የኃይል ምንጮች ካልተደገፈ በስተቀር ማለቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ፖሊሲዎች ብዙ ጊዜ ድንገቴ ናቸው ተብለው ወቀሳ ይቀርብባቸዋል፡፡ ይኼኛው ውሳኔ ድንገቴ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ በረከት፡- አብዛኛውን ጊዜ የመንግሥት ፖሊሲዎች ተገማች ያልሆኑ፣ ነገር ግን ብዙ ትልምና ሕልም ያላቸው ሆነው እናያለን፡፡ ፕሮግራሞቹን በትክክል አናውቃቸውም፡፡

ነገር ግን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተሠርተው ወይም ለመሠራት ታቅደው ሀብት ተመድቦላቸው እናያለን፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ውሳኔን ስንመለከተው በሰፊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እያንዳንዱ ችግር የሚፈታበት ዝርዝር ዕቅድ ወጥቶለትና ሀብት ተመድቦለት የተገባበት ነው ማለት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት በመሥራትዎና ብዙ ጥናቶችን እንዳካሄካሄደ ሰው መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በተደረጉ ምክክሮች የነበረዎት ተሳትፎ ምን ይመስላል?

አቶ በረከት፡- በፊት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በተመለከተ ጥናቶች እናደርግ ነበር፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በተመለከተ ዕውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎችና ኤሌክትሪክ ተሸከርካረን የሚገጣጥሙ ባለሙያዎች ማኅበር አቋቁመን፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ ጥናት ሲቀርብ በውይይት መድረኮች ጥያቄ ማቅረብና አስተያየት መስጠት ችለን ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ዋነኛ ከነበሩት አስተያየቶች ውስጥ ማበረታቻ ይኑረው፣ አሁን ባለው መንገድ ብዙ ርቀት አያስኬድም፣ ሰፋ ያለ ዕቅድ ይኑረው የሚሉ ጉዳዮችን በማንሳት እንጠይቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የነዳጅ ተሽከርካሪ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ይቆማል የሚል ዕሳቤ ኖሮን አያውቅም፣ ስንጠይቅ ከነበረው በጣም የራቀ ውሳኔ ነው፡፡ ከታክስ ነፃ ማድረጉ የምንጠብቀው ማበረታቻ ነበር፡፡ ይህ መደረጉ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መጠን ሁለተኛ የነዳጅ መኪና አገር ውስጥ አይገባም የሚል እምነት ግን አልነበረንም፡፡ ምናልባት ይህ በዕቅድ ቢሠራ ኖሮ እ.ኤ.አ ከ2030 በኋላ ሊታሰብ የሚችል ነበር፡፡ ለምሳሌ እንደ ዕቅድ ስናቀርብ መጀመሪያ አስቀምጠነው የነበረው ቢያንስ እ.ኤ.አ. 2030 ሰላሳ በመቶ ያህሉ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ  ተሽከርካሪ የኤሌክትሪክ ቢሆን የሚል ነበር፡፡ በ2024 ወደ አገር ውስጥ መግባት ያለበት መቶ በመቶ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ብቻ ነው መባሉ አዲስ ክስተትና ትክክለኛ ያልሆነ ፖሊሲ ይመስላል፡፡ ይህንን ውሳኔ ዓይተህ የመንግሥትን የአሥር ዓመት የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ዕቅድ እንኳን ስተመለከት በፖሊሲው የተካተተው በ2030 ቢያንስ 160 ሺሕ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገራችን ውስጥ ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን የሚል ነበር፡፡ እሱን ደግሞ በቅርብ አሻሽለውት እስከ 500 ሺሕ ድረስ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ ይኖራሉ ተብሎ ነበር፡፡ እኔ እ.ኤ.አ. ከ2020 በፊት ባደረግኩት ጥናት በየዓመቱ የሚገባው የነዳጅ መኪና ከአሥር እስከ 15 በመቶ ያድግ ነበርና የመኪናው ቁጥሩ አሁን ከ1.4 ሚሊዮን በላይ አልፏል፡፡

ሪፖርተር፡- ድንገተኛ ፖሊሲዎች ምን ችግር ይፈጥራሉ?

አቶ በረከት፡- እንዲህ ዓይነት ፖሊሲዎች አለመረጋጋትን ያመጣሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የተዘጋጁ ባለሀብቶች ዕቅድ አውጥተው በመጪዎቹ አምስት ወይም አሥር ዓመት ያቀዱት ነገር ይኖራል፡፡ ይህን ድንገተኛ ውሳኔ አምጥተህ ዱብ ስታደርገው፣ እነዚህ ባለሀብቶች መንግሥት በዚህ በኩል ውሳኔውን የሚቀያይር ከሆነ የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ ነገ ምን ሊመጣበት እንደሚችል መተማመኛ የለንም በሚል ባሉበት ይቆማሉ፡፡ አንድ ባለሀብት መተማመኛ ካላገኘ ደግሞ አገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ አይፈልግም፣ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች በየጊዜው የሚቀያየሩ ተገማች ያልሆኑ ፖሊሲዎችን ሲያዩ አገር ቤት መጥተው ሀብት ለማፍሰስ ፍራቻ ያድርባቸዋል፡፡ ምናልባት አንዳንዶች በተለያዩ መንገዶች ዕድሉን ስላገኙና ሁኔታው ስለፈቀደላቸው የሆነ ነገር አምጥተው እዚህ አገር ሊያከማቹ ይችላሉ፡፡ ለነገ ለውጥ የሚያመጣ ቢዝነስና አምራች ኩባንያ መገንባት ብዙ ጥናትና ሀብት ይፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ውሳኔዎች በተገቢውና በተጠና መንገድ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ አሁን ይህ ውሳኔ እስከምን ድረስ እንደሚቀጥልና ምን ያህል ጫና በመንግሥት ላይ ሊያመጣ እንደሚችል አናውቅም፡፡ ስለዚህ ተገማች ባልሆነ ውሳኔ ምን ያህል ተሽከርካሪ እንዲገባ ታቅዷል? ከገባ በኋላ ተሽከርካሪዎች ሁሉም ቤታቸው ቻርጅ ሊያደርጉ ነው?  ቤት ውስጥ ያለው የኤሌክትሪክ ጭነት ይህን ማስተናገድ ይችላል ወይ? ከዚያም አልፎ በርካታ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በየሠፈሩ ቻርጅ ስታርግ የኤሌክትሪክ መቆራረጡን የበለጠ ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል፡፡ አሁን የሚገቡ ተሽከርካሪዎች እኮ ትልልቅ ባትሪ ያላቸውና ከፍተኛ ኢነርጂ የሚፈልጉ ናቸው፣ የንግድና የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡትን ተሽከርካሪዎች በተመለከተ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ይህ ከአሁኑ ሥጋት የፈጠረና እንዴትም አድርጎ መተንበይ የማይቻል ጉዳይ ነው፡፡ አይደለም ከመሀል አገር ወጣ ያለውን አካባቢና በብዙ የመሠረተ ልማት ችግር ውስጥ ያለው ሕዝብ ቀርቶ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል ዘላቂ ይሆናል የሚለው ትልቅ ጥናት ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ ጥናት ያደረጋችሁበት ሰነድ አለ?

አቶ በረከት፡- የተወሰኑ ጥናቶች አሉ፡፡ በተለይም የነዳጅ ኢነርጂ ባለሥልጣን አካባቢ ብትሄድ ጥናቶች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥናቶች ዝርዝር አይደሉም፡፡ በነበሩን ምክክሮች ወቅት የኤሌክትሪክ ቻርጅ ጣቢያ ለመገንባት የተዘጋጀ ሰነድ ላይ ከባለ ድርሻዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሰነዱን በዝርዝር አላየነውም፡፡ እነሱም ይፋ አላደረጉትም፡፡ እንግዲህ ይፋ ሲያደርጉት የምናየው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አጠቃላይ አጠቃቀም አያያዝና ሥርዓት ጋር በኢትዮጵያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ሰምተው ያውቃሉ?

አቶ በረከት፡- አሁን እንግዲህ ይህ ቴክኖሎጂ ገና ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ነው መግባት የጀመረው፡፡ ቅሬታ መነሳት የሚጀምረው ከአምስትና በስድስት ዓመት በኋላ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ የአንዳንዶቹ ተሽከርካሪዎች የባትሪ ሕይወትና ዕድሜ ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመት በኋላ ሊያልቅ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ባትሪውን ጥለህ አዲስ ባትሪ ልትገዛ ነው ማለት ነው፡፡ የባትሪ ዋጋ በዓለም ገበያ ባለፉት አሥር ዓመታት እንደታየው እየቀነሰ ነው የመጣው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ዋጋው እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ አንዳንዶች ባትሪዎች የመኪኖቹን 40 በመቶ ዋጋ ይስተካከላሉ፡፡ 30 እና 25 በመቶ በትንሽ የመኪናውን ዋጋ ይወስዳሉ፡፡ ስለዚህ በዚያን ጊዜ ባትሪ ለመቀየር ሲታሰብ ብቻ የዋጋው ጉዳይ በዚህ ልክ ሲሆን አሳሳቢነቱ እየጎላ ይመጣል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እነዚህ የንግድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተማ ውስጥ ያን ያህል ላያስፈልጉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም በብዛት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በመኖራቸው ሰው እነዚህን ብቻ እየተጠቀመ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን የኤሌክትሪክ አውቶብሶች እቀበላለሁ ካልክ በቂ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ በየመንገዱ መገንባት ስለሚኖርብህ ቅሬታውን መስማትህ አይቀርም፡፡ ሌላው አሁንም የሚፈራውና መንግሥት ከወሰነው ውሳኔ ጋር ላይሄድና ሊጋጭ የሚችለው ተጠቃሚዎችም ያቀርቡታል ተብሎ የሚጠበቀው፣ ባንኮች ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ያላቸው ዕይታ ጥሩ አለመሆኑ ነው፡፡ ለነዳጅ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ድጋፍ በጣም የተሻለ ሲሆን፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እምነት የላቸውም አደጋውን ይፈራሉ፡፡ ሌላው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ችግር ሲያጋጥማቸው ምናልባት እንደ ነዳጅ ተሽከርካሪ ብዙ ቁሳቁስ ላያስፈልግ ይችላል ነገር ግን ያም ሆኖ ቴክኖሎጂው ዓለም ላይ ገና እያደገ የመጣ በመሆኑ መለዋወጫ እንደ ልብ ላይገኝ ይችላል፡፡ ለዚያ የሚሆን አገልግሎት መስጫና፣ የመለዋወጫ ቦታና ሰው ካልተገኘ ይህም የቅሬታ ምንጭ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ቦታ የኤሌክትሪክ መዋዠቅ አለ፣ ከፍ ዝቅ ማለት የተለመደ በመሆኑ ዕቃ ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ይህንን የምትቆጣጠርበት ሌላ መሣሪያና ቴክኖሎጂ ያስፈልግሃል፡፡ እነዚህ የሚጠበቁና ሊነሱ የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተሞች የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዋች አሉ? መኪና የሚገዙ ሰዎች ቻርጅ የሚያደርጉት የት ነው?

አቶ በረከት፡- አብዛኞቹ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ቤታቸው ነው ቻርጅ የሚያደርጉት፡፡ ለስምንትና ለአሥር ሰዓት ድረስ ቻርጅ በማድረግ ነው ከቤታቸው የሚወጡት፡፡ በእርግጥ ሌሎች ያደጉ አገሮች የሚባሉትም ቢሆን ከ80 እስከ 90 በመቶ በላይ በቤታቸው ነው ቻርድ የሚያደርጉት፡፡ ነገር ግን ዋነኛው ጉዳይ እነዚህ አገሮች አስተማማኝ የሆነ ኃይልና የኢነርጂ አቅርቦት አላቸው፡፡ እዚህ አገር ግን አንድ ቀን ይመጣል፣ ሌላ ቀን ይጠፋል፡፡ ወይ ሁለት ቀን ይመጣና ሦስተኛው ቀን ላይ ይጠፋል፡፡ ስለዚህ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህ ማለት ቢያንስ የንግድና የሕዝብ ትራንስፖርት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎ ከመኖሪያ ውጪ ቻርጅ የሚደርጉባቸው ጣቢያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ ባለ26 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በ20 ብር ቻርጅ አድርገህ 200 ኪሎ ሜትር በሰዓት ልትሄድበት ትችላለህ፡፡ በነዳጅ ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ ሌለው ለአካባቢ ብክለት የሚኖረው ሚና በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህን ጥቅሞች አንክድም፡፡ ነገር ግን ይህንን ስትፈጽም በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማት ተሳትፈውበት፣ ተናበውና አብረው መሥራት አለባቸው፡፡ ቁልፍ ተቋማት ያሉበት ኮሚቴ ፈጥረህ መሥራት አለብህ፡፡ ነገር ግን አሁን ያለውን አካሄድ ስትመለከት ምንም አልተሠራም፡፡ ለዚህም ነው በጉጉት የወጣ ዕቅድ ነው ያልኩህ፡፡

ሪፖርተር– ይህንን ውሳኔ የሰሙ አካላት ኢትዮጵያ ይህን የዓለማችን የመጀመሪያዋ አገር ናት ይላሉ፡፡ አቅሙና ቴክኖሎጂው ያላቸው አገሮች እንኳን በቅርቡ እንፈጽመዋለን የሚል ዕቅድ የላቸውም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ገደብ አልጣሉም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ምን አስቦ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው?

አቶ በረከት– ቅብጠት ነው፡፡ በጣም በጉጉት የወጣ በመሆኑ ብዙ ነገሮችን ከቅርብ ጊዜ በኋላ እናያለን፡፡ መንግሥት ማቀዱ የሚደገፍ ነው፡፡ ምክንያቱም የትራንስፖርት ዘርፍ በነዳጅ ላይ ብቻ መመርኮዝ የለበትም፡፡ ብቻውን አዋጭ አይደለም፡፡ የኢነርጂ ዘላቂነትንም አያረጋግጥም፡፡ ኢትዮጵያ ነዳጅ ከሚልኩ አገሮች ጥገኛ ላለመሆን ይህንን መቀየር ግድ ይላታል፡፡ ነገር ግን ይህ በቅደም ተከተል ሰፋ ባለ ዕቅድና ሁሉም ባለጉዳዮች መክረውበት፣ በጥናትና በበቂ ፋይናንስ ተደግፎ እንጂ ዘለህ የምትገባበት ነገር አይደለም፡፡ እስኪ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ተቋም ንገረኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሠራ አንድ ጥራልኝ፣ የለም፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለማስተርስ ዲግሪ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም ሊጀምር ያሰበው ከዛሬ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ እኔ የፕሮግራሙ ማብሰሪያ ላይ ንግግር እንዳደርግ ተጋባዥ ነበርኩ፡፡ የካሪኩለም ዴቨሎፕመንት ፕሮግራማቸውን አግዝ ነበር፡፡ እሱ አንድ ጥሩ ሐሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን በተፈጠረው የፀጥታ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች በታሰበው ልክ ሄዶ ውጤት ላይ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ያ እንግዲህ በዩኒቨርሲቲ በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ ነው፡፡ ነገር ግን በቴክኒክና በሙያ ኮሌጆች፣ በማሠልጠኛ ደረጃ የአሠልጣኖች ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም መወሰን ጥልቅ ጥናቶችና ትልቅ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ ያለውን ምኅዳርና አስፈላጊነቱን መረዳት ወሳኝነት አለው፣ በመሆኑም በጥሞና ሊታይ ይገባል፡፡ ሌላው ትልቅ ጉዳይ የመኪናው ባትሪ ነው፡፡ ባትሪው ከአምስት ዓመታት ባነሰ አገልግሎት ይጨርሳል፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ በርካታ ባትሪዎችን ተጥለው ልናይ እንችላለን፡፡ ይኼኛው ባትሪ የሕዝቡን ጤና ይጎዳል፡፡ ባትሪው የሚወገድበት ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች ደግሞ የባትሪ አወጋገድ ሥርዓት አለን ወይ? ታቅዷል ወይ? ለዚያ ማስወገጃ የሚሆን ቦታ ተዘጋጅቷል ወይ? ስትል እንኳን በእኛ ሌሎች አገሮችም በልኩ አላቀዱትም፡፡ እና እነዚህ ጉዳዮች ግምት ውስጥ የገቡ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ በጣም ሰፊ ባለጉዳይ የሚነካካና ምክክር የሚፈልግ በመሆኑ በተለይም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢነርጂ ባለሥልጣን፣ የትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋማትን በአንድ አጠቃልሎ የሚይዝ ኮሚቴ ያስፈልጋል፡፡ በእያንዳንዱ ላይ ጥልቅ የሆነ የፖሊሲ ሰነድ ያስፈልጋል፡፡ ውይይት ሊደረግበትና አዋጭነቱ ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጎበት የሽግግር ጊዜ ተሰጥቶ ሊፈጸም ያስፈልጋል፡፡