September 22, 2024

ርዕሰ አንቀጽ

ኢትዮጵያ በዓለም ፊት የሚያኮሯት አንፀባራቂ ታሪኮች ባለቤት ብትሆንም፣ በፀረ ኮሎኒያሊስት ትግል ተወዳዳሪ ባይገኝላትም፣ በተለያዩ ጊዜያት ሊወሯት የመጡትን በሙሉ አሳፍራ በመመለስ ብትታወቅም፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነችና ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠር መነሻ ምክንያት መሆኗ ቢታወቅም፣ ይህንን የተከበረና ኩሩ ሕዝብ አንገት ሲያስደፋ የኖረው ድህነት ግን አንደኛው የጨለመ ገጽታዋ ማሳያ ነበር፣ አሁንም ነው፡፡ ድህነት ብሔራዊ ክብርንና ማንነትን ያዋረደ የዘመናት ጠላት ከመሆኑም በላይ፣ አሁንም አገሪቱን እየተፈታተናት ያለ ክፉ ደዌ ነው፡፡ ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው የልማት ጥረት የአገራችንን ሕዝብ ብርቱ ትብብር ካላገኘ ችግሩ እየከፋ መሄዱ አይቀርም፡፡ ድህነት የሚባለው አገራዊ ውርደት የሚቀረፈው በልማት ቢሆንም፣ ልማቱ ግን እኩል ተጠቃሚነትን ካላመጣ ዋጋ የለውም፡፡ ልማት ከዴሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በእጅጉ መቆራኘት ይኖርበታል፡፡ ፍትሐዊነትና እኩልነት የሚኖረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ድህነት የሚባለው ውርደት ከምንጩ መድረቅ እንዲኖርበት ሲፈለግ፣ ከልማቱ ጎን ለጎን ለዴሞክራሲም ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ዜጎች አገራቸውን እየተው በገፍ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት ለምን ይሰደዳሉ ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ ምክንያቱ በአመዛኙ ድህነት ነው ቢባልም፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በሰብዓዊ መብት አለመከበር ሳቢያ የሚሰደዱትን መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ከአገራቸው ርቀው ተሰደው ይኖራሉ፡፡ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውስትራሊያና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተሰደዱ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር መውጣታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የሚሰደዱ ወገኖች፣ የአገሪቱን የድንበር ኬላዎች እያቋረጡ በገፍ በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሲሰደዱ ለአገር ክብር ጭምር ውርደት ነው፡፡ ይህ ውርደት የተከበረች አገርን አንገቷን እንድትደፋ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፣ አሁንም እየተጫወተ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ አደገኛ ክስተት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አንገቷን እያስደፋ ሸክሙ በከበደበት ወቅት፣ በእርስ በርስ ጦርነት ወደ ወደመችው የመን የሚደረገው ፍልሰት መጠኑ መጨመሩ ይታወቃል፡፡ ሜዲትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ በመሻገር ያልፍልናል ብለው ለስደት የሚዳረጉ ወጣቶች፣ የዓሳ ነባሪ እራት እየሆኑ በተደጋጋሚ መርዶ ይሰማል፡፡ ከድህነቱ መክፋት በላይ ስደት ሌላ ችግር የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ድህነቱ ዘመናትን የተሻገረ ጠባሳ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጉዳይም እንዲሁ፡፡ ችግሩ ከኋላ የሚመዘዝ ታሪክ አለው ሲባል መፍትሔውም አንድ ላይ ይፈለጋል ማለት ነው፡፡ ልማትና ዴሞክራሲን ማመጋገብ የግድ ይላል፡፡ የችግሩ ግዝፈትም ይህንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ወጣቶችን ለስደት የሚያነሳሳው ምክንያት ሲፈተሽ በአብዛኛው ድህነት የፈጠረው ምሬት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ድህነት ጋር አብሮ ያለና ያደፈጠው ሌላ ችግር ደግሞ ከዴሞክራሲ ዕጦት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ስደት ብሔራዊ ክብርንና ኩራትን ያዋርዳል ሲባል፣ ዙሪያችንን የከበቡን ችግሮች አንድ በአንድ ተመንጥረው መታየት አለባቸው፡፡ የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ሲፈለግ ደግሞ ዴሞክራሲንና ልማትን በአንድ ላይ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ዴሞክራሲንና ልማትን እንደ መፍትሔ መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ከልማትና ከዴሞክራሲ ማን ይቅደም የሚለው የዶሮና የዕንቁላል እንቆቅልሽ ቀርቶ፣ አፍጥጦ ለሚታየው ችግር ተግባራዊ ምላሽ መትጋት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ርብርብም እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የአገራችንና የሕዝባችን ክብር ወደፊት ጭምር ሊከሰት ከሚችለው ውርደት የሚድነው በዚህ መጠን ችግሩ ሲጤን ነው፡፡ መንግሥት እያከናወንኩት ነው በሚለው ልማት ተሳታፊም ሆነ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው ወጣቶች ልባቸው ስደት ሲከጅል፣ ለአገር መዋል ያለበት ዕምቅ የሰው ኃይል ይባክናል፡፡

ድህነትን እንደ ብሔራዊ ውርደት በመቁጠር በስደት ምክንያት የኢትዮጵያ ገጽታ ሲበላሽ መንግሥት ቆሞ ማየት የለበትም፡፡ ስደተኞች ‹ባህር ውስጥ ሰጠሙ፣ ተደበደቡ፣ ተደፈሩ፣ ተገደሉ፣ ተዘረፉ፣ ወዘተ…› በተባለ ቁጥር አገር ሲያባንናት ማየት የውርደቱ አንድ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ዜጎች አገር እያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ዘግናኝ የሆኑ በደሎች ሲፈጸምባቸው መስማት አንገት ያስደፋል፡፡ ስደት በድህነትና በዴሞክራሲ ዕጦት የሚመጣ ውርደት ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከድህነት እላቀቃለሁ ብላ የምትማስን አገር እየተፈጠረች ነው ሲባል፣ ለዜጎቿ የምትመችና ተስፋ የሚደረግባት መሆኗን ለማሳየት የሚረዱ ተግባራዊ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ተግባራዊ ዕርምጃዎችም ዴሞክራሲንና ልማትን ያጣጣሙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከወገናዊነት የፀዱና ዜጎችን በአንድነት የሚያሰባስቡ ዘለቄታዊነት ያላቸው ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ልማት የጋራ የሚሆነውና ሕዝባዊ ተሳትፎም አለው የሚባለው ድህነትን በአንድነት ለመቅረፍ የሚያስችል መግባባት ሲፈጠር ነው፡፡

የዚህ ዘመን ስደት አስፈሪ ነው፡፡ ወትሮም በሁሉም ሥፍራዎች ስደተኞችን ለመቀበል ያለው ፍላጎት ቀዝቃዛ ከመሆኑም በላይ፣ አሁን ደግሞ በጣም ብሶበት በሁሉም አቅጣጫዎች አትምጡብን እየተባለ ነው፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱ ዜጎችን ከመምከር በላይ፣ በአገራቸው ኮርተውና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚራመዱበትን ፖሊሲ ማመቻቸት የግድ ይላል፡፡ የስደትን ምንጭ ማድረቅ የሚቻለውም የአገሪቱ ዜጎች በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ለዚህ የተቀደሰ ተግባር እንዲረባረቡ ብሔራዊ ጥሪ ሲደረግ ነው፡፡ የዜጎችን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ሲቻል ልማቱንና ዴሞክራሲውን ማመጋገብ ይቻላል፡፡ የሁለቱ ቁርኝት ደግሞ የአገር የውርደት መገለጫ የሆኑትን ድህነትና ስደትን ለመቀነስ ይጠቅማሉ፡፡ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ሲባል የምር መሆን አለበት፡፡ የልማት ውጥኑ ከእኩል ተጠቃሚነት ጋር ሳይጣጣም ስለዕድገት ማሰብ አይቻልም!