ተሟገት ሳይቦርቁ የጨረጨሱት ‹‹ሉዓላዊነት›› እና ‹‹የራስን ዕድል በራስ ወሳኝነት››

አንባቢ

ቀን: September 22, 2024

በበቀለ ሹሜ

ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ የምንገኝበት ዘመን እንኳን ደሃ አገሮች የደረጁትም ለብቻቸው ተገድበው መኖር የማይችሉበት ዘመን እንደሆነ፣ የአገሮች ዕጣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እርስ በርስ የሚወሳሰን እየሆነ እንደመጣ፣ የአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ የጎረቤትም የአካባቢም እንዲያም ሲል የዓለም ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል፣ ይህ ሁሉ ውስብስቦሽ ባለበት የዛሬው ዓለም ውስጥ ከድህነት የመውጣትና ሰላምን የመቀዳጀት ጉዳይ አካባቢያዊ ስብስብና ትግግዝ ከመፍጠር ጋር በእጅጉ እንደተያያዘ፣ ከውጭ ጣልቃ ገብነትና ጥቃት የሚያድነንም ሉዓላዊ ነኝ ከማለት ይልቅ ከትርምስ አምልጦና ተባብሮ በዕድገት መገስገስ እንደሆነ በማሳየት አጠንጥኗል፡፡ የከበሩት አገሮችና ኩባንያዎቻቸውም ከብዙ መንግሥታት አመል ጋር የመላፋት ድካምንና ወጪን የሚያቃልልላቸውን ክፍለ አኅጉራዊና አኅጉራዊ ስብስብ እንደ መምረጣቸውም፣ ቁራጭ አገር ሆኖ ለመቆየት መሞከር መረሳት ማለት የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ የዛሬው ጽሑፌም የማዕዘን ድንጋይ ያደረገው እነዚህን ቁልፍ ነጥቦች ነው፡፡

በአጠቃላይ የምንገኝበትን ዓለማዊና አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችንና አዝማሚያዎችን በትክክል መረዳት ለውድቀት ሳይዳረጉ፣ ጉድባና ገደልን በብልኃት ለመሻገር ያስችላል፡፡ በየአካባቢው የተፈጠሩ/የተወጠኑ ስብስቦች ውጤታማነትም ይህንኑ በተመለከተ ዕይታቸው በመግባባቱ ልክ ይወሰናል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም አንድ አባል አገር በሌላው አባል አገር የውስጥ ጉዳይ አይገባም የሚል ነባር የአፍሪካ አንድነት አንቀጽን ከመውረስ ባሻገር የፆታ እኩልትን፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን መከበርና የመልካም አስተዳደር መረጋገጥን የሚመለከቱ አንቀጾች ማካተቱ፣ እንዲሁም የጦር ወንጀሎችና በሰው ልጅነት ላይ የሚያርፉ የፍጅት ወንጀሎች በአባል አገር ውስጥ በተፈጸሙ ጊዜ ኅብረቱ ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅድና ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን የያዘ መንግሥትንም በኅብረቱ ውስጥ ከመሳተፍ የሚከለክል ትልልቅ ድንጋጌ አስፀድቆ ትርምሶችን ለማብረድ፣ ወታደራዊ ግልበጣን ለማስቀረትና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግርን ለማፅናት በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር እየታገዘ የጀማመረው ትግል ከጊዜው ጋር የገጠመ ጉልህ ለውጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አያያዝንና የዘመኑ የተገደበ የሥልጣን ቆይታን ቋሚ የድጋፍና የቅዋሜ መለኪያ በማድረግ የፖለቲካ ጣጣዎችን ማቃናት አይቻልም፡፡ ዋና መለኪያ መሆን ያለበት የአገሮችን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ በደንብ እያስተዋሉ ማግለልም ሆነ ማዕቀብ ወይም ወታደር ማስገባት ቀውስን ያደርቃል ወይስ ቀውስ ያባብሳል? የሚለውን ጥያቄ በትክክል መመለስ ነው፡፡ በሩዋንዳም ሆነ በብሩንዲም ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሌለ፣ በሁለቱም አገሮች እ.ኤ.አ. በ2008 የተካሄደው የሕዝብ ድምፅ የተለጠፈበት ሥልጣን የማራዘም ክንዋኔ ፀረ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ሁኔታ ግን በአንድ ዓይን ሊታይ የማይችል ነው፡፡ የተሻለ አንፃራዊ ሰላምና ዕድገት በሚታይባት ሩዋንዳ ታላላቆቹ አገሮች የተጨመሩበት ማዕቀብና ማግለል ቢሰነዘር ቀውስን ለማምጣት የመተናነቅ ያህል ይሆን ነበር፡፡ የብሩንዲ ገዥ ለሦስተኛ ጊዜ ‹‹ተመርጦ›› በሥልጣን ለመቆየት ገና ሲወጥን ቅዋሜና ግርግር በጀመራትና ሥልጣን ማራዘሙ ከተከናወነ በኋላ በተባባሰባት ብሩንዲ ውስጥ፣ ከሞላ ጎደል ሕዝብ ተባብሮ ከገዥው ቡድን ጋር የተፋጠጠ (ገዥው የተነጠለ) ሆኖ ቢሆን ኖሮ የአፍሪካ ኅብረት ጦር ማስገባት የሕዝብን ፍላጎት የሚያግዝና ውጤቱም ፈጣን በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን በብሩንዲ ውስጥ ሕዝብ ገዥውን በመደገፍና በመቃወም የተከፋፈለ እንደመሆኑ ጦር ገብቶ ቢሆን ኖሮ ቀውስ ከማድረቅ ይልቅ ጭራሽ የማጦዝ ውጤት ሳይኖረው ባልቀረ ነበር፡፡ እናም ከኃይል መንገድ ይልቅ ደም መቃባት የጀመሩትን ወገኖች ወደ ዕርቅና ግልግል በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ቀዳሚና ፈጣን ጥረት ማድረግ (የጎረቤት ነገር አባባሽነት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ ለማስወሰድ ከመቁረጥ ጋር) ጊዜ የማይሰጥ ተግባር ሆኗል፡፡ የመንግሥት ግልበጣ ክንዋኔዎችንም እንዲሁ የተጀመረ ትርምስን ለማስቆም የመጡ ወይም ወደ ትርምስ የሚወስዱ በመሆን አለመሆናቸው መለካት ከስህተት ለመዳን ይጠቅማል፡፡

ዋናው ትግል ግን የፖለቲካ መናጋት የደረሰባቸውን፣ ፍጅትና ስደት የፈነዳባቸውን አካባቢዎች እያሳደዱ ለማቃናት በመሞከር ላይ አይደለም፡፡ ከትርምስ፣ ከፍጅትና ከጅምላ ስደት ጀርባ ብዙ ጊዜ የኢኮኖሚ ድህነት፣ የአስተዳደር መበላሸትና ቅሬታ ያጣመረ ማኅበረሳባዊ መገፋት ይገኛሉ፡፡ ቀደም ያሉት የእነሴራሊዮን ቀውሶችም ሆኑ የዛሬዎቹ የማሊና የማዕከላዊ አፍሪካ ዓይነት ቀውሶች የድቀት ውጤቶች ናቸው፡፡ እናም ረሃብን፣ የእርስ በርስ ግጭትንና ስደትን ከመመረታቸው በፊት ለመታገልና ለመቅጨት ከተፈለገ ዋና የትግል ትኩረት መሆን ያለበት አገሮች እንዲለሙ በንዋይ፣ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀትና በሥራ አመራር ክህሎት በማገዝ ላይ ነው፡፡ አፍሪካ ኅብረትም ጦር ከማሰናዳት በበለጠ በብዙ ዘርፍ ልማትን የሚያግዝ አቅም ሰንቆ ማተኮር ያለበት እዚህ ተግባር ላይ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የዴሞክራሲን ከወግ ማለፍ ሕዝብ ከዕድገት ጋር እንቅስቃሴው አድርጎ እስኪያመጣው ጠብቆ በመደገፍ መወሰንም ሳይዘነጋ፣ በተናጠል የማይገታ አገር-አለፍ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ንጠት የሚመላለስባቸውን ሥፍራዎች ወደ አካባቢያዊ መሰባሰብ እንዲመጡ ማማከር ሳይበጅ አይቀርም፡፡ በዚህ አቅጣጫ ለመሄድ ቢሞከርም እንኳን ጉዞው አልጋ በአልጋ አይሆንምና በሆነ ቦታ ቀውስ ባርቆ መንግሥት ‹‹ሕጋዊ›› ተቀባይነቱን ሊያጣና ለመውረድ ባልፈቀደ ገዥና በተቃዋሚ ግትርነት አገር የተቀሰፈችበትና የምትታመስበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የዚያ ዓይነቱን የማይነቃነቅ ፍጥጫ፣ ሕዝብን በሚበጅ አኳኋን ለመቁረጥ የሚቻለው ከመንግሥት ተብዬም ሆነ ከተቃዋሚ ተብዬ በላይ በሁለት በኩል የተሰነገውን ሕዝብ ክቡርነትና ታላቅነት አብልጦ ለማየት የሚያስችል የአመለካከትና የፖለቲካ ስንዱነት ሲኖር ነው፡፡ ሶሪያ አምስት ዓመታት በፈጀና ገና ባላበቃ ጦርነት የወደመችው፣ ሩብ ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ሊያልቅባትና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝቧ ሊፈናቀል የቻለው የዚህ ዓይነት አሳቢነት ታጥቶ ነበር፡፡ ለዚህ ግፍ ተጠያቂዎቹ የውስጥ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ አቀናባሪዎችም ናቸው፡፡ ከዚህ ልምድ አፍሪካውያን በእጅጉ መማር አለባቸው፡፡  

የኢትዮጵያ አንድ ልብ የመሆን ፈተና

እስካሁን ከተባለው ከኢትዮጵያ ተቀናንሶ ትንንሽ አገር የመፍጠር ፍላጎት ከዘመኑ የጉዞ አቅጣጫና ሕይወትን በዕድገት ከማቃናት ጋር እንደሚጋጭ መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጋር የተያያዘ እውነታ ከዚህም የተለየ ፈተና አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ክፍለ አኅጉራዊ ትስስር ብትፈጥር እንኳን የኢትዮጵያ የልማት ግስጋሴ ሁሌ በዓይነ ቁራኛ መታየቱና የአየር ንብረትና የፀባይ ለውጥ መጠርጠሪያዋ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ንዶ እንደገና አካባቢ አቀፍ ስብስብ መፍጠር ቀላል የሚመስላቸው ቢኖሩ መቀናነስ፡፡ እየተጨፋጨፉ መርገፍ፣ የሚሊዮኖች መሰደድና ፍርስራሽ በፍርስራሽ መሆን ማለት እንደሆነ ዛሬ በሌሎች ላይ እየደረሰ ያለውን ቢያስተውሉ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና በዕድገት ጎዳና መጓዝ ከክፍልፋዮች ይልቅ አያያዥ ፈርጥ ማግኘትን እንደሚሻ ቢረዱ ለሁሉም ይበጃል፣ ይህ ጥቅል ሀቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ብቻ ወደሚመለከተው ሀቅ ደግሞ እንምጣ፡፡ አሁንም ከዚህ ይሰውረን እንጂ ኢትዮጵያ የመናድ ሒደት ውስጥ መግባት ይቅርና በውስጥ ቁርቁስ ወደ ደካማነት ብታመራ፣ አቅጣጫ ቀይሮ የመዞር ነገር በፈረሰኛ ውኃ ከተጠለፉ በኋላ አምልጦ እንደመትረፍ ይከብድባታል፡፡ ደክሞ ከማገገም ይልቅ ወደ መበታተን መሄድ ይቀላል፡፡ ከተበታተኑም በኋላ መልሶ ‹‹በአዲስ›› መልክና ጥንካሬ ከመሰባሰብ ይልቅ በብጥስጣሽ ሰላም የለሽነት መቀጠል ቀላል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ቁርጥራጮቿን የእርስ በርስ ቅራኔ ከሚያናጫቸው ባሻገር የጎረቤት ግዛት አለን ባይነት በየአቅጣጫው የምንተፋ እጁን የሚሰድበት፣ በሌላ ገጽም ‹‹ከቀድሞዋ›› ኢትዮጵያ ከሚወጡ ወንዞች ጋር ህልውናቸው የተያያዘ ወገኖችም ከትርምስና ከድቀት አዙሪት እንዳይወጡ ለማድረግ ብዙ ድንጋይ ሊፈነቅሉ የሚችሉበት ጥሬ ዕድል የቀውስ ጊዜን ጠብቆ ስለሚያፈጥ ነው፡፡

ከእነዚህ ነጥቦች ማጠቃለል እንደሚቻለው፣ ኢትዮጵያ የምታካሂደው ከጎረቤቶቿ ጋር የተሳሰረ የልማት ጥረት ሁሉንም አቻችሎ የሚጠቅም ሆኖ እንዲቀጥል የመግራቷ ጉዳይ፣ ፍትሐዊ የጋራ ጥቅምን ከፍ አድርጎ ከማቀንቀን ባሻገር ሌላ ነገር ይጠይቃታል፡፡ ይህ ነገር ፀሎት ወይም እንተማመን እያሉ መማማል ሳይሆን፣ በውስጣዊ ፖለቲካዋ አንድ ልብ ሆኖ የመገኘት ጥንካሬ ነው፡፡ ይህንን ጥንካሬ ማሟላትና አለማሟላት በቀጥታ የስኬት ዕጣዋን ይወስናል፡፡

አንድ ልብ መሆን ይህን ያህል ዕጣችንን ከወሰነ፣ ውስጥ ለውስጥ ከመቋሰልም ሆነ በድንገተኛ ቁጣ ከመንጎል መገላገል የተሳነን ለምንድነው?

1). ሕገ መንግሥቱ አደናቅፎን ይሆን ወይስ ሕገ መንግሥቱን አደናቅፈነው?

‹‹ፌዴራላዊ ዴሞክሲያዊ ሪፐብሊክ›› የተሰኘችው ኢትዮጵያ ነፃ የሆኑ የተለያዩ አገሮች የኅብረት አገር ለመሆን የመፈለግን ጉዳይ በየአገራቸው ሕዝብ ካስወሰኑ በኋላ፣ ለጋራ ጉባዔ የየአገር ተወካዮቻቸውን ልከው ያቋቋሟት አገር አይደለችም፡፡ እንዲያ ሳትሆን፣ ፊትም የነበረች ግን በሕገ መንግሥት ጉባዔ ነባር የግንኙነትና የአወቃቀር መሠረቷን ቀይራ የቀጠለች አገር ነች፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በመግቢያው ላይ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ…›› ብሎ መጀመር የቻለው ለዚህ ነው፡፡ በመግቢያው (ገጽ 5-6) ውስጥ የተቀመጡት መሠረተ ሐሳቦች፣

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 2፣ 8፣ 9፣ 40፣ 50፣ 51፣ 52 እርስ በርሳቸውና ከቀሪዎቹ አንቀጾች ጋር ተገናዝበው ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ አካል ያላት አገር መሆኗን በግልጽ ያሳያሉ፡፡ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ ግዛት የፌዴራል አባላቱን ወሰን የሚያጠቃልል መሆኑን ሲያሳውቅ፣ አንቀጽ 40 (3) ‹‹… መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው›› ብሎ ያውጃል (ሰረዝ የተጨመረ)፡፡ ሕጉ ይህንን ቢልም መሬትን የየክልልና የየብሔር ብሔረሰብ ንብረት አድርጎ የቆጠረ ብሔርተኛ አስተሳሰብ ሕዝብ ውስጥና መንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ ሲያሳስትና ጥፋት ሲያሠራ እናገኛለን፡፡

አንቀጽ 8 (1) ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፤›› ሲልም በማያሻማ ሁኔታ የአገሪቱ ሥልጣን አዛዥነት የፕሬዚዳንት ወይም የጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን የእነሱ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ አዛዥነታቸው (የሥልጣን ባለቤትነታቸው) የሚገለጸውም በተወካዮቻቸውና በቀጥተኛ ውሳኔያቸው አማካይነት ነው (አንቀጽ 8፡3)፡፡ እነዚህ ንዑስ አንቀጾች በብሔርተኛ አዕምሮ ውስጥ ውላቸውን ስተው ልክ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ሉዓላዊ ህልውና ያለው ተደርጎ ይታሰባል፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ወይም ክልል በተመድ የታወቀ ይዞታ ያለው፣ የውጭ ግንኙቱን ራሱን ችሎ የሚመራ ቁመና በኖረው፣ ኢትዮጵያም ፌዴራል ሪፐብሊክ ከመሆን ይልቅ ኮንፌደሬሽን ወይም የአውሮፓ ኅብረት ዓይነት ማኅበረሰብ በሆነች ነበር፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት  መሠረት ክልላዊ መንግሥታት የኢትዮጵያ አካል እንጂ በየራሳቸው ሉዓላዊ አይደሉም፡፡ አገሪቱን በጥቅል የሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙት ወደ የክልሎች ወርደው ታይተው ሳይሆን፣ ‹‹ተጠሪነቱ ለአገሪቱ ሕዝብ በሆነው›› በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ነው (አንቀጽ 50፡3)፡፡

ከታች ጀምሮ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ደረጃ ያሉ የሥልጣን አካላት በሕዝብ ወሳኝነት እንዲደራጁና እንዲመሩ የደነገገ፣ ክልል ገብ ጉዳዮችን ለክልሎች፣ ክልል አለፍና ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለፌዴራል ለያይቶ የሰጠ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አስማምቶ ለማስተዳደር በፍፁም አያንስም፣ አይጠብም፡፡ አንዳንዶች ለልብ መከፋፈል የዳረገን ባሻ ጊዜ የራስ ክልል ከመፍጠር አንስቶ ከኢትዮጵያ እስከ መለየት ድረስ የሰፉ መብቶችን የሰጠው ሕገ መንግሥት  ነው ብለው ያስባሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እነከሌን ምን አካሰሳቸው ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ከመሞከር ፈንታ፣ የመክሰስ መብትን ጥፋተኛ በሚያደርግ መንገድ ውስጥ የሚነጉድ ነውና ችግራችንን ወደ ማወቅ አያደርሰንም፡፡

ችግራችን ያለው እኛ ሰዎቹ ዘንድና ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ አሟልተን አለማክበራችን ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥልጣን በመላ ሕዝቦቿ ባለቤትነት ውስጥ ገብቷል የሚል እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ቆንጥጦ (አጠቃላይ እምነት ሆኖ) አይገኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሥልጣን በአንድ ፓርቲ እጅ ነው የሚለው ግንዛቤ ተንሰራፍቷል፡፡ እንዲያውም ያለ ማድበስበስስ የኢትዮጵያ አገዛዝ ‹‹ሲም ካርድ››  ሕወሓት ነው እስከማለት የሄደና በተራ ሰው ደረጃ የሚፈሰፈስ ግንዛቤ አለ፡፡ ይህ የፈለቀው ከተንኮል አዕምሮ ሳይሆን እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የሥልጣን መዋቅሮች ከአንድ ፓርቲ ወገናዊነት ተላቀው ባለመደራጀታቸውና ጭራሹኑ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በፓርቲ መቃኘታቸውን ትክክለኛና አስፈላጊ አድርጎ፣ ከመዋቅሮቹም ባለፈ የሕዝቦችን ማኅበራዊ ህሊና በአስተሳሰቡ መቆጣጠርን ትግሌ ብሎ በመያዙ ነው፡፡ የችግሮቻችን እናት የሆነው ችግር ይኼው ነው፡፡ የፓርቲዎች ፖለቲካ ከጠላትነት እንዳይወጣ አድርጎ የቀሰፈው፣ የምርጫ ሜዳዎች ከፓርቲ ጫና ነፃ እንዳይሆኑና የምርጫ ሒደቶች እውነተኛ የውድድር ነፍስ እንደይኖራቸው ያደረገው፣ ምክር ቤቶች እስከ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ የእኛ/ዓለታችን ከመባል ይልቅ በኢሕአዴግ ይዞታነት እንዲታዩ ያደረገው፣ በአጠቃላይም ለመንግሥት የተቀባይነት ጉድለት ምክንያት የሆነው ይኼው ችግር ነው፡፡ በዚህ ላይ በሚስጥራዊነት የተሞላው የኢሕአዴግ መንግሥታዊ አመራር ተጨምሮበት በጥርጣሬ መታየት ሌላ የማይላቀቅ አበሳ ሆኗል፡፡

2) ቁርጥራጭ የብሔርተኛ አመለካከት መንገሥ

በኢሕአዴግ ጽሑፎችና ንግግሮች ውስጥ ብሔር/ብሔረሰብነትንና ማንነት አንዳቸውን ለአንዳቸው ተለዋጭ አድርጎ መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ማንነት ሲሉ ብሔር/ብሔረሰብነት ማለታቸው ነው፡፡ ይህንኑ መሠረት ያደረገውና የራስን ማንነትን ማወቅ፣ የሌላውን ማንነት ማወቅ፣ በመፈቃቀድ የጋራ ማኅበረሰብ መገንባትና የማንነት አካባቢን ማልማት የተሰኙ አገዳዎች ያሉት ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ክፍለ አኅጉራዊና አኅጉራዊ መተሳሰብን ለሚሻው ሰፊ እውነታ ይቅርና ለኢትዮጵያም የውስጥ ሥምረት የሚያንስ ነው፡፡ ብሔር/ብሔረሰብነትን የማንነት መለኪያ ማድረግ መጥበብም ከዘመን ወደኋላ መቅረትም ነው፡፡

ቋንቋ የማንነት አንድ ገጽታ እንደሆነ ሁሉ ሃይማኖትና ባህልም የማንነት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ብዙ አካባቢዎችን ያወናጨፈ፣ ብዙ መሰያየፍና መዘናነቅ የታየበት ረዥም የአገር ግንባታ ታሪክም የማንነት ገጽ ነው፡፡ ብዙ ቋንቋዎችና ባህሎች የተንቆጠቆጡበት ሕይወት አካል ሆኖ መገኘትም ማንነት ነው፡፡ የጥቁርነትና የአፍሪካዊነት አበሰኛ ታሪክም ማንነት ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ የማንነት ዘርፎች መዋያ የሆነው የሰው ልጅነት ደግሞ ለሁሉም መሠረት የሆነ ማንነት ነው፡፡ እነዚን መሰሎቹ የማንነት ገጾች በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ሁሉ በአንዴ የሚታዩ ሆነው ሳለ፣ ብሔርተኝነት ግን ሌሎቹን ሳጥን ውስጥ አቆዩና በብሔር/ብሔረሰብ ማንነት አጊጡ ባይ ነው፣ በተግባራዊ ፖለቲካው፡፡ ገጸ-ብዙ ማንነታችንን ዘርግተን ‹‹የራስን ማንነት ማወቅ፣ የሌላውን ማንነትም ማወቅ›› በተሰኘው ቢጋር መሠረት ማዶ ለማዶ የሚነፃፀር የየብቻ ማንነት ለመፈለግ ብንሞክርም፣ የራሳችንን ማንነት በሌላው ውስጥ፣ በራሳችንም ውስጥ የሌላውን ማንነት እናገኘዋለን፤ በሌላ አባባል የቋንቋ/የባህል ወዘተ. የሚባሉ ልዩነቶች ሁሉ የተወሳሰበ የጋራ ማንነታችን ዥንጉርጉር አካላት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እውነታ ስናጤንም፣ እንደ አገር አብሮ ለመቀጠል ‹‹መፍቀዳቸው›› በእኩልነትና በነፃነት አብሮ መኖር የግስጋሴያቸውና የሰላማቸው ዋስትና መሆኑን የማወቅ ውዴታ ነው፡፡ ሁሉን ያዳረሰ ተመጣጣኝ ልማትና የተሳሰረ ኢኮኖሚ የመገንባት ትግል የሚያደርጉባት ኢትዮጵያቸውም ብትሆን ለክፍለ አኅጉራዊና ለአኅጉራዊ የላቀ መስተጋብር የሚዘጋጁባት ትንሿ ቤታቸው ነች፡፡ በዚህ ዓይን፣ ‹‹የማንነት አካባቢን/ብሔራዊ ክልልን የማልማት›› አደራን የሚያስታጥቅ ብሔርተኛነት አላታሚ ነው፡፡ የልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ተወላጆች ሁሉ ሥራና ኑሮ በየመገኛ ብሔር የተገደበና ሊገደብ የማይችል እንደመሆኑ፣ የትም ኑር የትም ሥራ ዞሮ መግቢያህን ማልማት ግን አትርሳ የሚል ‹‹ንቃት››፣ ‹‹የወንዝ ልጅ›› እና ‹‹ባይተዋር/መጤ›› የሚሉ መከፋፈልንና ከብሔራዊ ተወላጅ ውጪ የሆነን ሰው ‹‹አጫራሽ›› አድርጎ ማየትን ተገቢ የሚያደርግ ነው፡፡

የተወሰኑ አካባቢዎች ወደፊት ተራምደው የተወሰኑ ወይም አንዱ ወደኋላ መቅረት ለጠቅላላዋ ኢትዮጵያ የሚነዘንዝ ቁስል ነው የሚሆነው፡፡ የሁሉም የተመጣጠነና የተሳሰረ ልማት መሟላት ደግሞ ለሕዝቦቿ ጠቅላላ ጤና ይሆናቸዋል፡፡ እናም ሁሉንም አካባቢዎች ለኢንቨስትመንትና ለሥራ መስፋፋት ሳቢ ማድረግና የሁሉን አካባቢ ቀርነት የራሴ ጉዳት ብሎ ለልማታቸው መረባረብ፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላሉበት ፈታኝ ሁኔታ የሚስማማው አመለካከት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ርቀን በብሔር/ብሔረሰብነት በተሸነሸኑ ትንንሽ ዕይታዎች ውስጥ እስከተሸጎጥን ድረስ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ሁላችንንም የሚመለከቱ ሰብዓዊ መብቶች በየትኛውም አካባቢ ኑሮ የመመሥረት መብትን (አንቀጽ 32)፣ እንዲሁም በዘር፣ በብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በትውልድ፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አቋምም ሆነ በሀብት ያለመንገዋለል መብትን (አንቀጽ 25) በአመዛኙ ያሳካ (ቁጣ የማያረግዝ) ሰላም መቀዳጀት ይሳነናል፡፡ የዚህ ዓይነት ፈርጆች ያሏቸው መሠረታዊ ችግሮች የአስተዳደር በደል፣ ሙስና፣ የብሔርተኛና የትምክህት ጥበት እየተስፋፉ መልካም ግንኙነቶችን እንዲያቆስሉ፣ ምሬትና ጥላቻም እንዲያመርቱ ዕድል ይሰጣሉ፡፡

የያዝነውን ነጥብ እንደገና ቁልጭ እናድርገው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቦቿን በአንድ ዓላማና ልብ አገናኝቶ ማትመም የሚችል አንድም ፓርቲ የለም፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ 24 ዓመታት በሥልጣን ቆይቶም አልተሳካለትም፡፡ ተቃዋሚዎቹም ለየብቻ ይቅርና አንድ ላይ ገጥመውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አትማሚ ለመሆን አይችሉም፡፡ ለዚያ የሚያበቃ ባህርይ ሲያሳዩም ገና አልታዩም፡፡ የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ፍጥጫ ያተረፈልን ነገር ቢኖር የእነሱን ገንታራ ሽኩቻ ወደ ሕዝብ የማስተላለፍ ችግር ነው፡፡ ፖለቲካዊ መጠማመድና ሕዝብና ገዥ የማይተማመኑበት ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስም ድንገት በሚፈነዳ ቁጣና ትርምስ የመበላት አደጋ አብሮን ይቆያል፡፡ የዚህ ዓይነቱን አደጋ የመከሰት ዕድል አምክኖ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እጅ ለእጅ አያይዞ በዴሞክራሲና በእኩልነት ሰላምን እየተመገቡ በዕድገት ወደ የሚገሰግሱበት ኑሮ ለመምራት በዛሬ ጊዜ ያለው ቀዳዳ አንድ ነው፡፡ ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ ጠበኛ መወነጃጀልን አቋርጠው በኢትዮጵያ የፖለቲካና የአስተዳደር ሜዳ ውስጥ የደረሱ ብልሽቶችን ለማቃናትና ዴሞክራሲን ለመገንባት ተባብረው ለመቆም ከቻሉ ነው፡፡

ፖለቲከኞቹ (የብረት ትግል ጀምረናል ያሉት ጭምር) የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከትርምስ ያመለጠ የነፃነት፣ የዕድገትና የብልፅግና ኑሮ መቀዳጀት ከምንም ነገር በላይ የሚያበልጡ ከሆነ አብሮ መሥራታቸው የሚቻል ነው፡፡ ይህ ጽሑፍም ከየቡድናዊ የሥልጣን ጥቅማቸው ይልቅ የሕዝቦችን የጥቅም ሚዛን ከፍ አድርጎ ይጠይቃቸዋል፡፡ የ2008 ዓ.ም. የኅዳርና የታኅሳስ ቁጣ ሳያዳግመን፣ በኢትዮጵያ አገዛዝና የፖለቲካ ሜዳ ላይ ያለውን ብልሽት ተባብሮ ለማስተካከልና በሕዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ሥር የሚያድር አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል ምን መርሐ ግብር አላቸው? ከሁከቱ ጀርባ ፀረ ሰላሞች/አሸባሪዎች እንዳሉበት፣ እንዲያውም በጎንደርና በምሥራቅ በኩል ታጣቂዎች የማስገባት ሙከራ እንዳለ ሁሉ ከኢሕአዴግ ሰዎች ተነግሮናል፡፡ (ሪፖርተር ጋዜጣ ታኅሳስ 10 ቀን 2008 ዓ.ም.) ‹‹ቆይታ›› ዓምድ ላይ፣ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ቃለ መጠይቅ ይመለከቷል) እናም በትጥቅ ትግል የመታመስን ቀዳዳ በሰላም መንገድ የመዝጋት ፖለቲካ የሚጀመረው ምን ደረጃ ላይ ሲደረስ ነው? ኢሕአዴግ ለሚከሳቸው ወገኖች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥቅም ሲል፣ የሚያቀርብላቸው የሰላም ጥሪ አለው? ተቃዋሚዎቹስ ከእሱ ካልመጣ ሳይሉ ለኢሕአዴግ የሚያቀርቡለት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ጥሪ ምን አላቸው? በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብን የሚያከብሩና በሕዝብ ሥር ማደርን ዓላማቸው ያደረጉ ፖለቲከኞች ካሉ፣ እነዚህ ጥያቄዎች የንፋስ ራት ሆነው አይቀሩም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ‹‹ቆመንላችኋል›› የሚሏቸውን ፖለቲከኞች በእነዚህ ጥያቄዎች መመዘን ይኖርባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡