እኔ የምለዉ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብር ዋጋ መውረድ (የመጨረሻ ክፍል)

አንባቢ

ቀን: September 22, 2024

በነጋድራስ ካሳ

ባለፉት ሁለት ክፍሎች የአገራችን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብር ዋጋ መዳከም ምክንያትና መንስዔዎችን በመመልከት፣ መንግሥት (በብሔራዊ ባንክ) አሁን የወሰደው የምንዛሪን ግብይት ተንሳፋፊ (Floating) ማድረግ ጥቅሙንና ጉዳቱን ከሞላ ጎደል ለመመልከት ሞክረናል፡፡ ሲጠቃለልም ተንሳፋፊ ግብይት ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና አፈጻጸም ሊያሳድግ እንደሚችል በመደምደም፣ ነገር ግን ይህ አካሄድ ዘላቂና በተደላደለ መሠረት ላይ መቆም ይችል ዘንድ ሌሎች ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ተጓዳኝ (Complementary) የፖሊሲ ማዕቀፎችና በሽግግሩ ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን በተመለከተ በይደር ያቆየናቸውን ሁለት ጥያቄዎች በዚህ የመጨረሻ ክፍል እንመለከታለን፡፡

ሀ). የሽግግር ጊዜና ውዥንብር

1ኛ) ይህ ውሳኔ ያልተጠበቀና ድንገተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ቁጥጥር አፍቃሪ (Control Freak) መንግሥት፣ ልሂቅና ማኅበረሰብ ባለበት አገር ድፍረት የተሞላበት የነፃ ገበያ አዋጅ ሲነገር መደንገጥ፣ መደናበርና ግራ መጋባት የሚጠበቅና የማይቀር ነው።

(እዚህ ላይ ከዘመነ ዘውድ አገዛዝ ወጥተን አብዮት የሚባል ነገር በዚህች አገር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ትውልድ፣ ማኅበረሰብና መንግሥት የሶሻሊዝም መገለጫ በሆኑ ብዙ ጉዳዬች የተጠለፈና ከእነዚህም አንዱ ‹ቁጥጥር› መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል)።

    እናም ይህ እንበለ ቁጥጥር (Laissez-Faire) ፖሊሲ ብዙዎችን በማስደንገጥ ቀደም ሲል እንደተገለጸው አብዛኛውን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚና የቢዝነስ ባለሙያ የሆኑና እዚያው የውጭ ምንዛሪ ንግድ ላይ እየሠሩ በሚገኙ ፕሮፌሽናሎች ጭምር ድንጋጤና ሽብር ፈጥሮ፣ ‹ከእንግዲህ ተስፋ ቆርጠናልና አበቃልን› ከሚል አስተያየት ጀምሮ ጥቅሙና ጉዳቱን በተቻለ መጠን ሳያብራሩልን ተሸብረው አገሩን የሚያሸብሩ አስተያየቶችን እያደመጥን እንገኛለን፡፡ መቼም ማኅበራዊ ሳይንስ በተለይም ደግሞ ኢኮኖሚክስና ቢዝነስ አንዳችን ያየንበት መንገድ ከሌላችን የሚለይበትን እየተነጋገሩ ሐሳብን በማዳበር የሆነ መቋጠሪያ ነገር ላይ ለመድረስ መሞከር እንደመሆኑ፣ በትምህርትና በሙያችን ቅርብ ነን የምንል አስተያየቶቻችንን በደፈናው በመወርወር ነጋዴውንና ማኅበረሰቡን ከማስደንገጥና ከመረበሽ ይልቅ፣ ሐሳቦቻችንን በምክንያትና በዕውቀት ገልጸን ለማስረዳት ብንሞክር ጉዳዩን አሁን እያየን ባለው ደረጃ ድንጋጤና መደናበር ይልቅ በዕርጋታና በጥሞና እንድናስተናግደው መርዳቱ አይቀርም ነበር፡፡

2ኛ). ባለሙያውና ጎምቱው ምሁር ከተደናገጠ በኋላ የንግድ ማኅበረሰቡና የሕዝቡማ ሊገርመን አይችልም፣ አይገባም፡፡ በአንድ በኩል ይህ ዓይነቱ ድንጋጤ የሚጠበቅ የመሆኑን ያህል ብዙ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን የዘጉ፣ ሸቀጦቻቸውን በመጋዘን ቆልፈው የተቀመጡ፣ አስመጪና ላኪዎችን ብቻ ሳይሆን ከውጭ ምንዛሪ ጋር ፍፁም ግንኙነት የሌላቸውን ቤትና ቦታ ሻጬችን፣ አትክልትና ፍራፍሬ አከፋፋዮችን፣ ጤፍና በግ ነጋዴዎችን፣ ወዘተ… አስደንግጦ ሱቅ አዘግቶና ግራ አጋብቶ ይገኛል።

    በመሠረቱ ይህ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን የማንም ነጋዴ ትክክለኛ (Rational) ግብረ መልስ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በየትም አገር በጠቅላይ ሚኒስትርና በብሔራዊ ባንክ ገዥ ደረጃ የተነገረን ይህንን መሰል አዋጅ ቀርቶ የባንክ ወለድ ሲቀየር፣ የሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ አሠራሩን ሲቀይር፣ ያልተጠበቀ የስቶክ ገበያ ውጤት ሲከሰት፣ ወዘተ… ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብና ሒደቱን መከታተል የግድና የማይቀር ክስተት ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን ክስተት መንግሥትና የብ.ባንክ ኃላፊዎች ሊጠበቅ የሚገባው መሆኑን አስቀድመው መረዳት የሚገባቸውና ተገቢውን ማብራሪያና ገለጻ በመስጠት ማስረዳትና ተከታታይ የግንዛቤ መስጨበጫ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

3ኛ). ይሁን እንጂ ይህ ጽሑፍ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት እየሰማን ካለው መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው፣ ግራ ዘመሙ መንግሥታችንና የመንግሥት ሲቪል ሠራዊት የተለመደውን የማስጠንቀቂያና የማስፈራሪያ መግለጫውን እየሰጠ ይገኛል፡፡

  እዚህ ላይ ድንጋጤና መረበሹን በማብራሪያና በገለጻ የማስረዳቱ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ገበያውን ማረጋጋት የሚቻለው የውጭ ምንዛሪውን አቅርቦት በማሳየትና የዕቃዎች (በተለይም ወሳኝ የሆኑ የገቢ ዕቃዎች) እጥረት ሊኖር እንደማይችል በመግለጽና በተግባርም የውጭ ምንዛሪ ለሚጠይቁ ሁሉ ባንኩ ሊያቀርብ እንደሚችል በማሳየትም ጭምር ነው፡፡

   ስለሆነም ባንኩ አስፈላጊ ከሆነም እነዚህ እጥረት ሊታይባቸው ይችላል ብሎ ያሰባቸውን ዕቃዎች በዝርዝር በማውጣት ጭምር፣ እነዚህን ዕቃዎች (ካስፈለገም) በስም በመዘርዘር ከውጭ ማስመጣት ለሚፈልጉ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ መውሰድ የሚችሉ መሆኑን በይፋ በሚዲያ እስከ መግለጽ የደረሰ ዕርምጃ ቢወስድ፣ ነጋዴውንም ሆነ ሸማቹን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ይህንን ዜና የሚያደምጥ ማንም ነጋዴ አሁን ዶላር በ120 ብርና ምናልባትም እየጨመረ ቢሄድም እንኳን፣ ቢያንስ ቀደም ሲል ከነበረው የጥቁር ገበያ እስኪደርስ ዕቃውን መጋዘን ውስጥ አስቀምጦ መቀጠል ለሌላ ኪሳራ ስለሚዳርገው ቶሎ ሽጦ ማገላበጥ እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም፡፡

  ከዚህ ውጪ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ከዚያም ከፍ ሲል የንግድ ቤቶችን የማሸግ ተግባር፣ ግለሰብ ነጋዴ ዜጋውን በግል ያላግባብ ከመጉዳት በላይ፣ የታሸገበት ነጋዴን ንብረትና ሸቀጥ ከገበያ ውጪ በማድረግ በገበያው ላይ ተጨማሪ እጥረት በመፍጠር፣ ውጥረቱን ከመባባስ፣ የሽግግሩን ጊዜ በማርዘምና በማወሳሰብ በፖሊሲው በጎ ጎን ላይ ጥላሸት ከመቀባት ውጪ አንዳችም የሚፈይድ ነገር እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል፡፡

   ቁጥጥር፣ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ከፍ ሲልም ቅጣትና የዜጋን ንብረት ከሕግ ውጪ ማሸግና መውረስ፣ መሠረታዊውን የሰው ልጅ መብትና የኢትዮጵያን ሕግ የሚጥስ ሕገወጥ ተግባር ከመሆኑም በላይ፣ ግለሰብ ነጋዴዎችንና ዜጎችን መጉዳትና ‹መበቀል› ይቻል ይሆናል እንጂ፣ የተፈለገውን የኢኮኖሚ ውጤት ግን ከቶም ሊያስገኝ እንደማይችል ላለፉት 50 ዓመታት አልሠራም፣ አሁንም አይሠራም፡፡

4ኛ). ሌላው የአንዳንድ ምሁራንን አስተያየት ‹እንደግፈዋለን፡፡ ነገር ግን አሁን ወቅቱ አይደለም ወይም ሊሆን አይገባም› ዓይነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በቅድሚያ ለምንድነው አሁን ወቅቱ ያልሆነው? እናስ መቼ ነው ያ ወቅት? ለሚለው ለእኛ ላልገባን አሊያም በተቃራኒው ለገባን እንዲያስረዱን እንጠብቃለን፡፡ እኔና መሰሎቻችን ግን እጅግ ዘግይተናል ባይ ነን፡፡ አሁን ስላለንበት ደረጃ ከላይ በክፍል አንድ በሰፊው ስለተገለጸ አልመለስበትም፡፡ እናም ይህች አገር አሁን ካለችበት አዘቅት ለማዳን በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ የተወሰደው ዕርምጃ እንኳንስ አሁን እየገለጽን ባለው ደረጃ የሆነ አዎንታዊ ምክንያት እያለው ቀርቶ፣ በጎርፍ ከመወሰዳችን በፊት ምንም ዓይነት ዕርምጃ ወስደን ጎርፉን መሻገር የግድ ነው፡፡      እዚህ ላይ የተወሰደውን ተንሳፋፊ ግብይትን ውሳኔ መቃወም ብቻ ሳይሆን በነበረው መቀጠሉ ይሻል ነበር ነው? ወይስ ሌላ አማራጭ ካለ እንዲነገረን እንጠብቃለን፡፡

5ኛ). ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ እኔ አስተያየት ይህ ወቅት ትክክለኛው ጊዜ የሚሆነው በመዘግየታችን ብቻ ሳይሆን፣ የዚህ ፖሊሲ ዋናው ተግዳሮትና ሥጋት የሽግግሩን ጊዜ ተንገዳግዶም ቢሆን መውጣት ነው፡፡ የሽግግሩን ጊዜ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸውና በአዋጁ ምክንያት ወደ ሕጋዊው መስመር በመምጣት የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ይሆናሉ ያልናቸው አካላት ከድንጋጤና ከውዥንብር ወጥተው እስኪመጡ ድረስ ያለው ፈተና ነው፡፡ ይህንን ፈተና ከሚያከብዱት አንዱና ዋነኛው ደግሞ እነዚህ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች እስኪመጡ ድረስ የሚቀርቡ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎችን ማስተናገድ መቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ከለጋሽና አበዳሪ ተቋማት ጋር ሲያደርግ የቆየውን እልህ አስጨራሽና ፈታኝ (አንዳንዶቻችን በግል እንደተከታተልነው) ሒደት በድል አጠናቆ፣ ለዚህ ሽግግር ጊዜ የሚሆን በቂ የውጭ ምንዛሪ መያዙ ይህንን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜ ያደርገዋል፡፡

6ኛ) በሌላ በኩል ግን በዚህ ውሳኔ አንዳንድ በበቂ ሁኔታ ያልተሄደባቸውና ለጸሐፊው ግልጽ ያልሆኑለት፣ ነገር ግን በአፋጣኝ ሊታረሙ ይገባቸዋል የሚል ፅኑ እምነት የወሰደባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ወደ ውጭ ላኪ ነጋዴዎች ለግል ሊጠቀሙበት የሚችሉትን (የሚገባቸውን) መጠን በተመለከተ በኢንዱስትሪ ዞን የተካለሉና ያልተካለሉ በሚል ለይቷቸዋል። ይህም ማለት እንደሚታወቀው በኢንዱስትሪ ዞን የተካለሉ ማለት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የማምረቻ ቦታ (Industrial Plot) ገዝተው/ተከራይተው የሚጠቀሙ በአብዛኛው የውጭ ዜጎችን ምንዛሪያቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት የተፈቀደ ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ ያሉ ማለት ደግሞ መሬት በሊዝ ገዝተውና ወይም ከአገሬው ዜጋ ተከራይተው እየሠሩ የሚገኙ የአገሬው ሥራ ፈጣሪዎች (Indegnious Entrepreneurs) 50 በመቶ ብቻ እንዲጠቀሙ አዋጁ ደንግጓል፡፡

  እንግዲህ ይህ እንቀጽ ከአገሬው ሥራ ፈጣሪ ይልቅ የውጭ ኢንቨስተር ይሻለኛል ወይም ይበልጥብኛል የሚል የኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካና የዜግነት መብት ጥያቄ የሚያስነሳ፣ እናም እየተወያየንበት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ግብይትን ተንሳፋፊ የማድረግ ዋነኛ ዓላማ በመሸራረፍ ከላይ የጠቀስነውን የጥቁር ገበያንና የኢንቮይስ ቅሸባን ያድናል ያልነውን ግብ የሚሸረሽር፣ በአጠቃላይ ፖሊሲውን ግማሽ ልጭ፣ ግማሽ ጎፈሬ የሚያደርግ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊስተካከልና ሊታረም እንደሚገባው በድፍረት ለመናገር አያግደረድርም።

7ኛ). ሌላው በውሳኔው ከተካተቱት ጉዳዮች አንዱ የሲቪል ሰርቫንት ሠራተኞችን ደመወዝ የመጨመር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የመጨረሻ (ነገር ግን ዋና ጉዳይ) ለመመልከት እንደምንሞክረው፣ ይህንን ፖሊሲ በዘለቄታ የተሳካ ለማድረግና የተፈለገውን ግብና ውጤት ማግኘት ይቻል ዘንድ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ሌሎች ተጓዳኝ፣ ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ የፖሊሲ ማዕቀፎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የመንግሥትን ወጪ በመቀነስና በመቆጣጠር ወደ ገበያ የሚገባውን የገንዘብ ፍሰት መቀነስ ሲሆን፣ በዚህ አዋጅ የተላለፈው የሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ የመንግሥትን ወጪ በመጨመር ለዋጋ ንረትና ለብር የመግዛት አቅም ማነስ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት የሠራተኞችን ገቢ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ምንም የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ ይህንን ግን ከደመወዝ ጭማሪ ይልቅ በታክስና በግብር ቅነሳ ቢደረግ ኖሮ የተሻለ ይሆናል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

     ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሠራተኞችን ደመወዝ መጨመር የመጀመሪያው ውጤት የሻጮች ዋጋን የመጨመር ሥነ ልቦናዊ ግብረ መልስ ነው፡፡ ብዙ ዓይነት የዋጋ መወሰኛ መንገዶች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ሁሌም ምንም ያህል ገበያውን ሊረብሹ ቢችሉ እንደ ሥነ ልቦና (Psychological Price) ዋጋ ኢምክንያታዊ፣ ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስና የትና መቼ ሊቆም እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ነገር የለም፡፡ ይህም አሁን የምንዛሪውን ውሳኔ ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር ያየነውን የዋጋ አለመረጋጋት የሚያበባስ ውጤት እንዳኖረው ያሠጋል፡፡ ስለሆነም ይህንን ወሳኔ ከደመወዝ ጭማሪ ይልቅ በታክስ ቅናሸ ቢደረግ ኖሮ የሠራተኛውን ፍላጎት ማሳካቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የመንግሥትን ወጪ በመቆጣጠር የተነሳንበትን የምንዛሪን አቅርቦት በማሳደግ በሽግግር ጊዜ ሊኖር የሚችለውን የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር የውሳኔውን ዓላማ በማሳካት ተገቢውን ድርሻ መወጣት ይቻል ነበር የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡

8ኛ) ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ጽሑፍ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ብሔራዊ ባንኩ በእጁ ያለውን ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ እየተዘጋጀ እንደሆነ እየተደመጠ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ ባንኮቹ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ለጨረታ የቀረበውን ጥቂት (ወይም አንድም ሊሆን ይችላል) ባንኮች እጅ ውስጥ በመግባት እነዚያ ጥቂቶች (ወይም አንዱ ባንክ) በፈለጉት ምጣኔ በመሸጥ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት ሊፈጥሩ እንዲችሉ ቀዳዳ የሚከፍት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ብሔራዊ ባንኩ ከጨረታ ይልቅ ሌላ መንገድ ቢቀይስ የተሻለ ይሆናል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ነፃ ገበያ ማለት ልቅና የተለቀቀ (Unregulated) ማለት ሳይሆን፣ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይችል ዘንድ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች የአሠራር ደንብና ሥርዓት አውጥቶ መምራት የማይቀር ነው፡፡

 ለምሳሌም ባንኮች በቅድሚያ ከደንበኞቻቸው የሚቀርበውን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ሰብስበውና መሟላት የሚያስፈልጋቸውን ሰነዶች አያይዘው የመግዣ ዋጋቸውን በመጥቀስ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ ቢደረግ፣ ብሔራዊ ባንክም የቀረበለትን ሰነድ እየመረመረ አስፈላጊ ከሆነም ጥያቄ የቀረበላቸውን የሸቀጥ ዓይነትና የመሳሰለውን መመዘኛ በማውጣት ጭምር በእጁ ያለውን ምንዛሪ ለሁሉም ባንኮች ማከፋፈል አንዱ ዘዴ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ዋነኛው ጉዳይ አቅርቦቱ መኖር እስከሆነ ድረስና ባንኮቹ ላቀረቡት ጥያቄ በሆነ ደረጃ እንደሚያገኙ እስካረጋገጡ ድረስ፣ በዚህ መንገድ የሚደረግ ውድድር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ትርፋማ መሆንን የሚያበረታታ ይሆናል፡፡ በመሠረቱ የብሔራዊ ባንክ ዋና ዓላማ ከምንዛሪ ሽያጭ ማትረፍ ሳይሆን የአገሩን ገበያ ማረጋጋት እስከሆነ ድረስ ራሱ ዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብን የሚያበረታታ (ለምሳሌም ከከፍተኛ ዋጋ ይልቅ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበ ባንክ ከጠየቀው መጠን ከሌሎች በተሻለ የሚስተናገድበትን ዓይነትና የመሳሰለ)፣ እንዲሁም የባንኮቹ መሸጫ ዋጋ ልቅና የተለጠጠ ሳይሆን በሆነ መቶኛ ውስጥ እንዲወድቅ በማድረግ የመሳሰሉትን ዓይነት የአሠራር ዘዴዎችን በመቀየስ ካልታገዘ ባንኮቻችን ሌላ ሥራቸውን ትተው በቀላል የውጭ ምንዛሪ ንግድ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ በሚያደርጉት አላስፈላጊ ውድድር የምንዛሪው ጣራ ቀደም ሲል ከነበረው ጥቁር ገበያም አልፎ ወደ ከፋ ቀውስ ሊወስደን ይችላል፡፡

ለ) የፖሊሲውን አሉታዊ ጎኖች ተቋቁሞ በጠንካራ መሠረት ላይ መጣል

ተግባርና ልምድ እንደሚያስተምረንና እንደሚያሳየን ይህንን ፖሊሲ ተከትለው የወደቁና የተሳካለቸው አገሮች አሉ፡፡ ይህንን ፖሊሲ የምንደግፈውን ያህል ሳይወድቅ በስኬት ይጓዝ ዘንድ የሚከተሉት አስፈላጊ እናም ወሳኝ (Complementary) ተግባራት ይፈጸሙ ዘንድ የግድ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህ ተግባራት እስካልተፈጸሙ ድረስ ፖለሲው ተግባራዊ አይሆንም ብቻም ሳይሆን፣ በመጨረሻም አገሪቱን ወደ ውድቀት የሚከት እንደሚሆን በአጽንኦት መገለጽ ያስፈልጋል፡፡

 1ኛ) የመጀመሪያው ዕርምጃ ከላይ እንደተጠቀሰው አምራቾች ምርታቸውን ወደ ውጭ እንዲልኩ ማበረታታት ነው። አንደኛውና ተገቢው ማበረታቻ የምርትና ምርታማነት አቅማቸውን ማሳደግ ነው። ይህም ለምሳሌ መሬት በዝቅተኛ ዋጋ ወይም በነፃ በማቅረብ፣ ብድር በአነስተኛ ወለድ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የሠራተኞቻቸውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የሥልጠናና የትምህርት ድጋፍ ማድረግ፣ የምርትን መጠን በሔክታር ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ዘር ማዳበሪያና የመሳሰሉትን በቀላሉ እንዲያገኙ ማድረግ ወዘተ፡፡

  ይህም በአገራችን አበባ እርሻ ላይ በተሰማሩ ኢንቨስተሮች በተግባር ተከናውኖ ከሞላ ጎደል ውጤታማ ሆኗል። ይህ ብቻም አይደለም፣ በተመሳሳይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ተክተው በሚሠሩ (Import substituting) የኢኮኖሚ ተቋማት ልክ በአበባ አምራቾች ላይ እንደተከናወነው በዚህ መስክ የተሰማሩ፣ በተለይም አገር በቀል ሥራ ፈጣሪ አምራችና ቢዝነሶችን (Indegnious Entrepreneurs) ለይቶ ተጨባጭ የሆነ ድጋፍና የማበረታቻ ፖሊሲና ዕርምጃ መውሰድ።

2ኛ) አንድ ገበያ መር የሆነ ኢኮኖሚ ጤነኛ ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው ሥርዓቱ ለተገበያዮች እኩል ዕድል መስጠት ሲችልና ተሳታፊዎች ግብይታቸውን በውድድርና በነፃነት ማከናወን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪን ከባንኩ የሚያገኙ አስመጪዎች የተወሰኑና የተመረጡ በሆኑበት ሁኔታ ወደ አገር የሚገቡት ሸቀጦችም በጥቂቶች ሞኖፖል እጅ በመውደቅ የሸቀጦችን የገበያ ዋጋ ከግሽበት መታደግ ከቶ አይቻልም፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ ማንም ዜጋ በአስመጪነት ንግድ ላይ መሰማራት ቢፈልግ በንግድ ሚኒስቴርና በተለያዩ ደንብና መመርያዎች የተተበተበው የፈቃድ አሰጠጥ እንዲታይና ባንኮችም ለሽያጭ የሚያቀርቡትን ምንዛሪ ማንም በአስመጪነት ንግድ ላይ ለተሰማራ ዜጋ በእኩል የሚስተናገድበትን ሥርዓትና አሠራር በመዘርጋት፣ የሸቀጥ ገበያው ከተወሰኑ እጆች ወጥቶ በብዙ ተዋናዮች ውድድር እንዲካሄድ ማድረግ ያሻል፡፡ ሸማችና ተጠቃሚዎች በዋጋ፣ በአገልግሎትና በጥራት የተሻለ እንዲያገኙ ወይም እንዲጠብቁ ማድረግ የሚቻለው ሻጮች በውድድርና በነፃነት ሲሠሩ ብቻ ነው፡፡

3ኛ) የመንግሥትን ወጪ በተለይም ደግሞ አስተዳደራዊና ወጪያቸውን መልሰው የማይሸፍኑ የቅንጦት ፈሰሶችን በመቀነስ ወደ ገበያ በሚረጨው ገንዘብ ላይ ተዓቅቦ ማድረግ።

4ኛ) ይልቁንም የመንግሥት በጀት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ በተለይም የግብርና ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ (ለጊዜው ከመሬት ሥሪት ጋር የተያያዙ ከፍ ያሉ ጉዳዮችን ትተን)፣ የማዳበሪያና ዘር አቅርቦትን በጊዜና በመጠን ለማሻሻል ቅድሚያና ትኩረት መስጠት ቢቻል፡፡ ሌሎች ከማዳበሪያ ባነስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ለምሳሌም ከአገሪቱ ለእርሻ ጥቅም ላይ ከሚውለው ወደ 14 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ ወደ 45 በመቶ በአሲድ የተጠቃና በሔክታር መስጠት ከሚገባው ከግማሽ በታች ብቻ የሆነውን አሲዳማ አፈርን በማከም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ለማስታወስ ያህል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ማስታወሻ ላይ ትንሽ ለመጨመር ለዚህ አሲዳማ አፈር ማከሚያ የሚያስፈልገው ጥሬ ዕቃ እንደ ማዳበሪያ የውጭ ምንዛሪ የማይጠይቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከማዳበሪያ ባነስ ወጪና በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ለመተግበር ከማያቋርጥ ዳተኝነትና ቸልተኝነት ወጥቶ መሥራትና በተለይም የአገር ውስጥ የምግብ ምርትና አቅርቦት ከፍላጎትና ፍጆታ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን በማድረግ የሕዝቡን በልቶ የማደር ጥያቄ መመለስና የብርን የመግዛት አቅም ለማሳደግ ጥረት ማድረግ፡፡

5ኛ) ሌሎች ከኤክስፖርት ውጭ የምንዛሪ ምንጭ የሆኑ እንደ ሐዋላ (Remittance) ዓይነቶቹን በቋሚነትና በተከታታይ ማግኘት ይቻል ዘንድ ገንዘብ አስተላላፊዎች አሁን በተወሰደው ውሳኔ ተበረታትው በተግባር መፈጸም ይችሉ ዘንድ የሐዋላ ማስተላለፍን ሥራ የሚያቀላጥፉ መተግበሪያዎችን ማዘጋጀት፣ ነገር ግን የገንዘብና የክፍያ ዝውውርን የሚገድቡ በአንድ ጊዜ ከሞባይል የሚከፈልን ከባንክ ወደ ባንክ የሚዘዋወር ገንዘብን፣ አንድ ሰው በቀን ከሒሳቡ ወጪ ማድረግ የሚችለውንና የመሳሰሉ ላይ ምክንያትና መነሻቸው የማይታወቅ፣ ንግድና ሥራን እንዲያቀላጥፉ በተፈጠሩ ዕውቀቶች ላይ የተጣለ ገደብና ክልከላን በማንሳት የገንዘብ ዝውውርና ክፍያ እንዲቀላጠፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

6ኛ) ብድርና ዕርዳታን ማፈላለግና ማግኘት አስፈላጊና የማይቀር የመሆኑን ያህል፣ የብድር ስረዛና የክፍያ ማራዘሚያ ጊዜን የማሸጋሸግ፣ እንዲሁም እንደ አጎዋ ዓይነቶቹን የውጭ ንግድን የሚያበረታቱ መንገዶችን ማስመለስና አዳዲስ ዘዴዎችን ለማግኘትም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን አጠናክሮ መቀጠል፡፡

7ኛ) እንደ ታዳጊ አገር ወደ ውጭ ሊላኩ የሚችሉ ምርቶች በአብዛኛው ያልተጠናቀቁ ጥሬ ዕቃዎች መሆናቸውን በመገንዘብ፣ እሴትን ጨምሮ መሸጥ በሚል በአስገዳጅ መመርያና ደንቦች ታስረው የሚገኙ ጥሬ ሀብቶችን ወደ ውጭ ለመላክ እንዲችሉ ደንብና መመርያዎቹን በማሻሻል፣ እሴት ጨምሮ ማምረት የራሱ ጊዜና ሒደት እንዳለው በመገንዘብ ፕሮሰስ ያልተደረገ ጥሬ ሀብትም ጭምር በቀላሉ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ዜጎች በእነዚህ ሥራዎች ላይ በቀላሉ እንዳይሠሩ እንቅፋት የሆኑ መመርያና ደንቦችን ማሻሻልና መከለስ፡፡ (ለምሳሌም እንደ ቁም ከብት፣ ቆዳና ሌጦ የጄምስቶንና ሌሎች ጥሬ ማዕድናት፣ ወዘተ…)

8ኛ) የቅንጦት ዕቃዎች ላይ የውጭ ምንዛሪ ክልከላ ማድረግ ለሌላ ጥቁር ገበያ እንዲጋለጡ ማድረግ ስለሆነ፣ እነዚህን ዕቃዎች ለመቆጣጠር የታክስ ጫና በማድረግ (Exceise Tax) በመጣል በገፍ እንዳይገቡ ለመገደብ መሞከር፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለሆኑ ስትራቴጂካዊ ሸቀጦች ማለትም እንደ መድኃኒትና ነዳጅ የመሳሰሉ ዕቃዎች የሚሰጠው ድጎማ በውጭ ምንዛሪ ድልደላና ትመና ጭምር እንዲከናወን ማድረግ፡፡

9ኛ) የመንግሥትና ፖሊሲ አውጪዎች ትኩረት በማክሮ ኢኮኖሚና ሞንተሪ ፖሊሲ ላይ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ የፊስካል ፖሊሲ (Fiscal Policy) እና ማይክሮ ኢኮኖሚው ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎችም ላይ ትኩረት በመስጠት፣ ሥራ ፈጠራንና የሥራ ቅጥርን የሚያበረታቱ፣ የአዳዲስ ንግዶች መፈጠርንና የተፈጠሩትንም ታክስና ቀረጥን ጨምሮ የተለያየ አስተዳደራዊ ወጪና ጊዜን በመቆጠብ ዕድገታቸውን የሚያሳልጥ እንዲሆኑ ማድረግ፡፡ ይህም ሲጠቃለል በተለይም የዓለም ባንክ የንግድ አሠራር ምቹነት (Ease of doing Business) እያለ ከሚጠራው አኳያ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ከ192 አገሮች ወደ 158ኛ ደረጃ ወጥታ እንድትሻሻል ለማድረግ ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ፡፡

10ኛ) ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የሸቀጦችን ልውውጥና ግብይትን የሚገድቡ ከንግድና ከትራንስፖርት ጋር የተያያዙ እንደ ኬላ፣ ሚዛን፣ መንገድ ትራንስፖርት፣ ከፀጥታና ደኅንነት ጋር በተያያዘ እንደ ፖሊስ፣ ትራፊክና ሚሊሻ ከንግድ ሚኒስቴርና ደንብ አስከባሪ፣ ወዘተ. ጋር የተያያዙ መመርያዎች፣ ደንቦችና አፈጻጸሞች፣ የቁጥጥርና ጥበቃ ተግባራትና ሚናቸውን ስተው ሠርቶ በሌዎችን ለእንግልትና የላባቸውን ዋጋ ለሙስና ከመዳረግ አልፎ፣  በሸቀጦች ዝውውርና ግብይት ላይ እያሳደሩ ያለው ተፅዕኖ ዜጎች አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ መስክ እንዳይሰማሩ፣ የተሰማሩትም ጊዜና ጉልበታቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ፣ ምርት እንዳይመረትና አገልግሎት እንዳይስፋፋ፣ ምርት ቢመረትም እንኳን ወደ ገበያው በጊዜና በተፈለገው መጠን እንዳይደርስ፣ የደረሰውም በውድድርና በሥርዓት እንዳይገበያይ በማድረግ አገሩ ላይ ለሚገኘው የዋጋ ንረትና የብር መግዛት አቅም ማነስ ሌላ ሰው ሠራሽ ችግርና ምክንያት ሆነው እንደሚገኙ ሊታወቅ ይገባል፡፡

   ስለሆነም ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ደንቦች፣ መመርያዎችና አፈጻጸሞች ሥራና ሠራተኛን የሚያስከብሩ፣ የሸቀጥ ዝውውርንና ግብይትን የሚያቀላጥፉና የሠርቶ በሌ ዜጎችን ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ መብት የሚያስጠብቁ ሆነው ሊቀረፁና ሊሻሻሉ፣ አፈጻጸማቸውም የቅርብ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡

11ኛ) ከኢኮኖሚው መነቃቃትና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ እንዲሁም የገንዘብ ክምችት በትክክለኛው የልማትና አትራፊ ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውን የአክሲዮን ገበያን በአፋጣኝ በተግባር ላይ ማዋል፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትና ተሳትፎን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን መከተል፣ መፈጸም፡፡

12ኛ) እንደሚታወቀው የአገራችን ሙስና እግርና እጅ አውጥቶ መራመድ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የዚህ ገበያ መር ምንዛሪ ግብይት የረዳው አንድ ጉዳይ ቀደም ሲል ውስጥ ለውስጥ በቅብብሎሽ ይከናወን የነበረውን የሙስና አሠራር ሊያስቀር የሚችል በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ሙስናን ለመዋጋት የመጀመሪያውና ዋነኛው መንገድ እንዲህ ዓይነት ፖሊሲዎችን መቅረፅ እንጂ፣ ሰዎችን በማሰርና (ከሕግ አኳያ መጠየቅ ሌላ ጉዳይ ሆኖ) በሌሎች ሰዎች በመተካት አይደለም፡፡ ስለሆነም መንግሥት ለዚህ መመርያ (ምንም እንኳን በውጭ ኃይላትም ጫና ሊሆን ቢችል) ያሳየውን ቁርጠኝነት በሌሎች ዘርፎችም በተመሳሳይ ከቁጥጥር ወጥቶ ወደ ቅልጥፍናና ምርት የሚያደሉ ፖሊሲዎችን፣ ደንቦችንና አፈጻጸሞችን በመከተል የሙስናንና የስንፍናን ምንጭ የሆኑ የአሠራር ዘዴዎችና በሮችን ሊዘጋ ይገባል፡፡

13ኛ) በመጨረሻም በዋነኛነትና ከሁሉም በላይ ሰላምና ደኅንነት ከምንም ነገር በላይ እንደመሆኑ የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን በማድረግ ዜጎች ጊዜና ጉልበታቸውን በማምረት ተግባር ላይ እንዲያውሉና ምርትና ሸቀጥ በፍጥነትና በነፃነት እንዲዘዋወር በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ወጣት ኃይል በምርትና ዕድገት ላይ ይሰማራ ዘንድ አመቺ ሁኔታን መፍጠር የመሳሰሉት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡

ሲጠቃለልም ይህ ውሳኔ ከላይ የዘረዘርናቸውን ዓይነት በአጭር ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ ምንጮችን በመሳብ አገሪቱ ካለችበት አዘቅጥ ለመውጣት የሚረዳ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን ይህ ውጤት ከአጭር ጊዜ መፍትሔነት አልፎ በዘላቂ መሠረት ላይ መቆም ወደ የሚያስችለን ደረጃ መሸጋገርና በአጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈጻጸማችን ላይ መሥራት እንድንችል ሰፊ የሥራ ጊዜና ዕድል እንድናገኝ በመርዳት በኩል ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ ሌሎች አስፈላጊና ወሳኝ የፖሊሲ አፈጻጸሞችንና ማዕቀፎችን ሥራ ላይ በማዋል ልንጠቀምበት እንደሚገባ ሊሰመርበት የሚገባ ነው የሚል አስተያየትና እምነት አለኝ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተቃራኒው ውጤት የከፋ መሆኑ ብዙ ንግግር የሚሻ አይመስለኝም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው negadraskassa48@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡.