እኔ የምለዉ ፕሮፌሰር በዩ ሲታወሱ

አንባቢ

ቀን: September 22, 2024

በአምባቸው ወረታ (ዶ/ር)

በዩ ብዩ የምጠራቸው የዛሬ ባለታሪክ በደንብ ቀርቤ የማውቃቸው  ከ2007 ጀምሮ ነው። እሳቸው  የዶክትሬት ዲግሪ (Ph.D) አማካሪዬና መምህሬ ሆነው ብቅ አሉ። በዩ ተማሪን ማቅረብ፣ ማዳመጥና ጊዜ መስጠት የሚችሉ ሰው ነበሩ። እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች  ከፍተኛ ዝግጅት አድርጌ አንብቤ ለጨዋታ የማልቀርባቸው እኔ ብቻ  ነበርኩኝ ብዬ አስባለሁ። ደካማ ጎኔን ያውቁት ኗሯል፣ እንዲሁም የሆነ የተስፋ ጭላንጭልም ይታያቸው ነበርና አብልጠው ያቀርቡኝ ነበር፡፡ እንዲያውም  ስጠፋ በአፋላጊም፣ በስልካቸው ጭምር የት ጠፋ  እያሉ ይፈልጉኝና ወደ ትምህርት ገበታዬ ይመሉስኝ ነበር።

በዩ የወሎን አካባቢ አብልጠው የሚወዱበት ነገር አላቸው። ወሎን እንደሚያፈቅሩና ኢትዮጵያ ወለል ብላ ወሎ ሥር  እንደሚያዩት ደፈር ብለው ነግረውኛል። አንዳንድ የወሎ  አካባቢ መጠሪያዎች አሁን ያለውን ፖለቲካ ተንተርሰው ፈገግ እንደሚያሰኛቸው በቀላሉ  በቀልድ መልክ ተረብ ያረጉኛል።  እኔ በእሳቸው አማካሪነት የዶክትሬት ዲግሪ ከጨረሱ የመጨረሻ ዘመናቸው ወጣት ተማሪ ነበርኩ።  አንዳንዴም ወደ ትውልድ ቦታዬ ወሎ  ቤተሰብ ለመጠየቅ ስሄድ ደውለው ‹አንተ ልጅ እንዴት ነህ፣ ከሰሞኑ ግርግር ተርፈሃል› ይሉኛል። ደህና መሆኔን ስነግራቸው ‹አሳሰብከኝ እኮ ምን ላድርግ?!› ይሉኛል በማዘን።
እሳቸው ተማሪን ከአባት በላይ ነው ጥበቃና ከለላ የሚያደርጉለት። ጠበቃና ተቆርቋሪ መሆን የእሳቸው መገለጫ ነው። 

በአንድ ወቅት የምማርበት የትምህርት ክፍል የዶክትሬት ዲግሪ ምርምሩን ሥራ መሄድ ባለበት ደረጃ አልተንቀሳቀሰም በሚል የክንውን ሪፖርት እንዳቀርብ በትንሽ ሴራ የተሸረበች ዝግጅት ተደረገ። 

አንዳንድ እኔ እንድባረር  የሚፈልጉ ሰዎችም ተሰባሰቡ። ይህንን ነገር ያላማራቸው በዩ ከተፍ አሉ። እኔም ትንሽ ተዘጋጅቼ ነበር ትንሽ የሠራኋቸውን ሥራዎች ለማቅረብ ተጣጣርኩ። ዘወር ብለውም ወደ ተሰበሰበው ሰው ተመለከቱ ሁኔታው አላማራቸውም። መናገር ቀጠሉ። ‹ይህንን ልጅ   አትላንታ  የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ድርጅት አንድ ተባባሪ ሰው አለኝ  እዚያ እልከዋለሁ፣ ሥራውን በሚገባ  እዚያው ጨርሶ ይመጣል። ስለዚህ የእሱ ነገር አያሳስብም› ብለው ወሽመጣቸውን ቆረጧቸው። ከዚያ በኋላ በክፍሉ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በደቂቃዎች ውስጥ አልነበሩም። ስብሰባውን የሚያስተባብረው ሰውዬ እኔና በዩ ነበርን በአዳራሹ። ቀና ብለው፣ ‹አንተ ሰው ከሳሾችህ ወዴት አሉ?›  አሉኝ በፈገግታ።  በዩ  ጥሩ አለባበስና በራስ መተማመን ያለው ሰው ይወዳሉ። ዘመናዊ ሰው ናቸው።  ቢሯቸው ስሄድ በጥሩ አለባበስና አነጋገር ዓይን ለዓይን እየተያዩ ማውራት ይወዳሉ። አባታዊ በሚመስል አስተያየት፣ ‹እንዴት ነው የለበስከው? አንታርቲክ  የምትኖር መሰልክ እኮ፣ ቀና ብለህ አናግረኝ እንጂ፣ ወሬህን ሳይንስ ጨምርበት እንጂ…› እያሉ በፈገግታ ጎሸም ያደርጉኛል።  

በዩ ተማሪ የነገሯቸውን ነገር ፈፅሞ አይረሱም። ‹የዛሬ ሦስት ዓመት እንዲህ አደርጋለሁ ወይም አድርጌያለሁ ብለኸኝ አልነበር እንዴ?› ሲሉ የማስታወስ ድንቅ ብቃታቸውና የእኔ በዕድሜ ከእሳቸው የማንሰው  የማስታወስ አለመቻል  ይገርመኛል። ያወራኋቸውን ቀልድና ቁምነገር አይረሱም። እሳቸውን ፈፅሞ መሸወድ አይቻልም። ዓይን አይተው ይረዳሉ። 

ሌላው ፖለቲካ ብዙም የማውራት ፍላጎት የላቸውም። አንዳንድ ወጣቶች ከሌላ ቦታ ሾለክ ብለው ቢሮአቸው ስለፖለቲካ ጉዳይ ሊያወሩ የሄዱ እንደሆ፣  ‹ልጆች ይህ የሥራ ቦታ እንጂ ፖለቲካ የሚወራበት አይደለም› ብለው ቆጣ ብለው ይመልሳሉ፡፡ እኛ ተማሪዎቻቸው ደግሞ በሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና መምህራን ተበደልን፣ ነገሮች እክል ገጠማቸው ስንላቸው፣ ‹ታገሉ እንጂ ወይም ታገል ነው› የሚሉት፡፡ ቀጠል አድርገውም፣  ‹ከእግዚአብሔር በታች ያለውን  ነገር ሁሉ  ደረጃ በደረጃ ታገል›  እያሉ ነበር  ምክር ጣል የሚያደርጉት።  ሥራ ይበዛብኛልና ክፍል ይቅር ቀጠሮ ይሰረዝ አይሉም። እሳቸው ይመጣሉ እኛ እንቀራለን። ‹እኔ እናንተን ብዬ እየመጣሁ  እናንተ ትቀራላችሁ› ብለው በትህትና የሚመልሱትም ነገር አላቸው።

በዩ ደመወዜ ይበቃኛል በሚለው አገላለጽ ይታወቃሉ። ለምሳሌ ውኃ ገዝቼ ስሰጣቸው የገዛሁበትን ሳንቲም ቆጥረው ይሱጡኛል። ‹ሙስና ልታደርግብኝ ነው አልፈለግም፣ ገንዘብህን ውሰድ› ብለው በፈገግታ ያጅቡኛል። አንድ የእኛ ጓደኛ የእሳቸውን ስም ተጠቅሞ የምርምር ድጋፍ ገንዘብ አገኘና አብዛኛውን ነገር በምንም በምንም አድርጎ ገንዘቡን ተጠቅሟል። በእሳቸው ስም ገንዘብ ተቀብዬ ምን ይሉኝ በማለት የተወሰኑ ሺሕ ብሮች ቆጠር አድርጎ ቢሯቸው ገብቶ ሊሰጣቸው ሞከረ፡፡ እሳቸው ትንሽ ገርመም አድርገውት፣  ‹ከፊቴ ውሰድልኝ  እኔ ገንዘብ አልፈልግም፣ ደመወዜ ይበቃኛል የሚገባኝም  ከሆነ ከአንተ ሳይሆን  ከመንግሥት እጅ ሕጋዊ ገንዘብ ፈርሜ ነው የምወስደው› ብለው መለሱለት።

በክፍለ ጊዚያቸው ረቀቅ ያለ ነገር ያስተምራሉ፣ ትንሽ ፈጠን ፈጠን እያሉ በሚከብድ የቋንቋ አጠቃቀም። አዳዲስ ነገሮችን አንብበው ዘመኑ የደረሰበትን የምርምር አቅምና  ስምምነት ቀምመው ያስተምራሉ።  ታዲያ እንደ እኔ ላለው ተማሪ አንዳንዴ ግርታን ይፈጥራል።   ሲጨርሱም ‹ጎበዝ ኮንፊውዝድ ሆናችሁ አይደል…›  ብለው ይጠይቃሉ።  በስምምነት አንገቴን ቀድሜ  የማወዛውዘው እኔ ነኝ።  እሳቸው ደግሞ ፣  ‹የትምህርቱም ዓላማ  ይኸው ነበር፣ ግቡን መቷል ማለት ነው› ብለው በፈገግታ ይሰናበቱናል።  ለማንበብ ወይም  ይበልጥ  ለማሰላሰል ይራዳችኋል ለማለት እንደሆነ እንረዳዋለን። አንዳንዴ በክፍል ውስጥ   የምርምር ኅትመቶችን እንድንተች ይጠይቁናል ። ‹በሉ ጀምሩ›  ይሉናል እንድናቀርብ እያጋበዙን፡፡ ‹ጎበዝ ከሞትና ከ”Presentation” የሚቀር ማንም የለም›  ብለው ያደፋፍሩናል። 
ከዚያ በተጨማሪ እሳቸው ለተማሪ ሙቀት ናቸው። እሳቸው ዘንድ ጥናታዊ ምርምሩን የሚሠራ ተማሪ ተሰናክዬ እቀራለሁ የሚል እምነት የለውም። የከፋ ነገር ከመጣ ተማሪዎቻቸውን አሳልፈው አይሰጡም፣ ይከላከላሉ፣ ይጠነቀቃሉ። የተማሪ ደካማ ጎን ይገባቸዋል። ከፍቶን ተስፋ ቆርጠን ከራቅን በሌላ ሰው ሳይቀር መልዕክት ልከው፣ ‹ና እንጂ ታገል የምን መሸነፍ ነው› ብለው መልሰው ያስገቡናል ወደ ትምህርት ገበታችን፡፡  ኢሜይላቸውንም ስልካቸውንም ጆሮ ዳባ ልበስ ብዬ ቢሮአቸው ለስድስት ወራት ጠፍቼ ሄጄ  እኔ ስሳቀቅ፣ ‹አይዞህ እኔ በሕይወት መኖርህን ነው የምፈልገው፣ እንዲሁ ጠፍቶ ከመቅረት ዘግይቶ መገናኘት ይሻላል› ብለው በፈገግታ ይቀበሉኛል።

ጽሑፍ ሲገመግሙ  ማሽን ራሱ እንደ እሳቸው በዚህ ዘመን እንከን ማውጣት አይችልም። እንከን አይወዱም፣ እንከን አይፈቅዱም። ያረጀ ያፈጀ ሐሳብ አይወዱም። ድግግሞሽና የይስሙሉላ ሐሳብ አይወዱም። አዲስ ነገር ናፋቂ ናቸው። አዳዲስ የምርምር ኅትመቶችን  ከየትም አሳደው ያገኟቸዋል። ‹ይህችን አይተሃት ነበር ይህንን ከመጻፍህ በፊት…› ይላሉ። ሐሳብ ቅልብጭ ሲል ይወዳሉ። ሀተታ ሲበዛ፣ ‹ይህንን ሁሉ ማጣቀሻ የደረደርከው አንብበኸው ነው ወይስ እንዲያው ኮርጀኸው ነው› ብለው ሸንቆጥ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያማ  እንደገና ይጻፋል፣ ጥረት ይደረጋል፣ ከዚያ አዲስ ልምድና በራስ መተማመን ይዳብራል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ያበቁናል።

በዩ ሥራ በዝቶብኛል የሚል ቃል አይወዱም፣ ደግሞም አይጠቀሙም።  የመጨረሻ ሥራዬን ለማቅረብ በምውተረተርበት ወቅት እሳቸው የመንግሥት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር ቢሆኑም፣ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው እያንዳንዱን ገጽ በትነው ይሠሩት ነበር። ጽሑፉን ገልብጠው ጠንከር ያለ እርማት ያደርጉ ነበር።  ጥናታዊ ጽሑፌን ለማቅረብ በምሰናዳበት ወቅትም   ማታ ማታ እየደወሉ፣ ‹እስኪ ዛሬ የተዘጋጀኸውን  በል ንገረኝ› እያሉ ረዥም ሰዓት ያዳምጡኝ ነበር። በዚህ ድርብ ኃላፊነታቸውም የትምህርት ክፍላችንም ተመላልሰው፣ ‹የዚህን ልጅ ጉዳይ ጨርሱለት አታንጓቱበት› እያሉ ሽንጣቸውን ገትረውም ይከራከሩልኝ ነበር።  ጭንቀታቸው በዚያው ተስፋ ቆርጨ እንዳልጠፋባቸው ነበር።  ያም ሆነ ይህ  የመጨረሻው ቀን ደርሶ መመረቂያዬን  አቀረብኩኝ፡፡ እሳቸውም እኔ የረሳሁትን ታሪኬን ለሰባት ዓመታት የትምህርትና የሕይወት ቆይታዬን ስንክሳር በአጭሩ በመግለጽ  ብዙ ለፍተውብኝ እያለ፣ ‹ይኼ ልጄ ብዙ የሚያስቸግር አይደለም፣ ራሱን በራሱ ነው እዚህ ያደረሰው› ብለው   ቀለል አደረጉት፣ አስመረቁኝ።

ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ድምቀት ነበሩ። አንዳንድ ከውጭ ተጋብዘውም ጠይቀውም የሚመጡ ሳይንቲስቶች የምርምር ሥራቸውን በሚያቀርቡበት አዳራሽ በዩ የመጀመሪያው ወንበር ላይ ነው የሚቀመጡት።  የማይጥም ነገር ከገጠማቸው አቋርጠው አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ። ሰፋ ያለ ትንታኔ ያቀርባሉ። የምርምር ሥራቸውን ሊያቀርቡ የመጡ የውጭ አገር ሰዎች በፍርኃትና በአክብሮት ፊታቸው ቲማቲም ሲመስል ሳይ ትንሽ ኩራት ቢጤ ይሰማኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።  እሳቸው የማያውቋቸው  የተላላፊ በሽታዎች ሳይንስ የክትባት ምርምሮችና ግኝቶች  የሉም። እሳቸው  በበርካታ  የወባ ክትባትን ወደ ትግበራ ለማስገባት በሚደረግ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ተሳትፏቸው የላቀ እንደነበር ተረድተናል።

ለዚያም ነው የውጭ እንግዶች በየነ በተገኙበት  ስብሰባ  ከፍርኃትና ከአክብሮታዊ ጥንቃቄ ጋር የምርምር ሥራዎቻቸውን የሚያጋሩት። በአጠቃላይ ግን በሰባት ዓመታት ቆይታ ውሸትን እንደማያውቋት  ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደሚችሉ፣ ተማሪዎቻቸውን እንደ ልጅ እንደሚያቀርቡና ችግሮቻችንን እንደሚፈቱ፣ የፖለቲካ ንግግር በካምፓስ ውስጥ እንደማያወሩ፣ ቀልድ አዋቂነታቸው፣ ሁሉንም በእኩል ማየታቸው፣ ቀጠሮ አክባሪነታቸው፣ የሰው አለመፈለጋቸውና  በደመወዛቸው ብቻ የኖሩ መሆናቸው፣ እኔና እኔን የመሳሰሉ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎችን ማፍራታቸው፣ አብዛኛው የእሳቸው አሻራ በእያንዳዳችን ሙያዊ ማንነት ላይ የሚንፀባረቅ መሆኑ ጉልህ ነው። 

ፕሮፌሰር በየነ  ከዚህ ላቅ ያለ ሰብዕና አገር ወዳድነት፣ ለሙያቸው ካላቸው ክብርና  ጠለቅ ያለ አስደማሚ ዕውቀተቸው አንፃር በቀላሉ የሚተኩ ሰው አይደሉም።  የዚህ ታሪክ ጸሐፊ እኔ ከአገሬ ውጪ በሙያ የምሠራ ሲሆን፣ በርካታ የሳይንስ ሰዎችን ለማግኘት የቻልኩባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከእኚህ አንጋፋ ፕሮፌሰር ጋር የሚስተካከል ሰው  አላገኘሁም።

አደራቸውን ተወጥተዋል፣ ቃላቸውን አላጠፉም፣ ከሰብዕናቸው አልወረዱም፣ በከንቱ ጊዚያቸውን አላበከኑምና ወገናቸውን በሚገባ አገልግለዋል፡፡ ሐሜትና  ተንኮል የሚጠየፉ ነበሩ፣ ሃይማኖታቸውን በተግባር የኖሩ፣ መድልኦና ጥላቻ የሌለባቸው አባት ምሁር ነበሩ፡፡ ተወዳጁን  በየነ ጴጥሮስ ከደጋጎቹ ቅዱሳን ጋር ፈጣሪ አምላክ እንዲያቆማቸውና መልካም ሥራዎቻቸው ለዘለዓለም እንዲታወሱ እመኛለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐዎቹ አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው ambachew.hailu@nih.gov ማግኘት ይቻላል፡፡