የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማ እና ላፕቶፕ
የምስሉ መግለጫ,ሞሳድ ጥቃቶችን እና አሻጥሮችን መሬት ላይ እና በይነ መረብ ላይ በመፈጸም ይታወቃል

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው ሳምንት በሊባኖስ ከተፈጸሙት በሺዎች የሚቆጠሩ ከትንንሽ ነገር ግን ከአደገኛ ፍንዳታዎች ጀርባ በርካቶች የእስራኤል እጅ አለበት ብለው ያምናሉ።

ምክንያታቸው ደግሞ እንዲህ ያለውን የረቀቀ እና የተቀነባበረ ጥቃት በዓለም ላይ ከአገሪቱ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ውጪ ማንም ይፈጽመዋል ብለው ስለማያስቡ ነው።

ፍንዳታዎቹ በዋናነት ኢላማ ያደረጉት በኢራን የሚደገፈው እና እስራኤል መሪዎቹን እንዲሁም አባላቱን እያሳደደች የምትገድልበት ሄዝቦላህን መሆኑ እንዲሁም በመገናኛ መሳሪያዎች ላይ የተጠመዱ ፍንዳታዎች መሆናቸው ድርጊቱ የእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ መሆኑን አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ።

በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጠላተ ብዙ የሆነችው እስራኤል በዙሪያዋ ያሉ አገራት በይፋ ሊያጠቋት ባይነሱ እንኳን፣ በአካባቢዋ የሚንቀሳቀሱት ፈርጣማ ታጣቂ ቡድኖች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ዒላማ ያደርጓታል። አገራቱ ላይም ቢሆን እምነት ስለሌላት ጓዳቸው ድረስ በመግባት መረጃ ከመሰብሰብ አልፋ ጥቃት እና ግድያዎችን ትፈጽማለች።

ይህን ሁሉ ኃላፊነት የተሸከመው ደግሞ ኃያሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ነው። የስለላ ተቋሙ ከእስራኤል ወታደራዊ ተቋማት ባልተናነሰ የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ጉልህ ሚና አለው። ሞሳድ መቼ ተመሠረተ? አቅሙስ ምን ያህል ነው? በመላው ዓለም በተለይም በመካከለኛው ለምን የሚፈራ ተቋም ሆነ?

ከእስራኤል ጋር የተመሠረተው ሞሳድ

በመላው ዓለም ‘ሞሳድ’ በሚል ስም የሚታወቀው የስለላ ድርጅት የተቋቋመው እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እንደ አገር ከተመሠረተች ከወራት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1949 ነው።

ፍልስጤም በብሪታኒያ የሞግዚት አስተዳደር ስር በነበረች ጊዜ የአይሁዳውያን ወታደራዊ ኃይል የሆነው ‘ሃጋናህ’ የመረጃ ክንፍን መሠረት አድርጎ በወቅቱ የእስራኤል መሪ በዴቪድ ቤን ጎሪዮን አማካኝነት የተመሠረተው ሞሳድ፣ ይፋዊ መጠሪያው ‘የስለላ እና ልዩ ተልዕኮዎች ተቋም’ የሚል ነው።

የስለላ ተቋሙ ዋነኛ ዓላማ “መረጃ መሰብሰብ፣ ስጋቶችን ማክሸፍ እና የእስራኤልን እንዲሁም የአይሁድ ሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ” መሆኑን ድረ ገጹ ያመለክታል።

ይህንንም ለማሳካት ሞሳድ “በውጭ አገራት የሚካሄዱ ምሥጢራዊ ተግባራትን በማይታወቅ ሁኔታ፣ በድፈረት እና በጥበብ መከወን የሚችሉ” ምርጥ የሚባሉ አባላትን እንዳሉት ይጠቅሳል።

ምንም እንኳን ሞሳድ በዓለም ዙሪያ የሚታወቅ የእስራኤል የስለላ ክንድ ቢሆንም፤ አገሪቱ ያላት ብቸኛው የደኅንነት ተቋም ግን አይደለም። ሞሳድ ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎችን ሲፈጽም፣ ‘ሺም ቤት’ የሚባለው መሥሪያ ቤት ደግሞ በእስራኤል ውስጥ የደኅነነት ሥራን ያከናውኛል። በተጨማሪም ‘አማን’ የሚባለው የስለላ ተቋም ደግሞ ወታደራዊ የደኅንነት ቡድን ነው።

የሞሳድ አባላት እና ሁሉም እንቅስቃሴው ምሥጢራዊ ሲሆኑ እስከ አውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ድረስም ተቋሙን የሚመሩ ሰዎች ማንነት በይፋ አይታወቅም ነበር። በኋላ ላይ ግን የተቋሙ ዳይሬክተር ማንነት በመገናኛ ብዙኃን መገለጽ በመጀመሩ ዓለም ያውቃቸዋል።

በእስራኤል ካሉ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የደኅንነት ተቋመት በተለየ የሞሳድ ዋና ኃላፊ ያለምን መንግሥታዊ እና የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ይሁንታ ሳያስፈልገው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ይሾማል። ከዚህ በተቃራኒ የእስራኤል የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም እንዲሁም የሺም ቤት ኃላፊዎች ግን በአገሪቱ ምክር ቤት በኩል ነው ሹመታቸው የሚጸድቀው።

ዴቪድ ቤን ጎሪዮን
የምስሉ መግለጫ,ሞሳድ እስራኤልን ከውጭ ስጋት እንዲከላከል ያቋቋሙት የመጀመሪያው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤን ጎሪዮን

ሞሳድ እንዴት ታዋቂ ሊሆን ቻለ?

ከእስራኤል መመሥረታ በፊት እና በኋላ ለአይሁዳውያን ደኅንነት ስጋት የነበሩ እንዲሁም የሆኑ አካላትን ዒላማ ያደረገው ሞሳድ በተከታታይ ያካሄዳቸው ውስብስብ ምሥጢራዊ ኦፕሬሽኖች ታዋቂነትን እንዲያገኝ ከማድረጉ በላይ የዓለም መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

ለበርካታ አይሁዳውያን ሞት ተጠያቂ ነው የተባለው የናዚው የጦር መኮንን አዶልፍ ኤክማን ለዓመታት ከተደበቀበት አርጀንቲና በስውር በማስወጣት ለፍርድ እንደቀርብ የተደረገው በሞሳድ ወኪሎች ምሥጢራዊ ዘመቻ ነበር።

ጀርመን ሚዩኒክ ውስጥ በተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ የእስራኤል አትሌቶችን አግተው በመግደል እጃቸው አለበት የተባሉ ቢያንስ ሰባት የፍልስጤም ቡድን አባላትን በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ለዓመታት ካሉበት አድኖ አንድ በአንድ አጥፍቷቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከምሥረታው ጀምሮ አስካሁን ድረስ ዋነኛ የእስራኤል ጠላቶች ናቸው ከሚባሉ የፍልስጤም እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ታጣቂ ቡድኖች መሪዎች ግድያ ጋር በተያያዘ የሞሳድ ስም አብሮ ይነሳል።

እነዚህ ኦፕሬሽኖች ውስብስብ የሚሆኑት የሚፈጸሙት ከእስራኤል ግዛት ውጪ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ውስጥ መሆናቸው ነው። እንዲሁም የእስራኤልም መንግሥትም ሆነ የስለላ ተቋሙ ስለተወሰዱት እርምጃዎች ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ እምብዛም ሲሰጡ አይታዩም።

“የእስራኤል የውጭ ስለላ ተቋም ሞሳድ የአሜሪካው ሲአይኤ እና የዩናይትድ ኪንግደሙ ኤምአይ6 አቻ ቢሆንም፤ በአገሪቱ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን ግን ከሁለቱም ሰፋ ያለ ነው” ይላል የቢቢሲ የደኅንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር።

በዚህም ከሲአይኤ እና ከኤምአይ6 በተለየ ሞሳድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያካሂደው ስለላ እና ምሥጢራዊ ዘመቻ ባሻገር ቁልፍ ዲፕሎማሲያዊ ሚናን ለአገሩ ይጫወታል። በተለይም ከሙስሊም አገራት ጋር እስራኤል ያላት ግንኙነት እንዲሻሻል ባለፉት ዓመታት በተደረገው ጥረት ውስጥ የተቋሙ ሚና ተጠቃሽ ነው።

እስራኤላዊው ፖለቲከኛ ዳኒ ያቶም እንደሚሉት “ከሞሮኮ እና ከሌሎች የሰሜን አፍሪካ አገራት ጋር እስራኤል ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል የተደረገው ጥረት የተመራው በሞሳድ ነበረ።”

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ
የምስሉ መግለጫ,ገደብ የሌለበት የሞሳድ ኃላፊ የሚሾመው በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው

ስለላ፣ አሻጥር እና ግድያ

የእስራኤል መንግሥት በዓመት ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት የሚመድብለት እና በአሁኑ ጊዜ 7 ሺህ የሚደርሱ ሠራተኞች ያሉት ሞሳድ፤ በሚያከናውነው የደኅንነት እና የስለላ ሥራ ብቃት በዓለማችን ከአሜሪካው ሲአይኤ ቀጥሎ ሁለተኛው የስለላ ተቋም እንደሆነ ይነገርለታል።

ሥራውን በ80 አባላት የጀመረው ሞሳድ ከባድ የሚባሉ ተልዕኮዎችን በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ በመፈጸም አድናቆትን በማግኘት መነጋገሪያ ከመሆን ባሻገር በርካታ የቡድኑ ተልዕኮዎች እና ታሪኮች ወደ መጽሐፍት እና ፊልም ተቀይረዋል። በተጨማሪም ብዙ የስለላ ፊልሞች እና መጽሐፍት ሞሳድን መሠረት አድርገው ተደርሰዋል።

ሞሳድ ዒላማ የሚያደርገው ግለሰቦች እና ቡድኖችን ብቻ ሳይሆን አገራትንም ጭምር ነው። በተለይ ደግሞ እስራኤልን በከበቧት አረብ አገራት ውስጥ የሚካሄዱ አስጊ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ እርምጃ በመውሰድም ስሙ ይነሳል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ ተቋሙ የእስራኤል “ጠላት” ናቸው በሚባሉ ጎረቤት አገራት ውስጥ የተለያዩ የስለላ ተግባራትን በመፈጸም ያልታሰቡ ዘመቻዎችን አካሂዷል።

በአገራቱ ውስጥ እስራኤል “ሽብርተኛ” የምትላቸው ደርጅቶች መሪዎች ላይ ግድያ መፈጸም፣ ሳይንሳዊ እና ወታደራዊ ተቋማቶቻቸው እንዲሰናከሉ አሻጥር መሥራት፣ መንግሥታቱን ከሚቃወሙ የጎሳ ወይም የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ማሴርን ጨምሮ ሞሳድ የእስራኤልን ጥቅም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን ፈጽሟል።

“በምንችልበት ስፍራ ሁሉ ወዳጆችን ለማፍራት ጥረት እናደርግ ነበር” የሚለው የቀድሞው የሞሳድ አባል ኤሊያህ ሳፍሪያ፣ እሱም የኢራቁን ሳዳም ሁሴንን በመቃወም ይዋጉ የነበሩትን የኩርድ ኃይሎችን ለመደገፍ ይሠራ እንደነበር ከዓመታት በፊት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

ግድያን እና አሻጥርን በሚመለከት የቀድሞው የሞሳድ ዳይሬክተር ዮሲ ኮኽን ከሦስት ዓመት በፊት እንዳረጋገጡት፣ ተቋሙ በአውሮፓውያኑ 2018 የኢራን የኑክሌር ፕሮግራምን በተመለከተ በሺዎች ከሚቆጠሩ የሰነዶች ዝርፍያ ጀርባ ሞሳድ እንደነበረ አምነዋል።

በተጨማሪም ናታንዝ በተሰኘው የኢራን ኑክሌር ማዕከል ላይ በተፈጸመው የበይነ መረብ ጥቃት እንዲሁም ሞህሲን ፋክሪዛዴህ በተባሉት ዋነኛው የአገሪቱ የኑክሌር ሳይንቲስት ላይ በ2020 (እአአ) በተፈጸመው ግድያ ውስጥ የሞሳድ ወኪሎች መሳተፋቸውን ኃላፊው ፍንጭ ሰጥተዋል።

አሁን በቅርቡ በዋና ከተማዋ ቴህራን ባልታሰበ ሁኔታ ከተገደሉት የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ግድያ ጋር በተያያዘ የኢራን መንግሥት ሞሳድን በተጠያቂነት ቢከስም እስራኤል ግን ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

ይህ እና ሌሎችም ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ጥቃቶችን መሠረት በማድረግ ነው አሁን ሊባኖስ ውስጥ በሺህ በሚቆጠሩ የግንኙነት ማሳሪያዎች ላይ በረቀቀ መንገድ ከተጠመዱ ፈንጂዎች ፍንዳታ ጋር በተያያዘ በርካቶች የእስራኤል የስለላ ድርጅት ስምን እያነሱ ያሉት።

ቤይሩት ከደረሰው ፍንዳታ በኋላ በተጨናነቀ መንገድ ላይ የሚታይ አምቡላንስ
የምስሉ መግለጫ,የሊባኖስ መንግሥት እና ሄዝቦላህ በግንኙነት መሳሪያዎች ላይ የተፈጸሙት ፍንዳታዎች ሞሳድ ያቀናበራቸው ናቸው ያሉ ሲሆን፣ አንዳንድ ምዕራባውያንም ይህንን ግምት ይቀበሉታል

ገደብ የሌለበት ሞሳድ

የእስራኤልን ደኅንነት እና ጥቅምን መሠረት አድርጎ የተሰጠውን ገደብ የለሽ ሥልጣን በመጠቀም ሞሳድ በተለያዩ አገራት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በአገሪቱ መንግሥት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ውግዘት እንዲሁም ከአገራት ጋር ያለው የግንኙት መበላሸትን አስከትሏል።

ለምሳሌም ከአርጀንቲና ባለሥልጣናት ዕውቅና ውጪ በድብቅ ታፍኖ ከአገሪቱ እንዲወጣ የተደረገው የናዚው የጦር መኮንን አዶልፍ ኤክማን ጉዳይ በእስራኤል እና በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር መካከል ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብን አስከትሎ ነበር።

በሚዩኒክ ኦሊምፒክ የእስራኤል አትሌቶችን ግድያ ለመበቀል ሞሳድ ባካሄደው ዘመቻ መካከል አንድ የሆቴል ሠራተኛ በስህተት የፍልስጤም ቡድን አባል ነው በሚል ኖርዌይ ውስጥ በመገደሉ እስራኤል ከምዕራባውያን ጋር ባለት ግንኙነት ላይ ችግርን አስከትሏል።

ሌሎችም እስራኤል በይፋ የደኅንነት ተቋሟ እርምጃዎች ናቸው ባላለቻቸው የስለላ ዘመቻዎች እና እርምጃዎች ምክንያት አገራት ቁጣቸውን እንዲሁም ተቃውሟቸውን ቢገልጹም ሞሳድ የተሰጠውን ዓላማ ከመፈጸም ወደኋላ አላለም።

በተጨማሪም እርምጃዎቹ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እና ውግዘትን ቢያስከትሉበትም ውጤቱ የእስራኤልን እና የአይሁዳውያንን ጥቅም እና ደኅንነትን የሚያስጠበቅ በመሆኑ እምብዛምት ትኩረት አልተሰጠው። “ውጤቱ መንገዱን ይወስነዋል” እንደሚባለው በምንም መልኩ ቢሆን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት የሞሳድ ዋነኛ ግብ ነው።

ሞሳድን ምንም የሚገድበው ነገር እንደሌለ የሚናገረው እስራኤላዊው ዮሲ ሜልማን “እስከ ሰማይ ጥግ ድረስ መጓዝ ይችላል” ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

ጨምሮም ሞሳድ “ወዳጅ አገራትን ቢተነኩስ፣ በግዛታቸው ውስጥ ወንጀሎችን ቢፈጽም ወይም ዓለም አቀፍ ወይም አገራዊ ሕጎችን ቢጥስ የእስራኤልን ደኅንነት ለማስጠበቅ መደረግ ያለበት እንደሆነ ይታመናል” ይላል።

በሞሳድ ዙሪያ የሚያጠነጥነውን “ስፓይስ ኦፍ ዘ ሆሎኮስት” የተባለው መጽሐፍ ደራሲ ዮሲ እንደሚለው ምንም ያህል የስለላ ተቋሙ አገራትን እና መንግሥታትን የሚያስቆጣ ድርጊት በግዛታቸው ውስጥ ቢፈጽምም አገራቱ ጉዳዩን አጥብቀው አይገፉበትም።

“በናዚ በተፈጸመው የአይሁዶች የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት የተፈጠረው ሐዘኔታ እና እስራኤል ትንሽ አገር በመሆኗ የተነሳ የሞሳድ ገደብ የለሽ እርምጃዎች እምብዛም ተጠያቂነት ሳያስከትሉ በዚያው ይቀራሉ” ይላል።

ነገር ግን ከተወሰኑት የሞሳድ ዘመቻዎች ውጪ የሊባኖሱን ፍንዳታዎች፣ በኢራን የሐማስ መሪ ግድያን ጨምሮ የሚጠቀሱትን እስካለንበት ዘመን ድረስ በእስራኤል የስለላ ተቋም አማካይነት የተፈጸሙ ጉልህ ኦፕሬሽኖችን በተመለከተ የእስራኤል ባለሥልጣናት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ለመስጠት አይፈቅዱም።

በዚህም የደኅንነት ባለሙያዎች እንዲሁም ጉዳቱ የደረሰባቸው ወገኖች እስራኤልን እና ሞሳድን ተጠያቂ ከማድረጋቸው ባሻገር ክስተቶቹ እንዲሁ ድፍን እንደሆኑ ተድበስብሰው ያልፋሉ።