የማንቸስተር ሲቲ እና የአርሰናል ተጫዋቾች

ከ 3 ሰአት በፊት

ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው አርሰናልን አስተናግዶ 2 ለ 2 በተጠናቀቀው ጨዋታ አንድ ቡድን ለመጫወት ወደ ሜዳ ገብቷል ሲል በርናንዶ ሲልቫ መድፈኞቹን ወቅሷል። የለንደኑ ክለብ “አስቀያሚ አጨዋወትን” መርጧል ሲሉም የሲቲ ተጫዋቾች ወቅሰዋል።

የአርሰናል አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ በበኩሉ ሁለተኛውን አጋማሽ በ10 ተጫዋች ተጫውተው ለድል አፋፍ መድረሳቸውን ‘ተአምር’ ብሎታል።

አርሰናል ሦስት ነጥቡን በእጁ አስገብቶታል ተብሎ ሲጠበቅ ነው ጆን ስቶንስ በ98ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ጎል ያስቆጠረው።

ሊያንድሮ ትሮሳርድ በመጀመሪያ አጋማሽ ተጨማሪ ሰዓት ላይ በአወዛጋቢ ሁኔታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ይህን ተከትሎም መድፈኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር 12.5 በመቶ ብቻ ነበር።

ሲቲ በሁለተኛው አጋማሽ ብቻ 28 ሙከራዎችን አድርጓል። ቡድኑ በ2012 በአጉዌሮ ጎል ሻምፒዮን በሆነበት ዕለት ኪውፒአር ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ባደረገው ሙከራ ብቻ የተበለጠበት የጎል ማግባት ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል።

“አንድ ቡድን ብቻ ነው ለመጫወት ወደ ሜዳ የገባው። ሌላኛው ደግሞ ለተሳትፎ ብቻ ወደ ሜዳ ከመግባቱም በላይ በዳኛ ተደግፏል” ሲል በርናንዶ ሲልቫ ለብራዚሉ ቲኤንቲ ስፖርት ተናግሯል።

“ሁሌም ወደ ሜዳ የምንገባው ለማሸነፍ ብቻ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

ብሬንትፎርድ በ2022 ካሳካው በኋላ በኢትሃድ ማንቸስትር ሲቲን ያሸነፈ የመጀመሪያው ቡድን ለመሆን አርሰናል ሰከንዶች ብቻ ቀርተውት ነበር። ሦስቱን ነጥብ ቢያሳካ ደግሞ በሊጉም አናት መቀመጥ ያስችለው ነበር።

“ኢትሃድ ላይ ለ56 ደቂቃ በ10 ተጫዋች መጫወታችን ተአምር ነበር። ያሳካነው ነገር የማይታመን ነው” ሲል ሚኬል አርቴታ ተናግሯል።

ትሮሳርድ ቢኖር ኖሮ ጨዋታውን ማሸነፍ ትችሉ ነበር ወይ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄም “አላውቅም። እንሞክር ነበር። ከዚህ ቡድን ጋር ለ56 ደቂቃ በ10 ተጫዋች 100 ጊዜ ብትጫወት 99ኙን ትሸነፋለህ። ያውም በሰፊ የጎል ልዩነት ነው የምትሸነፈው” ብሏል።

በትሮሳርድ ቀይ ካርድ ዙሪያ ደግሞ ሌሎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል።

ቀደም ሲል ቢጫ ካርድ የነበረበት ትሮሳርድ ሲልቫ ላይ ጥፋት ከፈጸመ በኋላ ኳሷን ሲመታት ታይቷል። በመሐል ዳኛው ማይክል ኦሊቨር ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የተመዘዘበትም ኳሷን በመምታቷ መሆኑን ፕሪሚየር ሊጉ ገልጿል።

ዠርሚ ዶኩ ተመሳሳይ ጥፋት ፈጽሞ ያለምንም ቅጣት ታልፏል ሲሉ የአርሰናል ደጋፊዎች ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

“አይቼዋለሁ። ፍርዱንም ለእናንተ እተዋለሁ” ሲል አርቴታ አክሏል።

ቡድኑ ሰዓት ለመግደል ሙከራ ሲያደርግ ነበር ለሚለው ቅሬታም ምላሽ አልሰጠም። ጨዋታው እንዲራዘም የተደረገውም አንድም በዚህ ምክንያት ነበር።

የሲቲን የአቻነት ጎል ያስቆጠረው ስቶን ለቢቢሲ ማች ኦፍ ዘ ዴይ በሰጠው አስተያየት አርሰናልን ተችቷል።

“ጨዋታውን ያቀዘቅዙት ነበር። በረኛው የተጎዳ መስሎ ተጫዋቾቹ ምክር እንዲያገኙ ሆነዋል። ጥሩ አሊያም መጥፎ ስልት ነው ልትሉት ብትችሉም ጨዋታው እየተቆራረጠ ጨዋታውን መንፈስ ረብሾታል” ብሏል።

“ይህን የሚያደርጉት ለራሳቸው ጥቅም ቢሆንም በደንብ ተቋቁመነዋል” ሲል አክሏል።

የሲቲውም አምበል ካይል ዎከር ለቢቢሲ ራዲዮ 5 “እንደእግር ኳስ ለፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ጨዋታ ነበር። አንዳንዴም አስቀያሚ አጨዋወቶች ነበሩት።”

“እንደሲቲ ተጫዋች እና ደጋፊ ደስ የማይል ቢሆንም ለአርሰናል አሰልጣኝ ግን ጥሩ ጨዋታ ነበር” ብሏል።

ኤርሊንግ ሃላንድ ቡድኑን ቀዳሚ ካደረገ በኋላ ሪካርዶ ካላፊዮሪ ባለሜዳዎቹን ያበሳጨች ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው አቻ ሆነ። ዎከር እና ቡካዮ ሳካ ከዳናው ጋር ተነጋግረው ወደ ቦታቸው ሳይመለሱ በፍጥነት ተጀምሮ የገባ ነው በሚል ሲቲዎች ቅሬታ ቢያቀርቡም ዳኛው ማይክል ኦሊቨር ጎሉን አጽድቀዋል።

ይህን ተከትሎም አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበስጭት የተቀያሪ ወንበሩን በእርግጫ ሲመታ ታይቷል። ቅሬታውንም በሰዓቱ ብቻ ሳይሆን በጨዋታ ማብቂያ ላይ ለአራተኛው ዳኛ ሲገልጽ ታይቷል።

ቀሪዎቹ ተጫዋቾች የዎከርን ቦታ መሸፈን ይችሉ እንደነበር እና ኳሱ ጋር በመቆም በፍጥነት እንዳይጀመር ማድረግ ይችሉ እንደነበረም ገልጿል። ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ነገር ከተከሰተ ዎከር ወደ ዳኛ እንዳእሄድ እንደሚነግረው እና የመሃል ዳኘቹ ወደ አምበሉ እንዲሄዱ እንደሚያደርግ አክሏል።

ሲቲ 21ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ሮድሪ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ከሜዳ ወጥቷል።

የአርሰናሉ ካይ ሃቨርትዝ ጨዋታው በጀመረ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ሮድሪን ገጭቶ ሲጥለው ቢታይም ምንም ቅጣት አልተላለፈበትም።

“ሁሉም ነገር የተጀመረው በመጀመሪያው ሰከንድ ነው። ኳሱ እንደተጀመረ ነው ምን ሊፈጠር እንደሚችል የገባን” ሲል ሲልቫ ገልጿል።

“በ10 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጫዋቾቻችንን ሜዳ ላይ ጥለዋል። ዳኛው አምበላችንን ጥርቶ ወደ ቦታው ሳይመለስ በተጀመረ ኳስ ጎል ተቆጥሮብናል።”

“ሁለተኛውን ጎል ያስቆጠሩብን በረኛውን እንዳይንቀሳቅስ አግደው ነው። ዳኛውም ፈቅዶላቸዋል። በተከታታይ ሰዓት ሲገድሉም ዝም ብሏቸዋል” ሲል አክሏል።

“አሳሳቢው ነገር በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከእግር ኳስ አስተዳዳሪው ጋር በተደጋጋሚ መሰብሰብ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገር እንደማይኖር ደጋግመው ቢገልጹልንም አሁንም እንደቀጠለ ነው። ብዙ ይናገራሉ ትንሽ ብቻ ይፈጸማል” ብሏል።

ቡድኑ ከአርሰናል ጋር ያለውን ተፎካካሪነት ከየርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ጋር እንዲያነጻጸር ሲጠየቅም “አላውቅም። ሊቨርፑል ፕሪሚየር ሊጉን አንስቷል። አርሰናል ግን አላሳካም። ሊቨርፑል ሻምፒዮንስ ሊግን ሲያሸንፍ አርሰናል ግን አላገኘም” ሲል መልሷል።

“ሊቨርፑል ፊት ለፊት ለማሸነፍ ይጋፈጠናል። ከዚህ አንጻር የአርሰናል አቸዋወት ከሊቨርፑል ይለያል” ብሏል።

አወዛጋቢ ክስተቶች ጨዋታው ላይ ተንጸባርቀዋል። አርቴታም የዳንነት ውሳኔ የጨዋታውን መልክ ባይቀይረው ይደሰት እንደነበር አስታውቋል።

“ደስተኛ አልሆንም። በተለመደው መልኩ የምንነጋገርበት ጨዋታ ሆኖ ቢያልፍ ደስተኛ እሆን ነበር። ስለዚህ ጉዳይ አሁን አናወራም። አንድም የታክቲክ ጥያቄ እስካሁን አልቀረበልኝም። ግልጽ እኮ ነው” ሲል መልሷል።