ትራምፕ ከግድያ ሙከራው በኋላ ሲፎክሩ
የምስሉ መግለጫ,ትራምፕ ከግድያ ሙከራው በኋላ ሲፎክሩ

ከ 9 ሰአት በፊት

አሜሪካውያኑ ዴዚሬ እና ከሚል በፖለቲካ አቋማቸው ሆድና ጀርባ ናቸው።

ዴዚሬ በኮሎራዶ ግዛት የገጠር ነዋሪ ናት።

በማኅበራዊ ሚዲያ ስሟ “ዋይልድ ማዘር” 80 ሺህ ተከታዮች አሏት። ለትራምፕ ነፍሷን ትሰጣለች።

ከሚል ደግሞ በኮሎራዶ ዋና ከተማ ዴንቨር ነው የምትኖረው። በፆታ እኩልነት፣ በሰብአዊ መብት እና በዘር እኩልነት ታምናለች። ለእንሰሳት ሳይቀር ትሳሳለች።

በድመቷ ስም የትዊተር (ኤክስ) አካውንት አላት፤ ከሺህ ተከታዯች ጋር።

ከሚል ዲሞክራት ናት፤ ዴዚሬ ሪፐብሊካን።

ከሚል ላለፉት 15 ዓመታት ለዲሞክራቲክ ፓርቲ ድምጽ ሰጥታለች። ትራምፕን ‘ዓይንህ ላ’ፈር’ ከሚሉት አሜሪካውያን ትመደባለች።

ሁለቱ ሴቶች በፖለቲካ አራምባና ቆቦ ቢሆኑም፣ በሚደንቅ ሁኔታ አንድ ነገር ላይ ግን ይስማማሉ።

ከወራት በፊት በፔንሴልቬንያ ግዛት ትራምፕ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ‘ድራማ’ ስለመሆኑ።

እንዲህ ዳርና ዳር፣ ጽንፍ ለጽንፍ የሆኑ ዜጎች የትራምፕን የግድያ ሙከራ ‘የተቀነባበረ ድራማ’ እንደሆነ እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምንድነው?

ሰላሳ ሚሊዮን ሰዎች የተመለኳታቸው እና በኤክስ ሰሌዳ ላይ የታተሙ መላምታዊ የሴራ ፖለቲካ ትንታኔዎች አንድ ነገር ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፤ የዶናልድ ትራምፕ ግድያ ሙከራ ድራማ ስለመሆኑ።

“ትራምፕ ይህን ግድያ ሙከራ ያቀነባበሩት ስማቸውን ከፍ ለማድረግ፣ ደጋፊዎቻቸውን ለማነሳሳት እና ቀጣዩን ምርጫ በቀላሉ እንዲያሸንፉ እንዲረዳቸው” እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ።

ዲሞክራቷ ከሚል በሴራ ትንታኔ የምታምን ሴት አይደለችም። ለማንኛውም ነገር ማስረጃ ትፈልጋለች።

ትራምፕ ላይ የተተኮሰ ዕለት ግን ገና ዜናውን እየተመለከተች “ዉይ ይሄስ ድብን ያለ ድራማ ነው” ብላ ቁጭ አለች። ተጨማሪ ማስረጃ ማገላበጥም አላሻትም።

ይበልጥ ድራማነቱ የተገለጠላት ትራምፕ ጆሮዬ በጥይት ተጨረፈ ማለታቸው ነው።

ግድያ ከተሞከረባቸው በኋላ እጃቸውን ወደ ላይ አድርገው ቀረርቶ ማሰማታቸው ሌላ ጥርጣሬዋን ያረጋገጠላት ክስተት ነው።

ከግድያ ሙከራ በኋላ ለፎቶ ተመቻችተው መቆማቸው፣ ከዚያ በኋላ ነገሩ የተድበሰበሰበት መንገድ፣ የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ ኃላፊ ሥራቸውን መልቀቅ በሙሉ ነገሩ ሁሉ አስቀድሞ የታሰበበት ‘ቀሽም ድራማ’ ሆኖ ነው የሚታያት።

ከሚል ዛሬም ድረስ ነገሩ ቅንብር እንጂ እውነት አይደለም ስትል ታምናለች። ይህን ሐሳቧንም በማኅበራዊ ሚዲያ ታጋራለች። ብዙ ሰዎች ሐሳቧን ይጋራሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ከግድያ ሙከራ ወዲህ ሲፎክሩ
የምስሉ መግለጫ,ዶናልድ ትራምፕ ከግድያ ሙከራ ወዲህ ሲፎክሩ

ዴዜሬ በበኩሏ ያበደች የትራምፕ ደጋፊ ናት። የሴራ ፖለቲካን በመፈልፈል የሚታወቀው፣ በምህጻሩ ‘ኪው-ኤ-ኖን’ (QAnon) በሚል የሚታወቀው የአክራሪው ቡድን አባልም ናት።

ይህ ቡድን ለትራምፕ የማያዋላዳ ድጋፍ ይሰጣል።

ድጋፍ መስጠት ብቻ ሳይሆን ትራምፕን አንዳች መሲህ አድርጎ ነው የሚመለከታቸው።

ለምሳሌ ብዙ የኪው-ኤ-ኖን አባላት ትራምፕ ከሰይጣን አምላኪዎች ጋር የአርማጌዶን ጦርነት ውስጥ ገብተው ሰይጣንን እየተፋለሙ እንደሆነ ያምናሉ።

ይህ ቡድን ታዲያ በትራምፕ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ የተቀነባበረ ሳይሆን አይቀርም ብሎ ያምናል።

ከዚህ ቡድን ይህ የሚጠበቅ አይመስልም። የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ ሆኖ ሳለ ለምን እንዲህ ዓይነት ሴራ እንዲነዛ ፈለገ?

ምክንያቱ ወዲህ ነው።

በዚህ ቡድን አመለካከት የትራምፕ ሰዎች አንድን ምሥጢራዊ ቡድን እየታገሉ ነው። ይህ ምሥጢራዊ ቡድን የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን አድራጊ የሰይጣናዊ ቡድን ነው።

ይህን ቡድን ለማጋለጥ አንድ ነገር መደረግ ነበረበት። ብዙ ተሞከረ። ሕዝብ ግን ሊነቃ አልቻለም። በዚህ ጊዜ የትራምፕ የውስጥ ሰዎች አንድ ብልህና ረቂቅ ዘዴ ፈጠሩ።

ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ እንዲደረግ። ያን ጊዜ ዓለም ስለ ድብቁ ዓለም አሻጥር ሁሉ ነገር ግልጥልጥ ይልለታል።

ስለዚህ የትራምፕ ሰዎች በሚወዱት ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ አሰናዱ፤ ዓለምን ለማንቃት ሲሉ።

ይህ የሴራ ትንታኔ ነው የትራምፕ ወዳጅ እና አምላኪ የሆነችውን ዴዜሬን ጭምር “የግድያ ሙከራው ድራማ ነው” እንድትል ያስደረጋት።

የሁለቱን ሴቶች የፖለቲካ ሴራ የሚያስረግጥ አንድም ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ ልብ ይሏል።

ከሚል
የምስሉ መግለጫ,ከሚል በሴራ ፖለቲካ ባታምንም የትራምፕ የግድያ ሙከራ ግን ድራማ ነው ትላለች

ከሚል በበኩሏ በፖለቲካ ሴራ ትንታኔ ብዙም አታምንም። ብዙዎቹ አክራሪ የትራምፕ ደጋፊዎች ኮቪድ-19 ውሸት ነው ይላሉ። የምርጫ 2020 ውጤት ውሸት ነው ይላሉ። ክትባት ውሸት ነው ይላሉ። እሷ ግን ይህን አትልም።

የትራምፕ የግድያ ሙከራው ግን ውሸት ነው ብላ በጽኑ ታምናለች።

ዴዜሬ በበኩሏ እንደ ከሚል ባይሆንም ድራማው ለትራምፕ ሲባል የተሰናዳ ነው ትላለች።

ትራምፕን በድብቅ ሆነው የሚታገሉ ‘የጥልቁ’ አባላትን ለማጋለጥ ነው የተቀነባበረው ብላ ታምናለች።

ዴዜሬ አሁን በኤክስ ብዙ ተከታዮች አሏት።

የሚሰድቧት፣ የሚያንጓጥጧት፣ እንዳሉ ሁሉ አድናቂዎቿም በሺህ ይቆጠራሉ።

ስለ ዌልሷ ልዕልት፣ ስለ ባልቲሞር ድልድይ መፍረስ ብዙ ሴራዎችን ታጋራለች። ከጀርባቸው አንዳች ኃይል አለ ትላለች።

ወጣት ሳለች፣ ዛሬ የደረሰችበት የማሰላሰል ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብዙ ‘ውሸቶችን’ ብዙ ‘ማታለሎችን’ እንደተታለለች ነው ዛሬ የምታምነው።

ለምሳሌ የጆን ኤፍ ኬኔዲን ግድያን፣ ለምሳሌ የመስከረም 11ዱን የሽብር ጥቃት፣ ለምሳሌ የኮቪድ ወረርሽኝን በተመለከተ አሁን ፍጹም የተለየ አመለካከት ነው ያላት።

“ስንታለል ነበር የኖርነው” ትላለች።

አሁን ስለሁሉም ነገር በሚዲያ የሚነገረውን ሁሉ አትቀበልም። የራሷ “አማራጭ እውነት”’ አላት። እውነት አንድ ናት ብላ ማመንም ትታለች።

“ልጅ እያለን አስማተኛ ይገርመን ነበር። አሁን ትልቅ ሆነን አስማተኞች እንዴት እንደሚያታልሉ እናውቃለን፤ ነገሩ እንደዚያ ነው” ትላለች።

ዴዜሬ የኪውኤነን አባል ናት። ይህ ቡድን ትራምፕ ቀደም ባለው ምርጫ በባይደን ከተሸነፉ በኋላ የአሜሪካ ምክር ቤትን ከወረሩት ቦዘኔ ቡድኖች ዋናው ነው። ነውጠኛ የትራምፕ ደጋፊዎች ስብስብ ነው።

ዲዜሬ አሁን ይህንን የትራምፕን የግድያ ሙከራ ያቀነባበሩት የዚህ ቡድን አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ትገምታለች።

ለምን ስትባል፣ “የጥልቁን ሥራ ለማጋለጥ ያን ማድረግ ነበረባቸው፤ ትራምፕ ከማን ጋር እየተናነቁ እንደሆነ ዓለም እንዲረዳ ያን ማድረግ ነበረባቸው” ትላለች።

ዲዜሪ እና ከሚል መረጃቸውን የሚጨልፉት ከማኅበራዊ ሚዲያ ነው። እሱኑ ለተከታዮቻቸው ያጋራሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያ እውነት ብለው የሚወስዱት መረጃ በየዕለቱ እየሰፋ ነው። በእውኑ ዓለምም ግንኙነታቸው እንዲያ ነው። እየሰፋ!

“አንድ እውነት ብሎ ነገር የለም” የሚለው አስተሳሰብ ልዩነቱን እያሰፋ ቀጥሏል።