የባሕር ዳርቻ

ከ 8 ሰአት በፊት

በሴኔጋል ለበርካታ ቀናት በባሕር ላይ ሲንሳፈፍ ነበር በተባለ አንድ ጀልባ ላይ የ30 ሰዎች አስክሬኖች መገኘታቸውን ወታደራዊ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የአገሪቱ መከላከያ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ከመዲናዋ ዳካር 70 ኪሎሜትር ርቆ ጀልባ ሲንሳፈፍ ከታየ በኋላ የባሕር ጠረፍ ጥበቃዎች በቦታው መገኘታቸው ተገልጿል።

ከእንጨት የተሠራውን ጀልባ ወደ ወደብ ከወሰዱት በኋላ እየፈራረሰ ያለ የሰዎች አስክሬን ተገኝቷል።

“የሰዎቹን ማንነት የመለየትና የማዘዋወር ሥራ እየተከናወነ ነው። አስክሬናቸው ካለበት የመፈራረስ ሁኔታ አንጻር ጥንቃቄ ይጠይቃል” ይላል መግለጫው።

ከሴኔጋል ወደ ስፔን ካናሪ ደሴት የሚደረጉ የስደተኞች ጉዞዎች በቁጥር እየጨመሩ ነው።

ጉዞው በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከ1,500 ኪሎሜትር በላይ ይሸፍናል።

የተገኙት አስክሬኖች ያሉበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ስደተኞቹ ለቀናት ሕይወታቸው አልፎ ውሃ ላይ ሲንሳፈፉ እንደነበር ተገልጿል።

ዓሣ አስጋሪዎች ጀልባውን አይተው ጥቆማ ከሰጡ በኋላ ነው ጀልባዋ በአገሪቱ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ልትገኝ የቻለችው።

ጀልባዋ ከየትና መቼ እንደተነሳች፣ ምን ያህል ሰዎች እንደተሳፈሩባ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው።

ነሐሴ ላይ ቢያንስ 14 አስክሬኖች በዶምኒካን ሪፐብሊክ ተገኝተዋል። ሟቾቹ ሴኔጋላውያን ስደተኞች እንደሆኑ የታመነ ሲሆን፣ አስክሬናቸው የተገኘው በዓሣ አስጋሪዎች ነው።

የሴኔጋል መንግሥት ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጠርና ከስደት ጋር የተያያዘ ሞትን ለመግታት የ10 ዓመት ዕቅድ አውጥቷል።

በቅርብ ሳምንታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በጀልባ ሲጓዙ ተይዘዋል።

ስደተኞች እየሞቱ ቢሆንም ሥራ አጥነት፣ ግጭት እና ድህነት ወጣት ወንዶች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በምዕራብ አፍሪካ በኩል ወደ ስፔን ካናሪ ደሴት እንዲጓዙ ምክንያት ሆኗል።

አንዳንድ ሴኔጋላዊ ዓሣ አስጋሪዎች ዓሣ በማስገር ብቻ መኖር እንደማይችሉ ይናገራሉ። መሰደድን አማራጭ የሚያደርጉትም ለዚህ ነው። ጀልባቸውን ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርም ያቀርባሉ።

ወጣት ምዕራብ አፍሪካውያን ስደተኞች በካናሪ ደሴት አድርገው ወደ አውሮፓ ለመግባት ይሞክራሉ።

ይህ መንገድ አደገኛ ቢሆንም ሳህል በረሃን እና ሜድትራቢያን ባሕርን ማቋረጥ አይጠይቅም።

የአውሮፓ የድንበር ኤጀንሲ ፍሮንቴክስ እንዳለው እአአ በ2023 በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል የሚደረግ የስደተኞች ጉዞ በ161 በመቶ ጨምሯል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም አምና ወደ 40,000 ስደተኞች ካናሪ ደሴት መድረሳቸውን አመልክቷል።

ወደ 1,000 የሚጠጉት በዚህ ጉዞ ሞተዋል አልያም መጥፋታቸው የተመዘገበ ሲሆን፣ ትክክለኛ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይታመናል።