ቴሌግራም መተግበሪያ
የምስሉ መግለጫ,ቴሌግራም ለወንጀለኞች መደበቂያ ሆኗል በሚል ይወቀሳል

ከ 8 ሰአት በፊት

በዓለም ታዋቂ ከሆኑ የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎች አንዱ የሆነው ቴሌግራም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የደንበኞቹን መረጃዎች ለሕግ አካላት አሳልፎ ሊሰጥ ነው።

በዚህም የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ስልክ ቁጥሮች፣ የኢንተርኔት አድራሻ እና ሌሎች መረጃዎ በፖሊስ፣ በፍርድ ቤት በመሳሰሉ የሕግ ተርጓሚዎች በሚፈለግበት ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል የመተግበሪያው አስተዳዳሪ ተቋም አሳውቋል።

የቴሌግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፔቨል ዱሮቭ ይህ አዲስ ደንብ መተግበሪያውን ለወንጀል የሚጠቀሙት ሰዎችን “ቅስም የሚሰብር ይሆናል” ብለዋል።

“99.999% የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ከወንጀል ጋር የሚያያይዛቸው አንዳችም ነገር የለም። 0.001% የሚሆኑት ግን ለድብቅ ወንጀል እየተጠቀሙበት የቴሌግራምን ዝና እና ክብርን እያጎደፉት ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ቢሊዮን የሚጠጉ ጨዋ ተጠቃሚዎቻችን የሚጎዳ ነው” ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።

የቴሌግራም መተግበሪያ ፈጣሪ እና ከመሥራቾች አንዱ የሆኑት ትውልደ ሩሲያዊው ዱሮቭ ባለፈው ወር በፓሪስ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር አይዘነጋም።

በፖሊስ ከተያዙ በኋላ የቀረበባቸው ክስ መተግበሪያው ለወንጀለኞች መፈንጫ እንዲሆን ፈቅደዋል የሚል ነበር።

ሕገ ወጥ የሕጻናት ምስሎች ዝውውር እና የአደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን በሚያበረታታ መልኩ መተግበሪያው ለወንጀል ተግባር እንዲውል ፈቅደዋል በሚል የተከሰሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሕግ አካላት ጋር ባለመተባበርም ተወንጅለው ነበር።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በበኩላቸው ሌሎች ለፈጸሙት ወንጀል እሳቸው ተከሳሽ መሆናቸው “አስደናቂ እና ግራ የሚያጋባ” ነገር ነው ሲሉ የፈረንሳይ ባለሥልጣናትን ወርፈው ነበር።

የቴሌግራም መሥራች ፓፌል ድሮቭ
የምስሉ መግለጫ,የቴሌግራም መሥራች ፓፌል ድሮቭ

የመተግበሪያው ተቺዎች እንደሚሉት ግን ቴሌግራም የደንበኞቹን መረጃዎች ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ የማይሰጥ በመሆኑ ለሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ለአደገኛ እጽ ዝውውር እና ለሽብር ተግባር ሁነኛ የግንኙነት መንገድ ፈጥሯል ሲሉ ይወቅሱታል።

ቴሌግራም ላይ የተፈጠረ ቡድን (ግሩፕ) በአንድ ጊዜ እስከ 200 ሺህ አባላት ሊኖሩት ይችላሉ። ይህም ለወንጀለኞች ምቾትን ፈጥሯል ይላሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች።

ሜታ የሚያስተዳድረው ዋትስአፕ መተግበሪያ ግን የቡድን (ግሩፕ) አባላት መጠንን በአንድ ሺህ ገድቦታል።

ቴሌግራም መተግበሪያ በዩናይትድ ኪንግደም ከተሞች ባለፈው ወር ለተፈጠረው ነውጥ ጥሩ መድረክ ሆኖ አገልግሏል በሚል ይተቻል።

በዚህ ሳምንት ደግሞ ዩክሬን በሩሲያ ሊቃጣብኝ የሚችል ጥቃትን ለመከላከል በሚል ዜጎቿ ቴሌግራምን መንግሥት በሚያውቃቸው ስልኮች ላይ እንዳይጠቀሙ ከልክላለች።

የ39 ዓመቱ የቴሌግራም መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ በፓሪስ በቁጥጥር ሥር መዋል ከንግግር ነጻነት መገደብ ጋር በመያያዙ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ቴሌግራም፣ አምባገነን መንግሥታት ባሉባቸው አገራት እንደ ሁነኛ የመረጃ መለዋወጫ መድረክ ሆኖ ዜጎችን ሲያገለግል ቆይቷል። አሁን የተደረገው ለውጥ ግን ብዙዎችን ስጋት ላይ የሚጥል መሆኑ እየተነገረ ነው።

ቴሌግራም ይህን ለውጥ ከማድረጉ በፊት ለባለሥልጣናት የደንበኞቹን አድራሻ አሳልፎ ይሰጥ የነበረው በሽብር ከተጠረጠሩ ብቻ ነበር።