እስራኤል ታይር ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃት
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል ታይር ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃት

ከ 7 ሰአት በፊት

በሊባኖስ ሄዝቦላህ ላይ ባነጣጠረው የእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 492 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። በዚህም ከ20 ዓመታት ወዲህ እጅግ አስከፊው ቀን ሆኖ ተመዝግቧል።

ሄዝቦላህ እአአ ከ2006 ወዲህ የገነባቸውን መሰረተ ልማቶችን ለማውደም የእስራኤል ጦር በወሰደው እርምጃ አንድ ሺህ 300 የቡድኑን ዒላማዎችን መምታቷን ገልጻለች። በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ደግሞ ቤታቸውን ጥለው ተወሰደዋል።

ሄዝቦላህ በበኩሉ ከ200 በላይ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ማስወንጨፉን አስታውቋል። በስለታማ ነገሮች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ሁለቱም ወገኖች ወደ ሁሉን አቀፍ ጦርነት እየተቃረቡ ባሉበት ወቅት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሟቾች መካከል 35 ህጻናት እና 58 ሴቶች መኖራቸውን እና ሌሎች አንድ ሺህ 645 ሰዎች ቆስለዋል ብሏል።

ከሟቾቹ መካከል ምን ያህሉ ሲቪሎች እና ታጣቂዎች እንደሆኑ አልገለጸም።

በጥቃቱ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችም መፈናቀላቸውን የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ፍራስ አቢያድ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እየተባባሰ በመጣው ሁኔታ ስጋት እንዳደረባቸው እና ሊባኖስ “ሌላኛዋ ጋዛ እንድትሆን” እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው የዓለም መሪዎች በኒው ዮርክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ከመታደማቸው በፊት “ግጭቱ እጅግ አደገኛ እና አሳሳቢ ነው” ከማለት ባለፈ “ሙሉ በሙሉ ጦርነት ውስጥ ነን ማለት ይቻላል” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ “ሰዎች በሠላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በሚያስችል መልኩ እየሠራን ነው” ብለዋል። ፔንታጎን በበኩሉ “ለጥንቃቄ ሲባል አነስተኛ ቁጥር” ያለው ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንደሚልክ አስታውቋል።

በጋዛ ጦርነት ምክንያት በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል በተቀሰቀሰው የድንበር ተሻጋሪ ግጭት ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ አብዛኛዎቹ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ሲሆኑ ከድንበሩ በሁለቱም አቅጣጫ የሚኖሩ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

ሄዝቦላህ ሃማስን በመደገፍ ላይ መሆኑን እና በጋዛ የተኩስ አቁም እስከሚደረስ ድረስ ድጋፉን እንደማያቆም ተናግሯል። ሁለቱም ቡድኖች በኢራን የሚደገፉ ሲሆን በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች አገራት በአሸባሪነት የተፈረጁ ናቸው።

ጥቃቱን በመሸሽ ከደቡባዊ ሊባኖስ በርካታ ሰዎች በመኪና ሲወጡ
የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱን በመሸሽ ከደቡባዊ ሊባኖስ በርካታ ሰዎች በመኪና ሲወጡ

ፔንታጎን እየጨመረ በመጣው ቀውስ ምክንያት “ጥቂት” ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እየላከ መሆኑን ገልጿል።

“በመካከለኛው ምስራቅ ካለው ከፍተኛ ውጥረት አንፃር አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ቦታው እየላክን ነው” ሲሉ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ፓት ራይደር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በዝርዝር ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

የሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የእስራኤል የመጀመሪያ ጥቃት የጀመረው ሰኞ ጠዋት 12፡30 ሰዓት ገደማ ነው።

“በጣም አስፈሪ ነበር። ሚሳኤሎቹ በጭንቅላታችን ላይ ሲያልፉ ነበር። የቦምብ ፍንዳታ ሲሰማ ከእንቅልፋችን ነቃን። ይህንን አልጠበቅንም” ስትል አንዲት ሴት ተናግራለች።

በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙት በሲዶና፣ ማርጃዩን፣ ናባቲህ፣ ቢንት ጀበይል፣ ጢሮስ፣ ጄዚን እና ዛህራኒ ወረዳዎች እንዲሁም በምስራቃዊ የበካ ሸለቆ ደግሞ ዛህሌ፣ ባአልቤክ እና ሄርሜል አውራጃዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ከተሞች፣ መንደሮች እና ክፍት ቦታዎች ቀኑን ሙሉ ዒላማ ተደርገው ውለዋል ሲል በመንግስት የሚተዳደረው ብሔራዊው የዜና አገልግሎት (ኤንኤንኤ) ዘግቧል።

ማምሻውን ደግሞ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ በቢር አል-አበድ አካባቢ የሚገኝ ሕንፃ በበርካታ ሚሳኤሎች ተመትቷል።

ጥቃቱ ያነጣጠረው በደቡብ ሊባኖስ በሚገኘውና የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ በሆነው አሊ ካራኪ ላይ መሆኑን የሊባኖስ የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል።

አዛዡ ስለመገደሉ ግን የታወቀ ነገር የለም። የሄዝቦላህ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ በበኩሉ ካራኪ “ደህና” መሆኑንና “ደህንነቱ ወደ ተጠበቀቦታ ተንቀሳቅሷል” ብሏል።

ከእስራኤል ጦር በድምጽ እና በጽሑፍ የተላለፈውን ከሄዝቦላህ የመሣሪያ ማከማቻዎች እንዲርቁ የተሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ጥቃቱን በመሸሽ ለመውጣት በሚሞክሩ ሰዎች ምክንያት መንገዶች ተጨናንቀው ነበር።

በሞተር ብስክሌት ከቤሩት ወደ ሰሜናዊቷ ትሪፖሊ ከተማ እያቀኑ የነበሩ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ከቢቢሲ ባደረጉት አጭር ቆይታ “ምን እንድንል ትፈልጋላችሁ? መሸሽ ነበረብን” ሲሉ ጭንቀት የገባቸው አባት ተናግረዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ዚያድ ማካሪ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ቤይሩት የሚገኘውን ህንጻ ለቆ እንዲወጣ ከእስራኤል የስልክ ጥሪ እንደደረሰው ተናግረዋል። ሆኖም “የስነ ልቦና ጦርነት” ብለው ከጠሩት ጋር አብሮ እንደማይሄድ አጥብቀው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ ከካቢኔያቸውው ጋር ባደረጉት ስብሰባ “እስራኤል በሊባኖስ ላይ የቀጠለችው ወረራ በሁሉም መልኩ የመጥፋት ጦርነት ነው” ብለዋል።

“ይህንን አዲሱን የእስራኤል ጦርነት ለማስቆም እና ወዳልታወቀ ቦታ ላለመውረድ እንደ መንግስት እየሠራን ነው” ሲሉም አክለዋል።

ለደህነታቸው በሚሸሹ ሰዎች የተዘጋጋ መንገድ
የምስሉ መግለጫ,ለደኅነታቸው በሚሸሹ ሰዎች የተዘጋጋ መንገድ

የእስራኤል መከላከያ ጦር (አይዲኤፍ) ሰኞ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ በደቡባዊ ሊባኖስ እና በበካ ሸለቆ ወደ አንድ ሺህ 300 የሚጠጉ የሄዝቦላህ “የሽብር ዒላማዎች” እና የሮኬቶች፣ የሚሳይሎች፣ የላውንቸር እና የድሮኖች ማካማቻዎችን ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

“በመሰረቱ ሄዝቦላህ ላለፉት 20 ዓመታት ሲገነባ የነበረውን የጦር መሠረተ ልማት ዒላማ እናደርጋለን። ይህ በጣም ጠቃሚ ነው” ሲሉ የአይዲኤፍ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ በቴል አቪቭ ለሚገኙ አዛዦች ተናግረዋል።

“ሁሉም ነገር ከድንበር አካባቢ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።”

የአይዲኤፍ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በበኩላቸው ከደቡብ ሊባኖስ የተገኙ ቪዲዮዎች ላይ “በህንፃዎቹ ውስጥ ተከማችተው በነበሩት የሄዝቦላህ መሳሪያዎች ከፍተኛ የሆነ ሁለተኛ ፍንዳታ መድረሱን” ያሳያሉ ብለዋል።

“ከጉዳቶቹ መካከል የተወሰኑት በእነዚህ ሁለተኛ ፍንዳታዎች የደረሱ ሳይሆኑ አይቀርም” ሲሉም አክለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሊባኖስ ህዝብ “ጥቃት ከሚሰነዘርባቸው አካባቢዎች በፍጥት እንዲወጡ” አሳስበዋል።

“ለረዥም ጊዜ ሄዝቦላህ እናንተን እንደ ጋሻ ሲጠቀምባችሁ ቆይቷል። በመኖሪያ ክፍሎቻችሁ ውስጥ ሮኬቶችን እና ሚሳኤሎችን አስቀምጧል። ህዝባችንን ከሄዝቦላህ ጥቃት ለመከላከል እነዚህን መሳሪያዎች ማስወገድ አለብን” ብለዋል።

አንድ የእስራኤል ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን አይዲኤፍ በደቡብ ሊባኖስ ምድር ጦር ሊያዘምት ተቃርቧል ተብሎ በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “አሁን ትኩረቱ በአየር ጥቃት ላይ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው” በማለት አጥብቀው ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ እስራኤል ሦስት ዓላማዎች እንዳሏት ተናግረዋል። በዚህም ሄዝቦላህ በሊባኖስና በእስራኤል ድንበር አቅራቢያ ሮኬቶችን እና ሚሳኤሎችን የመተኮስ አቅሙን ዝቅ ማድረግ፤ ተዋጊዎቹን ከድንበር እራቢያ ማራቅ እና የእስራኤል ማህበረሰቦችን ለማትቃት በሄዝቦላህ ትልቁ ራድዋን ፎርስ የተገነባውን መሠረተ ልማት ማውደም እና ማጥፋት ናቸው ብለዋል።

በመኖሪያ ቤት የጦር መሳሪያዎችን ደብቋል ስትል እስራኤል ላቀረበችው ክስ ሄዝቦላህ ምንም ምላሽ አልሰጠም። የመገናኛ ብዙሃን ፅህፈት ቤቱ ሰኞ ማምሻውን በደረሰ ጥቃት የአንድ ተዋጊው ህይወት ማለፉን አስታውቋል።

የአጸፋ ጥቃት እንደሚሰነዘር ለማሳየትም በሰሜን እስራኤል በሚገኙ በርካታ የእስራኤል ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ሮኬቶችን በመተኮስ “ለእስራኤል ጠላት ጥቃት” ምላሽ እንደሰጠ ተናግሯል። ከሃይፋ ከተማ በስተሰሜን በዝቩሉን ባህር ዳርቻው አካባቢ የሚገኝን የጦር መሳሪያ ማምረቻ ተቋምን ዒላማ ማድረጉንም አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ምሽት ላይ 210 ሚሳኤሎች ከሊባኖስ ተሻግረው እንደነበር እና በቁጥር ያልተገለጹት ደግሞ በታችኛው ገሊላ እና በላይኛው ገሊላ ክልሎች በሃይፋ እና በአቅራቢያው ባሉት የቀርሜሎስ፣ ሃአማኪም እና ሃሚፍራዝ አካባቢዎች እንዲሁም ጎላን ተራሮች ላይ አርፈዋል ብሏል።

ከሊባኖስ በተተኮሰ ሮኬት በሰሜን እስረኤል የወደመ መኖሪያ ቤት
የምስሉ መግለጫ,ከሊባኖስ በተተኮሰ ሮኬት በሰሜን እስረኤል የወደመ መኖሪያ ቤት

በታችኛው ገሊላ ጊቫት አቭኒ ውስጥ አንድ መኖሪያ ቤት በሮኬት ክፉኛ ተጎድቷል።

የቤቱ ነዋሪ የሆነው ዴቪድ ይስሃቅ ለቢቢሲ እንደተናገረው እሱ፣ ባለቤቱ እና የስድስት ዓመት ሴት ልጁ የማስጠንቀቂያ ድምጽ በመስማታቸው እና በቤቱ ጠንካራ የደህንነት መጠበቂያ በመሸሸጋቸው ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም።

“በህይወት እና በሞት መካከል የነበረው ርቀት አንድ ሜትር ነው” ብሏል።

የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት በበኩሉ በታችኛው እና በላይኛው ገሊላ ክልሎች ውስጥ ወደ መጠለያ ሲሸሹ የነበሩ ሁለት ሰዎች በስለታማ ነገር ቆስለዋል ብሏል።

እሑድ ዕለት ሄዝቦላህ ከ150 በላይ ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ድንበር አቋርጦ ያስወነጨፈ ሲሆን የእስራኤል ጄቶች ደግሞ በደቡብ ሊባኖስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዒላማዎችን ደበድበዋል።

የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሄዝቦላህ ከተመሰረተ በኋላ “በጣም አስቸጋሪውን ሳምንት” ማሳለፉን ቢገልጽም ተዳክሞም ቢሆን ሄዝቦላህ ጠንካራ ሃይል ሆኖ ቀጥሏል።

ማክሰኞ እና ረቡዕ ሄዝቦላህ የሚጠቀምባቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎች ከፈነዱ በኋላ 39 ሰዎች ሲሞቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። አርብ ዕለት በደቡባዊ ቤይሩት እስራኤል በሰነዘረችው የአየር ጥቃት ከ45 ሰዎች ሲገደሉ፤ የራድዋን ፎርስ ከፍተኛ አዛዦችን ጨምሮ ቢያንስ 16 አባላት እንደሞቱ ሄዝቦላህ ገልጿል።

የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ናኢም ቃሴም እሑድ በተከናወነ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ቡድኑ ምንም ተስፋ እንደማይቆርጥ ተናግረዋል።

“ወደ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል። ርዕሱም ማቆሚያ የሌለው ጦርነት ነው” ብለዋል።

በቤይሩት ጎዳናዎች ላይ አንድ ወጣት ለቢቢሲ እንደገለጸው “ብዙ አደጋ ስለሚያስከትል እና ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን ስለሚያቆሙ ጦርነቱ እየጨመረ በመሄዱ በጣም መፍራቱን” ገልጿል።

ሌላ ግለሰብ በበኩሉ “አንፈራም። ጠንካራ ሆነን በመቆም ራሳችንን መከላከል አለብን” በማለት ተናግሯል።