የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ
የምስሉ መግለጫ,የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ

ከ 5 ሰአት በፊት

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ “የውጭ ኃይሎች” ወደ ሶማሊያ የሚልኳቸው የጦር መሳሪያዎች “በአሸባሪዎች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ” የሚል ስጋታቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ ገለጹ።

አምባሳደር ታዬ፤ ይህንን ስጋታቸውን የገለጹት በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ካለው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ትናንት ሰኞ መስከረም 13/2016 ዓ.ም. ከረዳት ዋና ፀሐፊዋ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት በሙሉ በሚሰበሰቡበት በዚህ ዓመቱ ጉባኤ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ፤ የአገሪቱን “ጥቅም የበለጠ ለማሳደግ” ከዋና ጉባኤው በተጨማሪ የጎን ስብሰባዎች እንደሚደርግ እና ሁነቶች ላይ እንደሚሳተፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ገልጾ ነበር።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ፤ እስካሁን ከቻይና፣ ከአልጄሪያ እና ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸው ተገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝሜሪም፤ ከጉባኤው ጎን ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ከተወያዩት ዲፕሎማቶች መካከል ናቸው።

የአምባሳደር ታዬ እና ረዳት ዋና ፀሐፊዋ ውይይት “የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ” ላይ ያተኮረ እንደሆነ ሮዝሜሪ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቅሰዋል። ሁለቱ ዲፕሎማቶች ባደረጉት ንግግር የጎረቤት አገራት ሱዳን እና ሶማሊያ ጉዳይ መነሳቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውይይቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

አምባሳደር ታዬ፤ ጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን በተመለከተ ለረዳት ዋና ፀሐፊዋ ባደረጉት ገለጻ፤ በአገሪቱ ሰላም ለማምጣት “የተቀናጀ ጥረት” እንደሚያስፈልግ ማንሳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያ በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት የፖለቲካ መፍትሔ እንደሚያሻው ስትወተውት መቆየቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ተብሏል።

በአምባሳደር ታዬ እና ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝሜሪ ውይይት ላይ ከሶማሊያን ጋር በተያያዘ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ “የውጭ ኃይሎች” ወደ አገሪቱ የሚልኳቸው የጦር መሳሪያዎችን የሚመለከት እንደሚገኝበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሃፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “የውጭ ኃይል” ያሉትን አካል በስም ባይገልጹም፤ ይህ ንግግራቸው የተሰማው ግብፅ ወደ ሶማሊያ የላከችው ሁለተኛ ዙር የጦር መሳሪያ አቅርቦት ወደ ሞቃዲሾ በደረሰ ማግስት ነው።

ባለፉት ቀናት በመርከብ ተጭነው ሞቃዲሾ ወደብ የደረሱት የጦር መሳሪያዎች ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ መድፎች እና ሌሎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች እንደሆኑ አንድ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። በቀጣዮቹ ጊዜያትም ከግብፅ የሚላኩ ታንኮች ወደ ሶማሊያ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

ባለፈው ነሐሴ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የፈረመችው ግብፅ፤ ስምምነቱ በተደረገ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶችን የጫኑ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ ሞቃዲሾ ልካ ነበር።

ወደ ሶማሊያ የሚገባ የጦር መሳሪያን ጉዳይ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ያነሱት አምባሳደር ታዬ፤ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል ተብሏል።

አምባሳደር ታዬ፤ “በውጭ ኃይሎች [ለሶማሊያ] የሚደረግ የመሳሪያ አቅርቦት የተዳከመውን የፀጥታ ሁኔታ ይበልጥ እንደሚያባብስ እና በአሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል” ስጋታቸውን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ውይይት ላይ በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ተልኮ ላይ ካለው በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ልዑክን (አትሚስ) በተመለከተ ማንሳታቸውም ተገልጿል።

በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብ ለመቆጣጠር ከዚህ ቀደም የነበረው የሰላም አስከባሪ ልዑክ በጊዜያዊነት የተካው አትሚስ፤ በመጪው ጥር ወር የሥራ ጊዜው ይጠናቀቃል። በቀጣይ አትሚስን በሚተካው ልዑክ ውስጥ ኢትዮጵያም የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ስትገልፅ ቆይታለች።

ከዋና ፀሐፊዋ ጋር በነበረው ውይይት ላይ “ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስታደርግ የነበረውን ጥረት” ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ፤ ድኅረ አትሚስ የሚኖረው ተልዕኮ አወቃቀር ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት “አስፈላጊው” ውይይት መድረግ እንዳለበት ገልጸዋል ተብለዋል።

አምባሳደር ታዬ፤ “ማንኛው ድኅረ አትሚስ የሚደረግ ሂደት መወሰን ያለበት [ተልዕኮው የሚኖረውን] ኃላፊነት፣ ብዛት፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና ትብብር ጨምሮ ሁሉም የተልዕኮው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በቂ ጊዜ ከተወሰደ በኋላ መሆን አንዳለበት” በአጽንኦት ማንሳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊዋ ሮዝሜሪ በበኩላቸው ድርጅቱ “በቀጣናው እና ከዚያም ባለፈ [በሚኖሩ] የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ” መሆኑን ገልጸዋል ተብሏል።